ሰሜን ኮሪያ 'ሮኬት ለማምጠቅ በዝግጅት ላይ መሆኗን' የሚያሳይ ምስል ተገኘ

የፎቶው ባለመብት, AFP
ፒዮንግያንግ አቅራቢያ በሚገኝ የሰሜን ኮሪያ ማእከል እየተደረገ ያለን እንቅስቃሴ የሚያሳይና አገሪቱ ሮኬት ለማስወንጨፍ ወይም ሳተላይት ለማምጠቅ በዝግጅት ላይ እንዳለች የሚጠቁም የሳተላይት ምስል መገኘቱ ተገለፀ።
የተገኘው የሳተላይት ምስል ሰሜን ኮሪያ አብዛኛውን ጊዜ ባለስቲክ ሚሳይሎችና ሮኬቶችን የምትገጣጥምበት የሳኑምዶንግ ማእከል ሲሆን እዚህ ማእከል ውስጥ በርካታ እንቅስቃሴ ሲደረግ እንደነበር ከምስሉ መረዳት ተችሏል።
ይህ ዜና የተሰማው በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ የአገሪቱ ዋነኛ የሮኬት ማምጠቂያ ማእከል እንደ አዲስ መገንባቱን ተከትሎ ነው።
ባለፈው የአውሮፓውያኑ ዓመት ይህን ማእከል የማፍረስ ስራ ተጀምሮ የነበረ ሲሆን የሰሜን ኮሪያና የአሜሪካ ውይይት ሲቋረጥ ማእከሉን የማፍረስ ስራም እንዲቆም ሆኗል።
ትናንት የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ሰሜን ኮሪያ ዳግም መሳሪያ ወደ መሞከር ከገባች በእጅጉ እንደሚያዝኑ ተናግረው ነበር።
"ከንግግራችን ውጭ የሆነ ነገር ቢያደርግ[ኪም ጆንግ ኡን] በመጥፎ መልኩ እደነቃለሁ። ግን ምን እንደሚሆን እናያለን" ብለዋል ትራምፕ።
ተንታኞች እንደሚሉት በአሁኑ ወቅት ሰሜን ኮሪያ ሚሳይል ከመሞከር ይልቅ ሳተላይት ማምጠቅን ትመርጣለች።
ሳተላይት ምስሉ ሳኑምዶንግ ማእከል አካባቢ ትልልቅ ተሽከርካሪዎች ሲንቀሳቀሱ የሚያሳይ ሲሆን በዚህም ሰሜን ኮሪያ ሮኬት ወደ ምታስወነጭፍበት አካባቢ እቃዎችን እያጓጓዘች እንደሆነ ታምኗል።
የሳተላይት ምስሉን ያተመው የአሜሪካው ሬድዮ ኔትወርክ ኤንፒአር ነው።












