የቀድሞ የአውስትራሊያ ጠቅላይ ሚኒስትር ልጅ መደፈሯን እንዳትናገር አባቷ እንደተጫኗት አሳወቀች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የቀድሞ የአውስትራሊያ ጠቅላይ ሚኒስትር ቦብ ሃውኬ ልጅ እንደ ጎርጎሳውያኑ አቆጣጠር 1980ዎቹ ላይ ብትደፈርም የፖለቲካ ህይወታቸውን እንዳትጎዳ በሚል በምስጢርነት እንድትይዘው መገደዷን ከሰሞኑ ይፋ አድርጋለች።
ሮዝሊን ዲለን ውንጀላዋን ያቀረበችው ፍርድ ቤት መሆኑን የአውስትራሊያ ሚዲያ ዘ ኒው ደይሊ ዘግቧል።
ደፋሪዋ ሌበር ፓርቲን ወክሎ የፓርላማ አባል የነበረው ቢል ላንደርዩ መሆኑንም ተናግራለች። አባቷም ሆነ ፖለቲከኛው ቢል ላንደርዩ በህይወት የሉም።
የ59 አመቷ ሮዝሊን በአባቷ ንብረት ላይ የአራት ሚሊዮን ዶላር ይገባኛል ጥያቄም አንስታለች። በሰጠችው ምስክርነት ፖለቲከኛው የደፈራት ቢሮው ውስጥ ትሰራ በነበረበት ወቅት ነው።
ሌሎች ሚዲያዎች እንደዘገቡት በተለያዩ ሶስት ጊዜያት መደፈሯን ነው።
በሶስተኛው ጊዜ መደፈሯን ለአባቷ የተናገረች ሲሆን ለፖሊስ ልትከስ መሆኗን ብታሳውቀውም በወቅቱ የአባቷ ምላሽ " ወደ ፖሊስ መሄድ አትችይም። በአሁኑ ሰዓት ውዝግብ ውስጥ መግባት አልችልም። የሌበር ፓርቲን አመራር ለመቆጣጠር የስልጣን ፍትጊያዎች አሉ" እንዳላት የፍርድ ቤት መረጃዎች ያሳያሉ።
እህቷም ሱ ፒተርስ ሃውክ ለኒውደይሊ እንደተናገረችው መደፈሯን ታውቅ እንደነበር ነው።
"በወቅቱ ለተለያዩ ሰዎች ተናግራ ነበር። አንዳንድ ሰዎች ድጋፍ ሰጥተዋታል፤ ነገር ግን የትኛውንም የፍትህ ስርዓት ያሳተፈ አልነበረም" በማለት ቃሏን ሰጥታለች።
ሌሎች የቤተሰቡ አካላት ምንም ከማለት ተቆጥበዋል።
ቢል ላንደርዩ በፓርላማ አባልነት እንደ ጎርጎሳውያኑ ከ 1976-1992 አገልግሏል። ከአባቷ ጠቅላይ ሚኒስትር ቦብ ሃውኬም ጋር ጥሩ ግንኙነት ነበራቸው ተብሏል።
በአውስትራሊያ ፖለቲካ ትልቅ ስፍራ የነበራቸውም ቦብ ሃውኬም አራት ጊዜ ምርጫዎችን ማሸነፍ ችለዋል ። በሃገሪቱም የኢኮኖሚ እንዲሁም የማህበረሰቡ ለውጦች ላይ ትልቅ ስፍራ ተጫውቷል ይባላል።












