የብሪታኒያው ጠቅላይ ሚኒስትርን ውሳኔ ፍርድ ቤት ውድቅ አደረገው

የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ፕሬዝዳንት ላዲ ሃሌ
የምስሉ መግለጫ, የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ፕሬዝዳንት ላዲ ሃሌ

ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን የሃገራቸውን ፓርላማ ለማገድ የደረሱትን ውሳኔ ሕገ ወጥና ተቀባይነት የሌለው ነው ሲል የብሪታኒያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ውድቅ አደረገው።

የብሪታኒያው ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ ፓርላማውን ለአምስት ሳምንታት ለማገድ ያሳለፉትን ውሳኔ፣ በጥቅምት ወር መጨረሻ ላይ ሃገሪቱ ከአውሮፓ ኅብረት የመውጫ ጊዜዋ በተቃረበበት ጊዜ በመሆኑና የፓርላማው አባላት ሥራቸውን እንዳያከናውኑ ስለሚያደርጋቸው ትክክል አይደለም ሲል ፍርድ ቤት ውሳኔ ሰጠ።

የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ፕሬዝዳንት ላዲ ሃሌ "ውሳኔው በዴሞክራሲ መሰረታዊያን ላይ ያለው ተጽዕኖ እጅግ ከፍተኛ ነው" ብለዋል።

የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽህፈት ቤት የፍርድ ቤቱን ውሳኔ በተመለከተ በሰጠው ምላሽ ውሳኔውን እየመረመሩት መሆኑን በመግለጽ ተቃውሞ ከማሰማት ተቆጥቧል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ጆንሰን የፓርላማው ጉባኤ ሳይካሄድ እንዲቆይ የፈለጉት ንግሥቲቱ ከሚያደርጉት ንግግር ቀድመው የመንግሥታቸውን ዋና ዋና አዳዲስ ፖሊሲዎችን ለማዘጋጀት እንዲያስችላቸው በማሰብ ነው።

ነገር ግን የጠቅላይ ሚኒስትሩን እርምጃ የሚተቹ ሰዎች እንደሚሉት ውሳኔያቸው የፓርላማው አባላት ብሪታኒያ ከአውሮፓ ኅብረት እንድትወጣ የሚያዘጋጁትን ዕቅድ በቅርበት እንዳይከታተሉባቸው ለማድረግ ነው ይላሉ።

በርካታ ቁጥር ያላቸው የፓርላማ አባላት ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን ስልጣናቸውን በፈቃዳቸው እንዲለቁና ፓርላማውም በአስቸኳይ ወደ ሥራው እንዲመለስ ጠይቀዋል።

የሌበር ፓርቲ መሪ የሆኑት ጄሬሚ ኮርቢን እንዳሉት የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ውሳኔ ቦሪስ ጆንሰንን "ለዴሞክራሲ ያላቸውን ንቀት" ያሳያል በማለት "ጠቅላይ ሚኒስትሩ የያዙትን አቋም መለስ ብለው እንዲፈትሹ እጠይቃለሁ" ሲሉ አክለዋል።

የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ፕሬዝዳንት ላዲ ሃሌ የውሳኔያቸውን መደምደሚያ ሲሰጡ "ውሳኔው በዴሞክራሲያችን ላይ ያለው ውጤት እጅግ ከፍ ያለ ነው" ብለዋል።

አክለውም "ንግሥቲቱ ፓርላማው ከሥራ ውጪ እንዲሆን ለመምከር የተደረሰበት ውሳኔ ከሕግ ውጪ ሲሆን ውሳኔውም ፓርላማው ሕገ መንግሥታዊውን ተግባሩን ካለምንም አሳማኝ ምክንያት እንዳያከናውን ሊያደርገው ይችላል" ብለዋል።

የፍርድ ቤቱ ፕሬዝዳንት እንዳሉት በውሳኔው ላይ የተሳተፉት 11 ዳኞች በሙሉ ድምጽ፣ ፓርላማው ከሥራው መታገድ እንዳልነበረበትና ውሳኔው ተቀባይነት የሌለውና ተግባራዊ መሆን እንደሌለበት መወሰናቸውን ተናግረዋል።

ቀጣይ እርምጃን በተመለከተ የሁለቱ ምክር ቤቶች አፈ ጉባኤዎች በጋራ የሚወስኑት ይሆናል።

የፓርላማው አፈ ጉባኤ የሆኑት ጆን ቤርኮው የጠቅላይ ፍርድ ቤቱን ውሳኔ በደስታ የተቀበሉት ሲሆን "ፓርላማው ጊዜ ሳያጠፋ ወደ ሥራው መመለስ አለበት" በማለት ከጉዳዩ አንገብጋቢነት አንጻር የፓርቲ መሪዎችን እንደሚያማክሩም ተናግረዋል።