"የብራዚሉ ፕሬዚዳንት ስለ ሚስቴ የተናገሩት ስድና መረን የለቀቀ ነው" ማክሮን

የብራዚሉ ርዕሰብሔር 37 ዓመት ከሚሆናቸው ባለቤታቸው ሜሼል ጋር

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የብራዚሉ ፕሬዚዳንት ቦልሶናሮ ባለቤት የሆኑት ሜሼል ቦልሶናሮ ዕድሜያቸው 37 ነው።

የፈረንሳዩ ኢማኑኤል ማክሮን የብራዚሉን ፕሬዚዳንት ቦልሶናሮን ክፉኛ ኮንነዋል። "ክብረቢስና ለብራዚል ሕዝብ የማይመጥን" ብለዋቸዋል።

ማክሮን ይህን አስተያየት የሰጡት በዕድሜ በእጅጉ የሚበልጧቸውን የ66 ዓመቷን የገዛ ባለቤታቸውን የብራዚሉ ፕሬዝዳንት መሳለቂያ ስላደረጉባቸው ነው።

የፈረንሳይዋ ቀዳማዊት እመቤት ብሪዢት ማክሮን የ66 ዓመት ወይዘሮ ሲሆኑ የብራዚሉ ጄይር ቦልሶናሮ ባለቤት ሚሼል ቦልሶናሮ ግን ገና 37 ዓመታቸው ነው።

ታዲያ የብራዚሉ ፕሬዝዳንት ቀንደኛ ደጋፊ እንደሆነ የተነገረለት አንድ ግለሰብ የሁለቱን አገራት ቀዳማዊ እመቤቶች ምሥል በፌስቡክ ገጹ ላይ በማተም ያልተገባ አስተያየት ይሰጣል።

በግለሰቡ የፌስቡክ ሰሌዳ ላይ የታተመው የሁለቱ ቀዳማዊት እመቤቶች ፎቶ ዋና ዓላማ ያደረገው የሁለቱን መሪዎች ሚስቶች ቁንጅናና ዕድሜን ማፎካከር ነበር።

ከፎቶው ሥር ታዲያ "አሁን ለምን ማክሮን ቦልሶናሮን መክሰስ እንደፈለገ መቼስ ግልጽ ነው" የሚል መልእክት ታትሞበታል፤ በዚሁ ግለሰብ።

ከዚህ የፌስቡክ ገጽ ሥር ብቅ ያሉት የብራዚሉ ፕሬዚዳንት ቦልሶናሮ የጻፉት አስተያየት ነው ኢማኑኤል ማክሮንን ያበገናቸው።

"አንተ ተው እንጂ ሰውየውን አታዋርደው!" ይላል በሽሙጥ ሳቅ የታጀለውና በፖርቹጋል ቋንቋ ከቦርሶናሮ የተሰጠው የፌስቡክ አስተያየት።

ይህም ኢማኑኤል ማክሮንን በነገር ለመጎንተል ሆን ተብሎ የተደረገ መሆኑን ግምት መውሰድ ያስችላል።

የፈረንሳዩ መሪ ማክሮን 66 ዓመት ከሚሆናቸው ባለቤታቸው ብሪጂት ማክሮን ጋር

የፎቶው ባለመብት, EPA

የምስሉ መግለጫ, የፈረንሳዩ መሪ ማክሮን በእድሜ ከሚበልጧቸው የ66 ዓመቷ ባለቤታቸው ብሪዢት ማክሮን ጋር

ከዚህ ክስተት በኋላ ስለ ጉዳዩ የተጠየቁት ኢማኑኤል ማክሮን የሰነዘሩት መልእክት የብራዚሉን ፕሬዚዳንት የፌስቡክ አስተያየት"አስነዋሪና ወራዳ" እንደሆነ ደምሳሳ ትርጉም የሚሰጥ ነበር። "ይህ ፍጹም ከመስመር የወጣ ብልግና ነው" ብለዋል።

"ሰውየው ባለቤቴን የሚያዋርድ ነገር ነው የተናገረው፤ የብራዚል ሕዝብ ትልቅ ሕዝብ ነው፤ ፕሬዝዳንቱ ግን 'ክብረ ቢስ' ናቸው፤ ብራዚላዊያን ለክብራቸው የሚመጥናቸውን መሪ ያገኛሉ ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ" ብለዋል፤ የበለጸጉ አገሮች ስብሰባ በተደረገባት በፈረንሳይዋ ቢያኺትዝ፣ ሰኞ ለታ በሰጡት አጭር ጋዜጣዊ መግለጫ።

የሁለቱ መሪዎች አንድ ሁለት መባባል የጀመሩት ታዲያ ቀደም ብለው ሲሆን ይኸውም በዋናነት በብራዚል የአማዞን ጫካን ሰደድ እሳት መነሳት ተከትሎ ነበር።

ባለፈው ሳምንት ማክሮን የዓለም ብልጹግ መሪዎች ሰደድ እሳቱን ለማቆም አንድ መላ እንዲመቱ እያስተባበሩ ነበር። ይህ ተግባራቸው ታዲያ በብራዚሉ ርዕሰ ብሔር አልተወደደላቸውም።

ከበለጸጉ 7 አገራት መሪዎች ተርታ የማይገኙት ቦልሶናሮ "ማክሮን ከቅኝ ገዢ አስተሳሰብ ያልወጡ ናቸው" በሚል አሉታዊ አስተያየት ሰጥተው ነበር፣ ያን ጊዜ።

ከቀኝ ዘመም ፓርቲ የወጡት የብራዚሉ ርዕሰብሔር ወትሮም በሴቶች፥ በጥቁሮችና በሕዳጣን ማኅበረሰቦች ላይ አሉታዊ አስተያየት መስጠት የለመዱ 'ዘርጣጭ' ቢጤ እንደሆኑ ይነገርላቸዋል።

በ2014 እንደ ጎርጎሮሲያዊያኑ ለምሳሌ የግራ ዘመም ፓርቲ የምክር ቤት አባል የነበሩትን ማሪያ ዱ ሮሳሪዎን እጅግ አስደንጋጭ ቃላትን ተናግረዋቸው [ያውም ሸንጎ ተቀምጠው] ዓለም ጉድ ብሎ ነበር። ቦልሶናሮ ወይዘሮዋን በጊዜው ያሏቸው የሚከተለውን ነበር።

"ጾታዊ የወሲብ ጥቃት እፈጽምብዎ ብመኝ እንኳ፤ ለዚያ የሚመጥን ቁንጅና የለዎትም"

ሚስተር ቦልሶናሮ በሚናገሩት ነገር ሕዝብ ሲያስቆጡ ታዲያ ይህ የመጀመርያቸው አልነበረም። በ2017 እንደ ጎርጎሮሲያዊያኑ ስለራሳቸው ይህንን ብለው ነበር፤

"አምስት ልጆች አሉኝ፤ አራቱ ወንዶች ናቸው። በአምስተኛው ስንፈት ገጠመኝና ሴት ተወለደች"