ቢቢሲ ለንደን ከሚገኘው ቢሮ ቀጥሎ ግዙፉን ቢሮውን በናይሮቢ አስመረቀ

የፎቶው ባለመብት, Armstrong Too
ቢቢሲ እንግሊዝ ውስጥ ካለው ቢሮው ቀጥሎ እጅግ ግዙፍ የሆነውን ቅርንጫፉን ትላንት በይፋ አስመርቋል።
በኬንያ መዲና ናይሮቢ የሚገኘው ዘመነኛ ቢሮው ውስጥ ወደ 300 የሚጠጉ ባለሙያዎች ይሰራሉ።
ቢቢሲ በመላው አፍሪካ ወደ 600 ያህል ጋዜጠኞች አሉት።
የናይሮቢው የቢቢሲ የምስራቅ አፍሪካ ቅርንጫፍ አማርኛ፣ ትግርኛና ኦሮኦምኛን ጨምሮ ሌሎችም ቋንቋዎች የሚሰራጩበት ነው።
የቢቢሲ ኒውስ ዳይሬክተር ፍራንቼስካ አንስወርዝ "ትልቁ ኢንቨስትመንታችን በሙያ የላቁ አፍሪካዊ ጋዜጠኞችን ማፍራት ነው" ብለዋል።
በእንግሊዝ መንግሥት የሚደገፈው የቢቢሲ የማስፋፋፊያ ፕሮጀክት 376 ሚሊየን ዶላር ወጥቶበታል።
አዲስ የተመረቀው ቢሮ፤ የቴሌቭዥን ስቱዲዮ፣ የቀጥታ ስርጭት ማስተላለፊያ፣ ሁለት የራድዮ ስቱድዮ እንዲሁም አምስት የቴሌቭዥን አርትኦት ክፍሎች አሉት።
በያዝነው ዓመት መባቻ ላይ በናይጄሪያ የቢዝነስ መዲና ሌጎስ ውስጥ ሌላ የቢቢሲ ቢሮ ተከፍቶ ነበር። ከሌጎስ በኢግቦ፣ በዮሩባና በፒጅን ቋንቋዎች መሰናዶዎች ይሰራጫሉ።
የፈረናሳይኛ ቋንቋ ስርጭት የሚተላለፈው ደግሞ በሴኔጋል መዲና ዳካር ከተከፈተው ቅርንጫፍ ነው።
ቢቢሲ የናይይሮቢውን ቢሮ የከፈተው እንደ አውሮፓውያኑ በ1998 ነበር። አሁን እንግሊዘኛን ጨምሮ በ40 ቋንቋዎች መርሀ ግብሮቹን ያስተላልፋል።
የቢቢሲ ወርልድ ሰርቪስ የምስራቅ አፍሪካ ኃላፊ ሬቸል አኪዲ ቢሮው ትላንት ሲመረቅ "አፍሪካውያን ጋዜጠኞችን እያከበርን ነው። የቢቢሲን የሙያ ስነ ምግባር፣ መድልዎ የሌለበትን ዘገባ እንደያዝን እንቀጥላለን" ብለዋል።
የአዲሱ ቢሮ መመረቅ "መኒ ዴይሊ"ከተሰኘው አዲስ መሰናዶ መጀመር ጋርም ገጥሟል። የቢዝነስ መርሀ ግብሩ የሚሰራው ናይሮቢ ውስጥ ነው።

የፎቶው ባለመብት, Armstrong Too
"አፍሪካ አይ" የተባለው የምርመራ ዘገባ መሰናዶ በተጀመሩ በአጭር ጊዜ ከተወደዱ ቅንብሮች አንዱ ነው።
በአውሮፓውያኑ 2018 የዓለም ዋንጫ ስለ አንድ ዳኛ ጉቦ መብላት የተሰራው ዘገባ የአፍሪካ እግር ኳስ ፌደሬሽን (ካፍ) በይፋ ምርመራ እንዲጀምር ያነሳሳ ነበር።
በወርሀ መስከረም ሁለት ሴቶችና ሁለት ህጻናትን የገደሉ የካሜሩን ወታደሮችን ከጥልቅ ምርመራ በኋላ ይፋ ማውጣቱም ይታወሳል።












