በጠገዴ ከታዳጊዎቹ ግድያ ጋር በተያያዘ የተጠረጠሩ ተይዘዋል፤ ክትትሉ ቀጥሏል- የወረዳው ፖሊስ

የፎቶው ባለመብት, Google map
በማዕከላዊ ጎንደር ዞን፤ ጠገዴ ወረዳ ታግተው ከተወሰዱ ስምንት ታዳጊዎች መካከል ስድስቱ መገደላቸውን መዘገባችን ይታወሳል።
ታዳጊዎቹ ማንነታቸው ባልታወቁ ሰዎች ታግተው የተወሰዱት ታህሳስ 10 ቀን 2012 ዓ.ም ከሰዓት አካባቢ ማይዳራ በሚባል ወንዝ አካባቢ ከብት በመጠበቅ ላይ ሳሉ ነበር።
እድሜያቸው ከ10-16 የሚሆኑት ታዳጊዎች፤ ለቀናት ታግተው አጋቾቻቸው የጠየቁት ገንዘብ ሳይከፈል በመቅረቱ በጥይት ተገድለዋል።
ከሟቾቹ መካከል አንዱ ጥጋቡ ደሳለኝ የተባለ የ10 ዓመት ታዳጊ ነው። ጥጋቡ ለቤተሰቦቹ ሦስተኛ ልጅ ሲሆን የመጀመሪያ ወንድ ልጅም ነው። አባቱን በመስክ ሥራዎች ለማገዝ በተለያየ ጊዜ ትምህርቱን ቢያቋርጥም ሁለተኛ ክፍል ግን ደርሶ ነበር።
ቢቢሲ ያነጋገራቸው የጥጋቡ አባት አቶ ደሳለኝ ማለደ "ልጄ በቤተሰቡም ሆነ በትምህርት ቤቱ የተወደደ፣ ታዛዥና ሰው አክባሪ ነበር'' ሲሉ በሀዘን በተሰበረ ልብ ይገልፁታል።
ጥጋቡ ከቤት እንደወጣ ባልተመለሰበት ታህሳስ 10 ቀን 2012 ዓ.ም ትምህርት ቤት አልሄደም ነበር። አባቱ ሰብል ለመሰብሰብ ወደ እርሻቸው ሄደው ስለነበር እርሳቸውን ለማገዝ እርሱም ከብቶቹን ይዞ ወደ መሥክ ሥራ ተሰማራ። ሰዓቱ ከቀኑ ከ8፡00 ገደማ ይሆናል።
ጥጋቡ ግን ወደ ቤቱ አልተመለሰም።
ማታ ወደ ቤት ይመለሳል ተብሎ ሲጠበቅ የነበረውን ጥጋቡን ትተው፤ ከብቶቹ ወደ ቤታቸው አመሩ። እርሱ ግን የውሃ ሽታ ሆነ። በሁኔታው የተደናገጡት ቤተሰቦች አመሻሽ 12 ሰዓት ጀምሮ ፍለጋቸውን ጀመሩ።
"ከዚህ በፊት ህፃናት ተይዘው ባያውቁም፤ በአካባቢው ሽፍቶች በመኖራቸው ይዘውት ይሆናል፤ ምን የበደልኩት ነገር ይኖር ይሆን?" በማለት ሰው እየጠየቁ፣ በርሃና ጥሻውን እያቆራረጡ ሲፈልጉ አደሩ።
በማግስቱም ታህሳስ 11 ቀን 2012 ዓ.ም ልጆቹን ያገቷቸው ግለሰቦች ደውለው "አስረናቸዋል" ሲሉ ነገሯቸው። ልጃቸው ከማን ጋር በምን ሁኔታ እንዳለ ቁርጡ የተነገራቸው አባት ታዲያ፤ ለወረዳው ፖሊስ ጣቢያ "ልጄ ታግቷል" ሲሉ አመለከቱ።
አመልክተውም ግን ዝም አላሉም። የወለደ አንጀት አይችልምና በወረዳው እና በአጎራባች ወረዳ፤ ምዕራብ አርማጭሆ ድረስ ሲፈልጉት ከረሙ። በተለያየ ቦታ ስልክ እየደወሉ፤ እየጠየቁ ማፈላለጉን ቀጠሉ።
በዚህ ሁኔታ ላይ ሳሉ ከአጋቾቹ ስልክ ተደወለ። 'ስምንት ሕፃናት ይዘናል፤ ለእያንዳንዳቸው 120 ሺህ ብር ይዛችሁ ኑ' ሚል ትዕዛዝ ደረሳቸው።
"እኛ ድሆች ነን። ብር የለንም፤ ምንስ ተገኝቶ ነው? ፤ ምንስ በድለናችሁ ነው?" ሲሉ ይጠይቃሉ።
"ብር ነው የምንፈልገው ሌላ ጉዳይ የለንም፤ ገንዘብ አላችሁ፤ ተካፍለን እንብላ" ሲሉ እቅጩን ነገሯቸው። በሁኔታው ግራ የተጋቡት ቤተሰቦች በተደወለበት ስልክ እየደወሉ "ብር አላገኘንም፤ እያሰባሰብን ነው፤ እባካችሁ ልጆቹን ስደዱልን" እያሉ ልጆቹ እንዳይጎዱና እንዳይገርፉ ሲለምኑ፤ አጋቾቹም ሲደውሉ ሰነበቱ።
