ሆንግ ኮንግ የፈረንጆቹን አዲስ ዓመት በተቃውሞ ተቀበለች

People hold a banner reading "Fight" as they take part in an anti-government rally on New Year's Day in Hong Kong

የፎቶው ባለመብት, EPA

በዐሥር ሺዎች የሚቆጠሩ ሆንግ ኮንጋውያን አዲሱን የፈረንጆች ዓመት በከባድ ተቃውሞ ተቀብለውታል።

ምንም እንኳን ተቃውሞው ሰላማዊ እንዲሆን ታስቦ የነበረ ቢሆንም ሰልፈኞች ከፖሊስ ጋር ተጋጭተዋል ተብሏል። ከስድስት ወራት በላይ የፈጀው የሆንግ ኮንግ ተቃውሞ በአዲሱ ዓመትም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ይጠበቃል።

ፖሊስ ሰልፈኞቹን ለመበተን አስለቃሽ ጭስ ለመጠቀም የተገደደ ሲሆን በሰዎች ላይ የደረሰ ጉዳት ግን የለም ተብሏል።

በአዲስ ዓመት ዋዜማ ተዋቃሚ ሰልፈኞች በአንድ ከፍተኛ ንግድ በሚደረግበት ጎዳና አካባቢ ተሰባስበው በመያያዝ የሰው ሰልሰለት ሠርተዋል። መንገዱንም መዝጋታቸው ታውቋል።

አዲስ ዓመት ሊገባ ሲል የቀሩትን ሰከንዶች በመቁጠር ፋንታ ከአስር ከጀመሩ በኋላ ሆንግ "ኮንግ ነጻ ትውጣ፣ አብዮት አሁኑኑ!" የሚሉ መፈክሮችን አሰምተዋል።

ሞንግ ኮክ በሚባለው ታዋቂ የገበያ ሥፍራ ደግሞ ሰልፈኞች መንገድ መከላከያዎችን በእሳት በማያያዝና ርችቶችን በመተኮስ የመኪና እንቅስቃሴዎችን ሲያስተጓጉሉ ነበር ተብሏል።

ሰልፈኞች በብዛት በሚገኙባቸው አካባቢዎች ፖሊስ አስለቃሽ ጭስና የጎማ ጥይቶችን ተጠቅሟል ሲል የደቡብ ቻይናው 'ሞርኒንግ ፖስት' ዘግቧል።

40 የሚደርሱ የፓርላማ አባላትና ከ18 ሀገራት የተውጣጡ ልኡካን ለሆንግ ኮንግ መሪ ኬሪ ላም በላኩት ይፋዊ ደብዳቤ የሆንግ ኮንግ ህዝብን ጥያቄ በአግባቡ እንዲያስተናግዱና የወደፊቱን ከግምት ውስጥ እንዲያስገቡ ጠይቀዋቸዋል።

An aerial shot shows thousands of protesters filling a street for a rally on New Year's Day in Hong Kong

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ከወራት በፊት በሆንግ ኮንግ የተቀሰቀሰው ተቃውሞ መነሾው ወንጀለኞችን ለቻይና አሳልፎ ከመስጠት ጋር የተያያዘ ቢሆንም በጊዜ ብዛት ወደ ድንበር ጥያቄና ሙሉ ዴሞክራሲ ስለማግኘት ወደሚሉ ጥያቄዎች አድጓል።

በዚህም መሰረት አምስት ዋነኛ ግቦችን አስቀመጠዋል ሰልፈኞች።

የመጀመሪያው በፖሊስ ቁጥጥር ስር የሚገኙ እንዲለቀቁ፣ ሁለተኛ ያለአግባብ ኃይል ተጠቅሟል የሚሉት ፖሊስ እንዲጠየቅ፣ ሶስተኛ ሁሉም እድሜው ለምርጫ የበቃ ዜጋ እንዲመርጥ፣ አራተኛ ሰልፈኞቹ የሚያደርጉት ተቃውሞ እንደ አመጽ እንዳይቆጠርና አምስተኛ አከራካሪው ወንጀለኞችን ለቻይና መስጠት የሚለው ህግ እንዲቀር ናቸው።

ሆንግ ኮንግ እስከ አውሮፓውያኑ 1997 ድረስ በእንግሊዝ ቅኝ ግዛት ስር የነበረች ሲሆን ከጊዜ በኋላ አንድ ሀገር ሁለት ስርአቶች በሚል መመሪኣ መሰረት ለቻይና ተልፋ ተሰጥታለች።

ምንም እንኳን ሆንግ ኮንግ የቻይና አካል ብትሆንም የራሷ የሆነ የህግ ስርአት፣ ድንበር እና ሌሎች መብቶች አሏት። ባለፉት ወራት በተከታታይ ሲደረጉ ከነበሩት የተቃውሞ ሰልፎች ጋር በተያያዘ 6500 ሰዎች በቁጥጥር ስር ውለዋል።