የጠቅላይ ሚኒስትሩ ፓርቲ በከፍተኛ ድምጽ አሸነፈ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን ወግ አጥባቂ ፓርቲ ከፍተኛ የበላይነት በማግኘት ሲያሸንፍ ተቀናቃኛቸው ሌበር ፓርቲ ደግሞ ቀደም ሲል አሸንፎባቸው በነበሩ ቦታዎች ላይ ሽንፈት ገጥሞታል።
ዩናይትድ ኪንግደም ውስጥ በተካሄደው ጠቅላላ ምርጫ ወግ አጥባቂዎች የብዙኀን መቀመጫን በማግኘት አሸነፉ። ገና ውጤታቸው ያልታወቁ የምርጫ አካባቢዎች እያሉ ነው 326 መቀመጫዎችን በማግኘት የሚያስፈልጋቸውን የበላይነት አግኝተዋል።
ቢቢሲ አንደተነበየው ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን 74 የሚሆኑ መቀመጫዎችን ጨምረው በጠቅላይ ሚኒስትርነት መንበሩ ላይ ይቆያሉ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉት ፓርቲያቸው ያገኘው የበላይነት "ዩናይትድ ኪንግደም ከአውሮፓ ኅብረት ለመውጣት የጀመረችውን ሂደት በቀጣዩ ወር ለመቋጨት ውክልና እንደሚሰጣቸው አመልክተዋል።
የጠቅላይ ሚኒስትሩ ተቀናቃኝ የሆኑት የሌበር ፓርቲው ጄሬሚ ኮርቢን ከውጤቱ በኋላ እንዳሉት "ሌበር አሳዛኝ ምሽት አሳልፏል" በማለት በቀጣይ ምርጫ ላይ እንደማይወዳደሩ ገልጸዋል።
ሌበር ፓርቲ በምርጫው ከሦስት ዓመታት በፊት የተካሄደውን ከአውሮፓ ኅብረት የመውጣት ሕዝበ ውሳኔን የደገፉት ሰሜናዊ፣ መካከላኛው የአገሪቱ ክፍል እንዲሁም የዌልስ አካባቢዎች የነበሩትን መቀመጫዎች አጥቷል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን በተወዳደሩበት የምዕራብ ለንደን አካባቢ በከፍተኛ ድምጽ ከተመረጡ በኋላ "ውጤቱ ከአውሮፓ ኅብረት ለመውጣት የተጀመረው ሂደት እንዲጠናቀቅ ከፍ ያለ አዲስ ጉልበት የሚሰጥ ነው" ብለዋል።
ተፉካካሪ የሆኑት ጄሬሚ ኮርቢንም በምርጫው የነበራቸውን መቀመጫ ማስጠበቃቸው ከታወቀ በኋላ እንደተናገሩት ፓርቲያቸው "ተስፋን የሰነቀ የምርጫ ማኒፌስቶ ብናቀርብም ከአውሮፓ ኅብረት የመውጣቱ ውዝግብ በመካረሩ ሳቢያ መደበኛው ፖለቲካዊ ፉክክር እንዲዘነጋ አድርጓል" ሲሉ ተደምጠዋል።
እስካሁን ከዚህ ምርጫ በተገኘው ውጤት መሰረት ሌበር ፓርቲ ቀደም ሲል በነበረው ምርጫ አግኝቶት ከነበረው ድምጽ 8 በመቶ የቀነሰ ሲሆን ተቀናቃኛቸው የወግ አጥባቂ ፓርቲው ግን ከአንድ በመቶ ትንሽ ከፍ ያለ ጭማሪ ድምጽ አግኝቷል። ነገር ግን ሌሎች ትናንሽ ፓርቲዎች የተሻለ ድምጽ ለማግኘት እንደተቻሉ ተዘግቧል።












