በደቡብ አፍሪካ የሚገኙ ንቦች የአውሮፕላን በረራ አስተጓጉለዋል

የፎቶው ባለመብት, News24
በደቡብ አፍሪካዋ የባህር ዳርቻ ከተማ ደርባን የአውሮፕላን ሞተር ውስጥ የንቦች መንጋ በመግባት ለበረራ የተዘጋጁ መንገደኞችን አስተጓጉለዋል።
ጉዳዩ ግራ ያጋባው የአየር መንገድ የንብ ማነብ ባለሙያዎችን በመጥራት እርዳታቸውን ጠይቋል። ባለሙያዎቹም በቦታው በመድረስ ቁጥራቸው እስከ 20 ሺ ይደርሳል የተባሉትን ንቦች ከሶስት የአውሮፕላን ሞተሮች ውስጥ በሰላም አስወጥተዋቸዋል።
አጋጣሚው አስገራሚና ያልተለመደ ነው ያሉት ከባለሙያዎቹ አንዱ አክለውም ምናልባት ንቦቹ ራቅ ወዳለ ቦታ እየተጓዙ ደክሟቸው የአውሮፕላኑን ሞተር እንደ ማረፊያ ተጠቅመውት ሊሆን ይችላል ብለዋል።
ነገሩን አስገራሚ የሚያደርገው ንቦች ለማረፊያነት የሚመርጧቸው ቦታዎች ብዙ ጊዜ አበባዎች በብዛት የሚገኙበትና ጥሩ መአዛ ያላቸው ናቸው።
በአውሮፕላን ነዳጅ ሽታና ሌሎች መጥፎ ጠረኖች የተሞላውን ሞተር መምረጣቸው ደግሞ ለባለሙያዎቹ ግርምታን ፈጥሮባቸዋል።
ንቦቹ የበረራ ፈቃዳቸውን እየጠበቁ የነበሩ ሶስት አውሮፕላኖች ሞተሮች ውስጥ ገብተው ሙሉ በሙሉ በቁጥጥራቸው ስር ለማድረግ 25 ደቂቃ እንደፈጀባቸው የአየር መንገዱ ቃል አቀባይ ሰርጂዮ ዶሳንቶስ ገልጸዋል።
የንብ ማነብ ባለሙያው ሜልቪን ዳውሰን ከዚህ በፊት ብዙ የንብ መንጋዎችን ከተለያዩ ቦታዎች እንዳስወጣና ይሄኛው አጋጣሚ ግን የመጀመሪያው እንደሆነ ለጋዜጠኞች ተናግሯል።
በአሁኑ ሰአት ንቦቹ በተመሳሳይ የስራ ዘርፍ ተሰማርቶ ከሚገኘው የወንድሙ የእርሻ ማሳ ውስጥ እንደሚገኙም አክሏል።












