የሰከረው ጃፓናዊ አብራሪ የ10 ወራት እስር ተበየነበት

የፎቶው ባለመብት, PA
ጃፓናዊው አብራሪ ከበረራ በፊት በተደረገበት የአልኮል ምረመራ በሰውነቱ ውስጥ ከተፈቀደው የአልኮል መጠን 9 እጥፍ በላይ ወስዶ በመገኘቱ የ10 ወራት እስር ተበየነበት።
የ42 ዓመቱ ጎልማሳ ካሱቶሺ ጂትሱካዋ የመንገደኞች አውሮፕላን አብራሪ ሲሆን፤ ከሎንዶን ወደ ጃፓን መዲና ቶኪዮ በረራ ለማድረግ በዝግጅት ላይ ነበር።
የጃፓን አየር መንገድ አብራሪው በቁጥጥር ሥር የዋለው ከሁለት ቀናት በፊት ሲሆን ከታቀደው በረራ 50 ደቂቃ በፊት የተደረገለትን የትንፋሽ ምረመራ ማለፍ ሳይችል ቀርቷል።
በትንፋሽ ምረመራ ውጤትም በአብራሪው 100 ሚሊ ሊትር ደም ውስጥ 189 ሚሊ ግራም የአልኮል ምጠን የተገኘ ሲሆን ለአውሮፕላን አብራሪዎች የሚፈቀደው መጠን 20 ሚሊ ግራም ብቻ መሆኑም ተጠቅሷል።
የ10 ወራት እስር የበየኑበት ዳኛ ''ብዙ ልምድ ያለህ አብራሪ ነህ፤ ይሁን እንጂ የበረራ ሰዓቱ እንኳን ተቃርቦ አልኮል ስትጎነጭ ነበር። ይህን ረዥም በረራ ሊያደርጉ ሲሰናዱ የነበሩ መንገደኞችን ህይወት አደጋ ላይ ጥለህ ነበር። በረራው ቢከናወን ኖሮ እጅግ አስከፊ አደጋ ይከሰት ነበር።'' በማለት ገልጸውታል።
አብራሪው ከመጠን ያለፈ አልኮል መጠጣቱ የታወቀበት፤ አንድ የጸጥታ ኃይል አስከባሪ አብራሪው የጠጣው አልኮል ከሸተተው በኋላ ነበር። አብራሪው ዓይኑን መግለጥ እና ቀጥ ብሎ መቆም ተስኖት ነበር ተብሏል።

የፎቶው ባለመብት, PA
ከፍርድ ሂደቱ በኋላ የጃፓን አየር መንገድ ምክትል ፕሬዚዳንት ይህ አይነቱ ባህሪ ዳግመኛ እንዳይከሰት እንሰራለን በማለት ይቅርታ ጠይቀዋል።
አቃቤ ሕግ ግን የአየር መንገዱ ሰራተኞች አብራሪው የአልኮል መጠን በማለፉ ማብረር እንደማይችል ሲነግሩት ከዚያ ቀን ቀደም ብሎ በነበረው ምሽት ውስኪ መጠጣቱን እና የትንፋሽ ምረመራ አድርጎ ማለፉን ግልጾላቸው ነበር።
ከዚያም አብራሪው ወደ መጸዳጃ ቤት በማቅናት የአፍ መታጠቢያ ሳሙና በመጠቀም ሲግሞጦሞጥ ነበር ብሏል።
ሊያበረው የነበረው ቦይንግ 777 የበረራ አስተናጋጆቹን ጨምሮ 244 ተሳፋሪዎችን ይዞ የነበር ሲሆን፤ ከ69 ደቂቃዎች መዘግየት በኋላም ወደ ቶኪዮ በርሯል።












