ከተገለበጠ ቦቴ ላይ ነዳጅ ሲቀዱ ሕይወታቸውን ያጡ 71 ታንዛኒያውያን ተቀበሩ

በታንዛኒያው የነዳጅ ቦቴ ፍንዳታ ሕይወታቸውን ያጡ ሰዎች ግብዓተ መሬት ትናንት እሁድ ተፈጸመ።
ቅዳሜ ዕለት ከአንድ ከተገለበጠ ነዳጅ የጫነ ቦቴ ላይ ድንገት በተከሰተው ፍንዳታ ነዳጅ በጄሪካን በመቅዳት ላይ ከነበሩ ሰዎች መካከል ሕይወታቸውን ያጡት 71 ሰዎች ናቸው ቀብራቸው የተፈጸመው።
ከግብዓተ-መሬቱ በፊት በመቶዎች የሚቆጠሩ የሟች ቤተሰቦች ወደ ሆስፒታሎች በማምራት ወዳጅ ዘመዶቻቸውን እንዲለዩ ተጠይቀው ነበር። ነገር ግን በቃጠሎው ምክንያት ሟቾቹን መለየት እንዳልተቻለ ታውቋል። በዚህም ምክንያት የዘር ቅንጣት [ዲኤንኤ] ምርመራ ማከናወን ግድ ሆኗል።
የታንዛኒያው ፕሬዝደንት ጆን ማጉፉሊ ሰዎች ተበላሽተው ከቆሙ መኪናዎች ላይ ነዳጅ ለመቅዳት ሲሉ ሕይወታቸውን አደጋ ላይ መጣል የለባቸውም የሚል መልዕክት አስተላልፈዋል።
ታንዛኒያ ለሦስት ቀናት የሚዘልቅ የሃዘን ጊዜ አውጃለች።
ከታንዛኒያ ዋና ከተማ ዳር ኤስ ሳላም 200 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ሞሮጎሮ ነው አደጋው የተከሰተው።
ነዳጅ ተሸካሚ መኪናዎች ፈንድተው አደጋ ሲያደርሱ በታንዛኒያም ሆነ በሌሎች የአፍሪካ ሃገራት ይህ የመጀመሪያው አይደለም። ባለፈው ወር ናይጄሪያ ውስጥ በተከሰተ መሰል አደጋ 45 ሰዎች ተቃጥለው መሞታቸው የሚታወስ ነው።
ኒጀርም 80 ያክል ዜጎቿን ለነዳጅ ቦቴ ቃጠሎ ገብራለች።
ታንዛኒያውያን በአደጋው የሞቱ ወገኖቻቸውን ሰብሰብ ብለው ቀብረዋል። የተወሰኑት ሟች ቤተሰባቸውን በግል በመውሰድ ሲቀብሩ የተቀሩቱ ግን በመንግሥት በተዘጋጀ የጅምላ ሥነ ሥርዓት ግብዓታቸው ተፈፅሟል።













