የካናዳ ፓርላማ የምንያማሯ መሪ የሳን ሱ ኪን የክብር ዜግነት ገፈፈ

የምያንማር መሪ ሳን ሱ ክዪ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የካናዳ ፓርላማ አባላት ለምያንማሯ መሪ ሳን ሱ ኪ ሰጥቶ የነበረውን የክብር ዜግነት እንዲነሳ በሙሉ ድምጽ ወሰነ።

የክብር ዜግነታቸው እንዲነሳ የተወሰነባቸው የምያንማሯ መሪ በሃገራቸው የሮሂንጂያ ሙስሊሞች ላይ የደረሰውን ጥቃት ማስቆም አልቻሉም ተብሎ ነው።

ሳን ሱ ኪ በወታደራዊ ቁጥጥር በነበረችው የቀድሞዋ በርማ የአሁኗ ምያንማር ላመጡት ከፍተኛ ዴሞክራሲያዊ ለውጥ እ.አ.አ በ1991 የኖቤል የሰላም ሽልማትን አሸንፈው ነበር።

የተባበሩት መንግስታት ባለፈው ወር ባወጣው ሪፖርት የምያንማር ወታደራዊ መሪዎች ሮሂንጂያዎች ላይ ለፈጸሙት አሰቃቂ ተግባር በዘር ማጥፋት ወንጀል መጠየቅ አለባቸው ብሏል።

ባለፉት 12 ወራት ብቻ እስከ 700 ሺ የሚደርሱ ሮሂንጂያዎች ጥቃቱን በመሸሽ መኖሪያ ስፍራቸውን በመተው ተሰደዋል።

የካናዳው ጠቅላይ ሚኒስትር ጀስቲን ትራዴዉ ለምያንማሯ መሪ የተሰጠውን የክብር ዜግነት ለማንሳት የተወካዮች ምክር ቤቱ እያሰበበት ነው ማለታቸውን ተከትሎ ከአንድ ቀን በኋላ ነው የፓርላማ አባላቱ የካናዳ የክብር ዜግነታችውን የገፈፈው።

ሳን ሱ ኪ በ2007 የክብር ዜግነት ሲያገኙ በካናዳ ታሪክ ስድስተኛዋ ሰው ናቸው።

ከዚህ በኋላ የካናዳ መንግስት ምን እንደሚወስን ባይታወቅም ፓርላማው ግን ሮሂንጂያዎች ላይ የተፈጸመውን ወንጀል የዘር ማጥፋት ነው ብሎ እንዳጸደቀው የፓርላማው አባል የሆኑት አንድሪው ሌዝሊ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።

ፕሬዚዳንቷ ምንም እንኳን በምያንማር የተፈጸመውን ጥቃት እንዲያወግዙ ከመላው አለም ግፊት ቢደረግባቸውም፤ እስካሁን ያሉት ምንም ነገር የለም።