አምነስቲ የማይናማሯን መሪ ሳን ሱ ኪን ከፍተኛ የተባለውን ሽልማት ነጠቀ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
አምነስቲ የማይናማሯን መሪ ሳን ሱ ኪ ከፍተኛ የሚባለውን "የህሊና አምባሳደር" ሽልማት ነጥቋቸዋል።
የሰላም የኖቤል ሽልማት አሸናፊዋ ፓለቲከኛ ይህንን ሽልማት የተቀበሉት በአውሮፓውያኑ 2009 ሲሆን በወቅቱም በቤት እስር ላይ ነበሩ።
የመብት ተሟጋቹ ድርጅት እንዳስታወቀው ይህንን እርምጃ ለመውሰድ የተገደደው በአገሪቱ ውስጥ የሮሂንጃን ጥቃት መከላከል ባለመቻላቸው እንደሆነ አስታውቋል። ከነዚህ ውስጥ 700 ሺ ህዝብ በላይ ወታደራዊ ጥቃትን በመፍራት ሸሽተዋል።
የ73 ዓመት ዕድሜ ባለፀጋዋ አን ሳን ሱ ኪ ይህ ሽልማት በቅርብ ጊዜ ካጧቸው ሽልማቶች አንዱ እንደሆነም ተገልጿል።
"የሰላም፣ የፅናትና የግለሰቦችን ሰብዓዊ መብት በመከላከል ረገድ የነበረሽ ተምሳሌነት አሁን የለም። ያንንም ስለማትወክይ እናዝናለን" በማለት የአምነስቲ ዋና ፀሐፊ ኩሚ ናይዱ ለማይናማሯ መሪ በፃፉት ደብዳቤ አስታውቀዋል።
ጨምረውም "በሮሂንጃ ላይ የደረሰውን ጭካኔያዊ ተግባርና የግፉን መጠን መካዷ ሁኔታውን ለማስተካከል ምንም ፍላጎት እንደሌለ አሳይ ነው" ብለዋል።
ምንም እንኳን የተባበሩት መንግሥታት ባደረገው ምርመራ መሪዋ ቀጥታ በባለፈው ዓመት የሮሂንጃ የዘር ጭፍጨፋ ቀጥታ ተሳታፊ አለመሆናቸውን ቢያረጋግጥም፤ ስልጣናቸውን በመጠቀም በሰራዊቱ የደረሱ ግድያዎችንና መደፈሮችን ማስቆም እንደተሳናቸው ገልጿል።
በአንድ ወቅት አምነስቲ የዲሞክራሲ ቁንጮ ብሏቸው የነበረ ሲሆን፤ ይህንንም ውሳኔ ያስተላለፈው የአን ሳን ሱ ኪ የቤት ውስጥ እስር ስምንተኛ አመት ክብረ በዓል ላይ ነው።
ለዲሞክራሲ ያደርጉት በነበረው ትግል የማይናማር አምባገነን መንግሥት ለ15 ዓመታት ያህል በቤት ውስጥ እስር አቆይቷቸዋል።
በዚህም ምክንያት የተለያዩ መንግሥታት፣ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች ክብራቸውን ለግሰዋቸው ነበር።













