በአፍጋኒስታን የአየር ጥቃት 23 ንፁሃን ዜጎች መገደላቸውን የተባበሩት መንግስታት አስታወቀ

በጥቃቱ የተጎዳ ህፃን በሆስፒታል ህክምና ሲደረግለት

የፎቶው ባለመብት, EPA

የምስሉ መግለጫ, 10 የሚሆኑ ህፃናት ሲገደሉ 3 ቱ ለጉዳት ተዳርገዋል

በአፍጋኒስታን ደቡባዊ ግዛት ሄልማንድ አሜሪካ በፈፀመችው የአየር ድብዳባ ቢያንስ 23 ንፁሃን ዜጎች ተገደሉ። የተባበሩት መንግስታት እንዳስታወቀው አብዛኞቹ ተጎጂዎች ሴቶችና ህፃናት ናቸው።

የአየር ድብደባው የደረሰው የአፍጋን ወታደሮችና የአሜሪካ ኃይሎች ባካሄዱት ውጊያ ወቅት ነው።

ቢያንስ 10 ህፃናት እና 8 ሴቶች በጥቃቱ ሳይገደሉ እንዳልቀሩ ገልፀዋል። የአሜሪካ ኃይሎች ግን የተጎጂዎችን ቁጥር በማጣራት ላይ እንደሚገኙ መርማሪዎች አስታውቀዋል።

አሜሪካ ባለፈው ዓመት በአፍጋን ላይ ጥቃት ለማድረስ አዲስ ስልት ካወጀች ወዲህ በንፁሃን የሚደርሰው ጉዳት እየተባባሰ መጥቷል።

ስልቱ ፈንጂዎችንና በርካታ ቦምቦችን መጠቀምን የሚፈቅድ ነው።

የአሜሪካው ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ የታሊባንና እስላማዊ ታጣቂ ቡድኖችን ለማጥቃት የወታደሮችን ቁጥር ለማሳዳግ ባለፈው ዓመት ነበር ውሳኔውን ያሳለፉት።

በአፍጋኒስታን በአሜሪካ የሚመራው የኔቶ ጦር እንዳስታወቀው በጋርምሰር አካባቢ የሄሊኮፍተር ድብደባው የተፈፀመው በአሜሪካ የሚደገፈው የአፍጋን ልዩ ኃይልና ታሊባን ባደረጉት የተኩስ ልውውጥ ወቅት ነው።

ኔቶ በበኩሉ ታሊባኖች በርካታ ንፁሃን ዜጎች የሚጠለሉበትን ህንፃ እንደ ምሽግ መጠቀሙ ለበርካታ ንፁሃን ዜጎች ሞት ምክንያት ሆኗል ብሏል።

ስሙ እንዲጠቀስ ያልፈለገው የአካባቢው ነዋሪ ለቢቢሲ እንደተናገሩት የአየር ድብደባው ሲፈፀም የታሊባን ተዋጊዎች በህንፃው አቅራቢያ ነበሩ።

እማኙ ጨምረው እንደተናገሩት በጥቃቱ ከተጎዱት በዕድሜ ትንሹ የ 6 ዓመት ህፃን እንደሆነ ተናግረዋል።

በአፍጋኒስታን የተባበሩት መንግስታት እንዳስተወቀው ባለፉት 9 ወራት ብቻ በተፈፀመ የአየር ድብዳባ 649 ንፁሃን ዜጎች ለሞትና ለጉዳት ተዳርገዋል። ከአውሮፓውያኑ 2009 ጀምሮ የተጎጂዎች ቁጥርም እየጨመረ እንደመጣ ተናግረዋል።

ባለፈው ሚያዚያ ወር ብቻ በሰሜን ምስራቋ ኩንዱዙ ግዛት በአንድ የምረቃ ስነ ስርዓት ላይ በአሜሪካ የሚመራው የአፍጋን የአየር ጥቃት 30 ህፃናት መገደላቸውን አስታውሰዋል።

የአሜሪካ አየር ኃይል በዚህ ዓመት ብቻ ባለፉት 10 ወራት ቀደም ካሉት ዓመታት ጋር ሲነፃፀር ከፍተኛ ቁጥር ያለው 6 ሺህ የሚጠጉ የጦር መሳሪያዎችን አስገብቷል።

በአፍጋኒስታን የሚደርሰው እልቂት በይበልጥ የመንግስት ተቀናቃኝ በሆኑት የታሊባን ታጣቂዎችና በእስላማዊ ታጣቂ ቡድኖች የሚፈፀም ነው።