የአፍሪካን የእግርኳስ ሙስና ቅሌት ያጋለጠው ጋናዊው ጋዜጠኛ አህመድ ሁሴን ተገደለ

የአፍሪካን የእግርኳስ የሙስና ቅሌት ያጋለጠው ጋናዊው የምርምር ጋዜጠኛ በጥይት ተገደለ።
ዘገባውን ተከትሎም አንድ ፖለቲከኛ ጋዜጠኛው ላደረሰው ጥፋት እንዲቀጣ ጥሪ ማድረጋቸውን ተከትሎ ዛሬ ወደቤቱ እየነዳ በሚሄድበት ወቅት ተተኩሶበት ሞቷል።
በሃገሪቱ ሚዲያ ዘገባ መሰረት ማንነታቸው ያልታወቁ ግለሰቦች በሞተርሳይክል ተከትለው አህመድ ሁሴን ሱዋሌን ሶስት ጊዜ ተኩሰው መትተውታል።
ታይገር አይ (የነብር አይን) የሚባል የምርመራ ድርጅት አባል የነበረው ጋዜጠኛ የአፍሪካ የሙስና ቅሌት ያለበትን ሁኔታ አጋልጧል።
ይህ በስውር የተሰራው የምርመራ ዘገባ የእግር ኳስ ሃላፊዎች የገንዘብ ስጦታ ሲቀበሉ የሚያሳይ ሲሆን፤ ዘገባውም የቀድሞው የጋና እግር ኳስ ማህበር ፕሬዚዳንት የህይወት ጊዜ እገዳ እንዲጣልባቸው አድርጓል።
ቢቢሲ አፍሪካ የተባለው ፕሮግራም የሙስና ቅሌቱን ጥናታዊ ዘገባ የሰራበት ሲሆን፤ ቢቢሲ የማሳየቱን ፍቃድ ያገኘው ታይገር አይ የተባለውን ድርጅት የሚመራው አወዛጋቢው ጋዜጠኛ አናስ አረማየው መፍቀዱን ተከትሎ ነው።
ቢቢሲ የጥናት ፊልሙን ካሳየ በኋላ የጋና ፓርላማ አባል የሆኑት ኬኔዲ አግያቦንግ በአንድ የጋና ዜና ማሰራጫ ድረገፅ ላይ በተለጠፈ ቪዲዮ ባስተላለፉት መልዕክት የጋዜጠኛውን ፎቶ በማሳየት " በሚገኝበት ቦታ ደብድቡት፤ የሆነውን ይሁን እኔ እከፍላለሁ" ብለዋል።
ጋዜጠኛው መገደሉን ተከትሎ አናስ በድፍረት በማህበራዊ ሚዲያ መልዕክቱ አባላቸው መገደሉ መቼም ቢሆን ዝም እንደማያሰኛቸው ተናግሯል።
ትናንትና ሌሊት አክራ ውስጥ በሚገኝ ማዲና በሚባል ሰፈር አህመድ ሁሴን ሱዋሌ በደረቱ አካባቢ ሁለት ጊዜ በጥይት፣ አንገቱ ላይ ደግሞ አንድ ጊዜ እንደተመታ ተዘግቧል።
በፖሊስ ሆስፒታል ወደሚገኝ መመርመሪያ አስከሬኑ የተላከ ሲሆን በቅርቡም የቀብር ስነ ስርአቱ ይፈፀማል።
የምርምራ ጋዜጠኛው አህመድ በተለያዩ ዘገባዎች ላይ ከቢቢሲ ጋር በመጣመር ፕሮግራም የሰራ ሲሆን ከነዚህም ውስጥ በማላዊ በሚደረጉ አንዳንድ ስርአቶች ላይ የሰው አካል እንዴት እንደሚሸጥ የሚያሳየው ዘገባ ይገኝበታል።
በጋና ጋዜጠኞች ላይ የሚደርስ ጥቃት ያልተለመደ ሲሆን፤ በአለም አቀፉ የጋዜጠኞች ፌዴሬሽን መረጃ መሰረት ከአራት አመት በፊት አንድ ጋዜጠኛ ተገድሏል።
ከሁለት አመት በፊት የወጣው መረጃ እንደሚያሳየው ደግሞ በአጠቃላይ በአፍሪካ ውስጥ ስምንት ጋዜጠኞች ተገድለዋል።












