ሆላንዳዊው ጡረተኛ የፍቅር አጋር ለማግኘት በማሰብ እድሜውን ለማስቀነስ ፍርድ ቤት ሄደ

የቲንደር ምልክት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ሆላንዳዊው ጡረተኛ ወጣት ሴቶችን በቲንደር ላይ ለማማለል እንዲመቸው እድሜውን ለማስቀነስ ፍርድ ቤት ሄዷል።

ኢሚሌ ራቴባንድ የተባለው የ69 ዓመት የዕድሜ ባለጸጋ ዕድሜውን በ20 ዓመት ዝቅ ለማድረግ የሕግ ትግል ላይ ነው።

''በፍርድ ቤቶች ስም መቀየር ይቻላል። ጾታን መቀየር ይቻላል። ዕድሜን መቀየር ለምን አይቻልም?'' ሲል ለአንድ የሆላንድ ጋዜጣ ተናግሯል።

ጉዳዩን የያዘው የአካባቢው ፍርድ ቤት በቀጣዮቹ አራት ሳምንታት ውሳኔ እንደሚያሳልፍ ይጠበቃል።

የሆላንዱ ጋዜጣ እንደዘገበው ከሆነ ፍርድ ቤቱ አንድ ግለሰብ እድሜውን ለመቀየር የሚያስችል የሕግ አግባብ ስለመኖሩ ጥረጣሬ አለው።

የ69 ዓመቱ ኢሚሌ ራቴባንድ ግን በእድሜው ምክንያት የሥራ ቅጥር ዕድል እና ቲንደር በተባለው የፍቅር አጋር መፈለጊያ መተግበሪያ ላይ እንደተገለልኩ ይሰማኛል ይላል።

''69 ስሆን እገደባለሁ። 49 ብሆን ግን አዲስ ቤት መግዛት እችላለሁ፤ የተለያዩ ዓይነት መኪናዎችን ማሽከርከር እችላለሁ። ብዙ ሥራዎችንም መስራት እችላለሁ።'' ብሏል።

''69 ስሆን ቲንደር ላይ ምንም አይነት ምላሽ አላገኝም። እድሜዬ 49 ቢሆን ግን ባለኝ መልክ እንደላቀቅ ነበር።''

ሰውየው የግል ሃኪሙ የሰውነት አካላቶቹ የ45 ዓመት ሰው እንጂ የ69 ዓመት የዕድሜ ባለጸጋ አይነት እንዳልሆነ አረጋግጦልኛል በማለት ራሴን ''ወጣት'' ብዬ ነው የምገልጸው ይላል።

ጡረተኛው በጥያቄው መሰረት ዕድሜው በ20 ዓመት ዝቅ ቢደረግለት ከጡረታው የሚያገኘውን ጥቅማጥቅም እንደሚተው ጨምሮ ተናገሯል።