"ኢትዮጵያ ኢንተርኔት ማቋረጧን ማቆም አለባት" የተመድ ከፍተኛ ባለሙያ

ዴቪድ ኬይ በተባበሩት መንግሥታት የንግግር ነጻነት ልዩ ፀሐፊ

የፎቶው ባለመብት, RONALDO SCHEMIDT

አንድ የተባበሩት መንግሥታት ከፍተኛ የንግግር ነጻነት ባለሙያ ኢትዮጵያ ያለ ሕጋዊ መሠረት ኢንተርኔት ማቋረጧን ማቆም ይኖርባታል ሲሉ ተናገሩ። አክለውም ረቂቅ የጥላቻ ንግግር ሕጉ የመናገር ነፃነትን እንዳይገድብ ዳግመኛ ልታጤናው ይገባል ብለዋል።

ዴቪድ ኬይ በተባበሩት መንግሥታት የንግግር ነጻነት ከፍተኛ ባለሙያ ሲሆኑ ከሮይተርስ ጋር በነበራቸው ቃለምልልስ ወቅት በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለውን ለውጥ አድንቀው፣ ለውጡን ያደናቅፋል ያሏቸውን ዘርዝረዋል።

እርሳቸው እንደሚሉት ምንም እንኳ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ ሀሳብን በነጻነት መግለጽ የሚያበረታታ እርምጃ ቢወስዱም ኢትዮጵያ በዚህ ዓመት ብቻ ኢንተርኔትን በተደጋጋሚ አቋርጣለች ብለዋል።

"መንግሥት አሁንም ኢንተርኔትን መዝጋት እንደመሳሪያ እየተጠቀመ ይገኛል። እኔ ግን መንግሥት ይህንን እንዳያደርግ አጥብቄ እመክራለሁ" ማለታቸውን ሮይተርስ አስነብቧል።

ሚስተር ኬይ በአስር ዓመታት ውስጥ ኢትዮጵያን የጎበኙ የመጀመሪያው የተባበሩት መንግሥታት የንግግር ነጻነት ባለሙያ መሆናቸውም ተገልጿል።

እኚህ ባለሙያ ኢትዮጵያ የመናገርን ነጻነት በማክበር ረገድ ረዥም ርቀት ሄዳለች ሲሉ ተናግረው "ቢሆንም ግን ይህ በርካታ የሕግና የፖሊሲ ድጋፎችን የሚፈልግ ረዥም ዓመት የሚፈጅ ሂደት ነው" በማለት ቀጣይነት ያለው የሕዝቦች ተሳትፎና የሰብዓዊ መብት ምልከታ እንደሚያስፈልገው ተናግረዋል።

ኬይ አክለውም እየተረቀቀ ያለው የጥላቻ ንግግር ሕግ የለውጡን ሂደት እንዳያደናቅፈው ያላቸውን ስጋት አስቀምጠዋል።

ኬይ የጥላቻ ንግግርንና ሐሰተኛ ዜናዎችን ለመገደብ የሚደረገውን ጥረት አድንቀው፣ የጥላቻ ሕግ ረቂቁ ሐሳብን በነጻነት የመግለጽ መብትን እንዳይገድብ ስጋት አለኝ ብለዋል።

የሚኒስትሮች ምክር ቤት የጥላቻ ሕጉን ረቂቅ አጽድቆ ወደ ተወካዮች ምክር ቤት የመራው በዚህ ወር ነበር። የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትም ወደ የሚመለከተው ቋሚ ኮሚቴ መምራቱ ይታወሳል።

ኬይ ከዚህ ቀደም የተነሳውን የጸረ ሽብር ሕጉን በእንዲህ ዓይነት አፋኝ ሕግ ለመተካት መሞከር " በቀጣይ ሂደቶች ላይ የሕዝብ አመኔታን የሚሸረሽር" ነው ሲሉ ገልጸውታል።

ዴቪድ ኬይ ሃሳብን በነፃ መግለፅ መብትን በተመለከተ በአዲስ አበባ መግለጫ መስጠታቸው ይታወሳል።