60 በመቶው የላይቤሪያ የኤሌክትሪክ ኃይል ተሰርቋል

የመዲናዋ ሞኖሮቪያ አብዛኛው ክፍል የኤሌክትሪክ አገለግሎት አያገኙም

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የመዲናዋ ሞኖሮቪያ አብዛኛው ክፍል የኤሌክትሪክ አገለግሎት አያገኙም

ላይቤሪያ በዓመት ከምታመነጨው የኤሌክትሪክ ኃይል 60 በመቶው ሕዝቡ በህገወጥ መንገድ ለመኖሪያ ቤትና ለንግድ ተቋማት ጠልፎ በሚያስገባው እንደሚሰረቅ ባለቤትነቱ የመንግስት የሆነ የኃይል ተቋም አስታውቋል።

የላይቤሪያ የኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን እንዳለው አገሪቷ በዚህ ህገወጥ ድርጊት በዓመት ወደ 35 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር (980 ሚሊዮን ብር ገደማ) ታጣለች።

ስርቆቱ የኃይል አቅርቦቱን ለማሳደግ እየተካሄደው ላለው ስራ ተግዳሮት እንደሆነባቸው ባለስልጣነቱ ጨምረው ተናግረዋል።

ላይቤሪያ ከአውሮፓውያኑ 1989 እስከ 2003 በዘለቀው የእርስ በርስ ጦርነት ሳቢያ ድምጥማጡ የጠፋውን የኃይል ተቋም እንደገና ለመገንባት እየታተረች ትገኛለች።

ለዚህም ይረዳ ዘንድ አሜሪካ የምዕራብ አፍሪካ አገራትን እርስ በርስ ለማስተሳሰር የገንዘብና የሙያ ድጋፍ እያደረገች ትገኛለች።

በቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዚደንት ባራክ ኦባማ በተቋቋመው 'አፍሪካ የኃይል ኢኒሸቲቭ' አማካኝነት ከሰሃራ በታች ባሉ አገራት 50 ሚሊየን የሚሆኑ ሰዎች የኤሌክትሪክ አገልግሎት እንዲያገኙ ለማስቻል ታልሞ ነው ድጋፉ እየተደረገ የሚገኘው።

ይሁን እንጂ እስካሁን 12 በመቶ የሚሆኑ ላይቤሪያውያን እንዲሁም የዋና መዲናዋ- ሞንሮቪያ ነዋሪዎች የኤሌክትሪክ አገልግሎት የሚያገኙት20 በመቶ የሚሆኑት ብቻ ናቸው። ይህም አገሪቷ በቂ የኤሌክትሪክ ኃይል ከማያገኙ አገራት ተርታ እንድትመደብ ምክንያት ሆኗል።

የአገሪቱ መንግስት ከ12 ዓመታት በኋላ ከአንድ ሚሊየን በላይ የሞኖሮቪያ ህዝብ 70 በመቶ የሚሆኑት የኤሌክትሪክ ኃይል እንዲያገኙ ትኩረት አድርጎ እየሰራ ይገኛል።

ነዋሪዎች የኤሌክሪክ ኃል ለምን ይሰርቃሉ?

የኃይል ስርቆት በኑሮ ደረጃ የማይወሰን፤ ከፍተኛ ገቢ ባላቸውም ሆነ በድህነት ደረጃ የሚገኙ ሰዎች የሚፈፅሙት ህገ-ወጥ ተግባር ነው። ይህንን ድርጊት የሚፈፅሙት የሚጠበቅባቸውን የአገልግሎት ክፍያ ላለመክፍል ብቻ አይደለም። የኃይል አቅርቦቱ ፍላጎታቸውን ማሟላት ስለማይችሉ ጭምር ነው።

በዚህም ምክንያት ሰዎች በቤታቸው አሊያም በሱቃቸው የሚያልፍ የኤሌክትሪክ ማስተላለፊያ ገመድ ላይ የራሳቸውን ገመድ በመቀጠል የኤሌክትሪክ ኃይል ለማግኘት ይሞክራሉ።

ይህንንም ችግር ለመፍታት የኤሌክትሪክ ኃይል የሚቆጣጠር አንድ ግብረ ኃይል መቋቋም እንዳለበት ተጠቁሟል።

እነዚህ በአካባቢው እንዲሰማሩ የታሰቡት ግብረ ኃይሎች በህገ ወጥ መንገድ አገልግሎቱን የሚያገኙ ሰዎችን የቀጠሉትን መስመር ይቆርጣሉ።

ከዚህም በተጨማሪ ሰዎች ይህንን ህገ ወጥ ተግባር ለመንግስት ሪፖርት ለማድረግ ነፃ የስልክ አገልግሎት መዘጋጀት አለበት ተብሏል።

በአገሪቱ በነበረው የርስ በርስ ጦርነት የወደመውን 'ማውንት ኮፊ' በውሃ የሚመነጨው የኤሌክትሪክ ኃይልን ከበጎ አድራጊ ድርጅቶች ጋር በመሆን እንደገና መገንባት እንደሚያስፈልግ ተገልጿል።

መንግስት በአገሪቱ ያለውን የኃይል አቅርቦት ካላስተካከለ አሁንም ህገ ወጥ ተግባሩ መቀጠሉ እንደማይቀር ተነግሯል።

አንዳንድ ሰዎች መፍትሔው ተቋማቱን በግለሰብ እንዲተዳደሩ ማድረግ ነው ይላሉ። ለዚህም የቴሌኮም ዘርፉ ለግል ከተሰጠ ከ20 ዓመታት በኋላ መሻሻል ማሳየቱን እንደ ማሳያነት ይጠቅሳሉ።

ነገር ግን መንግስት ለኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦቱ ተመሳሳይ የመፍትሄ ርምጃ ሊወስድ እንደሚችል እስካሁን ምንም አመላካች ነገር የለም።