"ገንዘብ ይዛችሁ ካልመጣችሁ እርምጃ እንወስዳለን" እያሉ ያስፈራሯቸው እንደነበር አቶ ደሳለኝ ይናገራሉ። አጋቾቹ ለልጆቹም ስልክ እየሰጡ "ገንዘብ ይዛችሁ የማትመጡ ከሆነ፤ አታገኙንም" እንዲሉ ያደርጓቸው ነበር።
"ልጆች ናቸው። ምን በደሏችሁ?፤ እኛ አልበደልናችሁ። እባካችሁ!" እያሉ እየተለማመጡ ነበር። ግን ይገድሏቸዋል የሚል ሃሳብ ፈፅሞ እንዳልነበራቸው አቶ ደሳለኝ ይናገራሉ።
ያሳለፉትን ቀናትም "በአፋችን እሳት በሆዳችን እሳት እየወጣ ነው የሰነበትነው" ሲሉ ይገልፁታል።
በዚህ ሁኔታ ላይ ሳሉ ታህሳስ 19 ቀን ልጃቸው ከሌሎች ጓደኞቹ ጋር እንደተገደለ ከወረዳው ፖሊስ ተደውሎ ተነገራቸው።
በልጃቸው ላይ ይህ ከሆነ በኋላ፤ እንኳን ለልጆቻቸው ለራሳቸውም ስጋት እንዳደረባቸው፤ ቀሪዎቹ ልጆቻቸውም ቤት ውስጥ እንደሚውሉ ይናገራሉ።
የጠገዴ ወረዳ ፖሊስ ፅ/ቤት ተወካይ ኃላፊ ኢንስፔክተር እሸቴ ገ/ማሪያም ከግድያው ጋር በተያያዘ ዘጠኝ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውንና አሁንም ፍለጋው ተጠናክሮ መቀጠሉን ያስረዳሉ።
እርሳቸው እንደሚሉት ከቤተሰብ የልጆቹ መጥፋት ጥቆማ እንደደረሳቸው፤ አጋቾቹ ደውለውበታል የተባለውን የስልክ መስመር ለማጣራት ወደ አካባቢው ኢትዮ ቴሌኮም መሥሪያ ቤት ደብዳቤ ፃፉ።
ተጣርቶም የስልክ መስመሩ ባለቤት ማንነት ተነገራቸው። ግለሰቡ በቁጥጥር ሥር ከዋለ በኋላ ሲጠየቅ "ለአጎቴ ሸጨለታለሁ" ይላል። የስልክ መስመሩ የተሸጠላቸው አጎት የሚገኙበትን ሌላ ስልክ ፖሊስ ከተቀበለ በኋላ ባደረገው ማጣራት፤ ግለሰቡ መቀሌ ከተማ እንደሚገኙ ማወቅ ችለዋል።
ግለሰቡን በቁጥጥር ሥር አውሎ ለመመርመር የሚገኙት በሌላ ክልል ውስጥ በመሆኑ ጉዳዩን የፌደራል መንግሥት ጸጥታ አስከባሪ ኃይል እንዲይዘው በማድረግ እየተሠራ መሆኑን ኢንስፔክተሩ ገልፀውልናል።
በሌላ በኩል በአካባቢው 'ሽፍታዎች' አልፎ አልፎ አሽከርካሪዎችን፣ ግለሰቦችን በማገት ገንዘብ የመጠየቅ ልማድ እንዳለ የሚናገሩት ኢንስፔክተሩ፤ ከዚህ ቀደምም በቁጥጥር ሥር የዋሉ ሽፍቶች መኖራቸውን ያስታውሳሉ።
ኢንስፔክተር እሸቴ እንደሚሉት፤ ከህፃናቱ ግድያ ጋር በተገናኘም በአካባቢው ሽፍታ ተብለው የሚንቀሳቀሱ ግለሰቦች ቤተሰቦች በስጋት ተሰውረዋል።
በአካባቢው በቀል ስላለ እርሱን ሽሽት መሰወራቸው እንዲሁም ከግድያው ከተረፈው ልጅ ከሰሙት ቃል ግድያውን የፈፀሙት ሽፍታዎች ሳይሆኑ እንዳልቀሩ ሌላ ፍንጭ እንደሰጣቸው ተናግረዋል። እስካሁንም ስምንት የሚሆኑ የሽፍታ ቤተሰቦች በቁጥጥር ሥር ውለዋል።
በአካባቢው በተለያየ ምክንያት የሸፈቱ 'ሽፍታዎች' የሚታወቁ ቢሆንም፤ እነርሱን አድኖ ለመያዝ ግን የአካባቢው መልከዓ ምድራዊ ሁኔታና ግለሰቦቹ ከቦታ ቦታ ስለሚንቀሳቀሱ አዳጋች ሆኖ መቆየቱን ገልፀዋል።














