የማሳይ ማህበረሰብን ሽርጥ ብቻ የሚለብሰው ስዊድናዊ ታዳጊ

በታንዛኒያ የሚኖሩ የማሳይ ጎሳዎችን ባህል የወረሰው የ11 ዓመቱ ስዊድናዊ ከማህበረሰቡ ደስታንና ትችትን አስተናግዷል።
ኦስካር ማግዋያ ወደ ታንዛኒያ ያቀናው የ4 ዓመት ሕፃን ሳለ ከእናቱ ሱዛን ማግዋያ ጋር ነበር።
እናቱ ሱዛን የጎዳና ልጆችን የሚደግፍ ግብረ ሰናይ ድርጅት ውስጥ ይሠሩ ነበር።
ታዲያ በዚህ አጋጣሚ የማሳይ የደህንነት ጠባቂያቸውን ዳውዲ ማግዋያ ጋር ይተዋወቃሉ። ትውውቁ ወደ ፍቅር አድጎ ትዳር መስርተው ሴት ልጅ ወለዱ። ኦስካርም እህት አገኘ።
ኦስካር የማሳይን ቋንቋ፣ ኪስዋሂሊ እንዲሁም የአፍ መፍቻ ቋንቋውን ስዊድንኛ አቀላጥፎ ይናገራል። የማሳይ ባህላዊ ልብስ ከሆነው ሽርጥ ውጭም ሌላ ልብስ አይለብስም።
"እዚህ አየሩ በጣም ይሞቃል፤ በመሆኑም የማሳይ ልብስ በቂ አየር ለማግኘት ያስችላል" ይላል ኦስካር የልብሱን ምቾት ሲገልፅ።
ኦስካር እንደሚለው ብዙ ጓደኞች ቢኖሩትም አንዳንድ የማሳይ ማህበረሰቦች ግን በሁኔታው ይተቹታል።

"ወደ አውሮፓ መመለስ እንዳለብኝ ይነግሩኛል፤ ባህሌ ስላልሆነ የማደርገው ነገር 'አብሮ አይሄድም' ይሉኛል። እኔ ግን ይሄ የምወደው ነገር ነው፤ መመለስ አልችልም፤ አንዳንድ ሰዎች ስለሚወዱኝ ደስተኛ ነኝ" ይላል።
ኦስካር ወደፊት አርሶ አደር መሆን ይፈልጋል፤ ሲያድግ በታንዛኒያ መንደር ብዙ ከብቶች እንዲኖሩትም ይመኛል።
በአሁኑ ሰዓት በታንዛኒያዋ ንግድ ከተማ ዳር ኤ ሰላም አካል በሆነችው ኪጋምቦን ከቤተሰቦቹ ጋር ይኖራል።
ከሰሜን ታንዛኒያና እና ደቡባዊ ኬንያ የማሳይ ጎሳዎች ሲመጡ እንደ የደህንነት ጥበቃ ለመስጠት ወደ ዳር ኤ ሰላም መሄዳቸው የተለመደ ነው።
"የማሳይ ሰዎችን ጀግና ሆነው ነው ያገኘኋቸው፤ እኔም በጣም ጀግና ነኝ፤ አንድ ቀን ትንሽ ሳለሁ እባብ ገድያለሁ" ይላል ኦስካር።














