የአማዞን እሳት፡ ብራዚል ከቡድን 7 የተበረከተላትን የገንዘብ ድጋፍ ውድቅ ልታደርግ ነው

የብራዚል መንግሥት የአማዞንን እሳት ለማጥፋት ከቡድን 7 ሃገራት የተደረገለትን የገንዘብ ድጋፍ ውድቅ ሊያደርግ መሆኑን አስታወቀ።
ሰኞ እለት የተጠናቀቀውን የቡድን ሰባቱን ጉባዔ የመሩት የፈረንሳዩ ፕሬዚደንት ኢማኑኤል ማክሮን የአማዞን ጫካን እየለበለበ የሚገኘውን እሳት ለማጥፋት 22 ሚሊየን ዶላር ለመልቀቅ ስምምነት ላይ መድረሳቸውን ይፋ አድርገዋል።
ይሁን እንጂ የብራዚል መንግሥት ገንዘቡን እንደማይቀበል ገልጿል። ምክንያቱ ይህ ነው ተብሎ አልተገለፀም። ነገር ግን የብራዚል ፕሬዚደንት ጀር ቦልሶናሮ ፈረንሳይ ብራዚልን እንደቅኝ ግዛቷ ቆጥራለች በሚል ወቀሳ ሰንዝረዋል።
የብራዚል መከላከያ ሚንስትር በበኩላቸው የአማዞን እሳት ከቁጥጥር ውጭ አልሆነም ብለዋል።
የቡድን 7 ሃገራት ያደረጉት ድጋፍ ላይ አስተያየታቸውን የሰጡት የፕሬዚደንት ቦልሶናሮስ አማካሪ ኦንይክስ ሎርንዞኒ ለግሎብ የዜና ድረ ገፅ እንዳሉት "ለድጋፉ እናመሰግናለን፤ ነገርግን ይህ ሃብት አውሮፓን በደን ለማልማት ቢውል ጥሩ ሊሆን ይችላል" ሲሉ ወርፈዋል።
ሎሮንዞኒ " ማክሮን የዓለም ቅርስ በሆነውና ቀድሞ የተተነበየውን የቤተ ክርስትያን ቃጠሎ መከላከል ሳይችሉ፤ አሁን ደግሞ ለእኛ አገር ትምህርት ሊሰጡ?" በማለት ባለፈው ሚያዚያ ወር የቃጠሎ አደጋ የደረሰበትን ኖትረ ዳም ካቴድራል በመጥቀስ ትችታቸውን በምሳሌ አስደግፈዋል።
"ብራዚል፤ አገር በቀል ጫካዎች እንዴት መጠበቅ እንዳለባት ማንኛውንም ሃገር ማስተማር ትችላለች" ሲሉም አክለዋል።
የቡድን 7 ሀገራት ፤ ካናዳ ፣ ፈረንሳይ ፣ ጀርመን፣ ጣሊያን፣ ጃፓን፣ እንግሊዝ እና አሜሪካ ለአማዞን ጫካ እሳት አደጋ መከላከል 22 ሚሊየን ዶላር ድጋፍ ለማድረግ መስማማታቸውን ያስታወቁት ባሳለፍነው ሰኞ ነበር።
ስብሰባው የመሩት ፕሬዚደንት ማክሮን ገንዘቡ በቅድሚያ ለእሳት አጥፊ አውሮፕላኖች ክፍያ ይውላል ብለዋል። ከዚህም በተጨማሪ ፈረንሳይ ወታደራዊ እገዛ እንደምታደርግ ገልፀዋል።
በታይታኒክ ፊልም ብዙዎች የሚያውቁት ተዋናይ ሊዮናርዶ ዲካፕሪዎም በበኩሉ የ5 ሚሊየን ዶላር ድጋፍ ማድረጉን አስታውቋል።
ብራዚል እሳቱን ለማጥፋት 44 ሺህ ወታደሮች እንዳሰማራች ባለፈው አርብ ማስታወቋ ይታወሳል።
በብራዚል የበጋውን ወራት ተከትሎ የእሳት አደጋ መቀስቀሱ የተለመደ ቢሆንም የሳተላይት መረጃዎች እንደሚያመለክቱት በዚህ ዓመት 85 በመቶ መጨመሩ ተገልጿል።
















