ትራምፕ ለግንቡ ገንዘብ ለማግኘት 'ብሔራዊ የአደጋ ጊዜ አዋጅ' ሊያውጁ ነው

ዶናልድ ትራምፕ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራም አሜሪካ ከሜክሲኮ ጋር በሚያዋስናት ድንበር ላይ ለመገንባት ላሰቡት ግንብ ገንዘብ ለማግኘት በማሰብ 'ብሔራዊ የአደጋ ጊዜ አዋጅ' ሊውጁ እንደሆነ ዋይት ሃውስ አስታወቀ።

በአሜሪካ ዜጎች ላይ የተደቀኑ የጤና እና የደህንነት ስጋቶችን በመደበኛ ሕጎች መግታት ሳይቻል ሲቀር ፕሬዚዳንቱ ብሔራዊ የአደጋ ጊዜ አዋጅ ወይም 'ናሽናል ኢሜርጀንሲ' የማወጅ ስልጣን አላቸው።

በዚህም መሰረት የአሜሪካ ጦር በጀትን ለግንቡ መስሪያ ሊጠቀሙት እንደሚችሉ የዋይት ሃውስ መግለጫ አስታውቋል።

ፕሬዚዳንት ትራምፕ ይህን የሚወስኑት ከዲሞክራቶች ፍላጎት እና ውሳኔ በተጸረረ መልኩ ነው።

በርካታ ዲሞክራቶች ትራምፕ ''ስልጣንን ያለ አግባብ እየተጠቀሙ ነው'' ሲሉ አምርረው እየወቀሷቸው ነው።

ፕሬዚደንት ትራምፕ በምርጫ ቅስቀሳቸው ወቅት ግንቡን መገንባት ዋነኛ እቅዳቸው እንደሆነ አጽንኦት ሰጥተው ሲቀሰቅሱ ነበር። ይሁን እንጂ እስካሁን ግንቡን የሚያገነቡበት በጀት ማግኘት ቀላል አልሆነላቸውም።

ትናንት ኮንግረሱ ትራምፕ ለግንቡ ግንባታ የጠየቁትን ገንዘብ የሚከለክል ረቂቅ አዋጅ አሳልፏል። ይሁን እንጂ ይህ ረቂቅ አዋጅ ሕግ ሆኖ የሚጸድቀው የትራምፕ ፊርማ ሲኖርበት ብቻ ነው።

''ፕሬዝዳንቱ አሁንም ቢሆን ግንቡን ለመገንባት ቃላቸውን እየጠበቁ ነው፤ አዋሳኝ ድንበሩ ይጠበቃል፤ ትልቋ ሀገራችን ደህንነቷ የተጠበቀ ይሆናል'' ብለዋል የዋይት ሃውስ ፕሬስ ሴክረተሪ ሳራ ሳንድረስ።

ሳራ ሳንድረስ ጨምረውም ፕሬዝዳንቱ በድንበሩ አማካኝነት የሚከሰተውን ብሄራዊ የደህንነት ስጋት እና ሰብአዊ ቀውስ ለማስቆም የተለያዩ እርምጃዎችን ይወስዳሉ፤ ከእነዚህም መካከል ብሔራዊ የአደጋ ጊዜ አዋጅ ማወጅ ይገኝበታል ብለዋል።

ኮንግረሱ ትናንት ለድንበር ደህንነት ያጸደቀው ገንዘብ 1.3 ቢሊዮን ዶላር ሲሆን፤ ትራምፕ ለግንቡ ግንባታ 5.7 ቢሊዮን ዶላር ጠይቀዋል።

በአሜሪካ እና ሜክሲኮ ድንበር ላይ ይገነባል ተብሎ የነበረው የኮንክሪት ግንብ መነጋገሪያ ሆኖ መቆየቱ ይታወሳል።

በቅርቡ ከሥራቸው የተሰናበቱት የፕሬዚዳንቱ አማካሪ ጆን ኬሊይ የኮንክሪት ግንብ ሃሳብ ውድቅ የተደረገው በትራምፕ የመጀመሪያዎቹ የፕሬዚዳንትነት ወራቶች ነው ሲሉ ተናግረው ነበር።

ዶናልድ ትራምፕ ግን ''Wall'' ወይም ግንብ የሚለውን ቃል በትዊተር ገጻቸው ላይ በርካታ ጊዜያት ተጠቅመውታል።