ኢላን መስክ፤ ከዛከርበግ የሚገጥመው ቡጢ በኤክስ በቀጥታ እንደሚተላለፍ ተናገረ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የሜታ አለቃ ማርክ ዛከርበርግ ከተቀናቃኙ ኢላን መስክ ጋር ሊገጥም ስላሰበው ቡጢ “ብዙ እንደማይጨነቅ” ተናግሯል።
ትሬድስ በተሰኘው አዲሱ ማሕበራዊ ሚድያ ገጹ ቡጢው በፈረንጆቹ ነሐሴ 26 ሊካሄድ እንደሚችል ዛከርበርግ ጠቁሟል።
በቀድሞው ትዊተር በአሁኑ መጠሪያው ኤክስ ላይ ኢላን መስክ “በየቀኑ ልምምዴን እያደረግሁ ነው” ሲል ዛከርበርግ ደግሞ “እኔ ዛሬም ቢሆን ዝግጁ ነኝ. . . እሱ ግን እርግጠኛ አይደለም” ብሏል።
ሁለቱ ቢሊየነሮች በቡጢ ይዋጣልን ያሉት ማርክ ዛከርበርግ ትሬድስ የተሰኘውን የትዊተር ተቀናቃኝ ማሕበራዊ ሚድያ ይፋ ካደረገ በኋላ ነው።
በአንድ የትሬድስ ተጠቃሚ ግጥሚውን ሁለታችሁም አምናችሁበታል ወይ ተብሎ የተጠየቀው ዛከርበርግ “ፈንዱን አግኝተናል” ሲል መስክን ሸንቆጥ አድርጓል።
ቴስላ የተሰኘው ተሽከርካሪ አምራች ተቋም ባለቤት የሆነው መስክ በፈረንጆቹ 2018 ኩባንያው የግል ድርጅት ሊሆን “ፈንድ አግኝቷል” ካለ በኋላ ይህ ሳይሆን በመቅረቱ 20 ሚሊዮን ዶላር መክፈሉ አይዘነጋም።
ብዙዎች በጉጉት የሚጠብቁት ፍልሚያ ይሆናል አይሆንም የሚለው ጥያቄ እስካሁን እርግጠኛ ምላሽ አላገኘም።
በርካቶች ሁለቱ ልጥጥ ሐብታሞች እንዲሁ ለንግግር እንጂ አይቧቀሱም ይላሉ።
ኢላን መስክ “ትክክለኛው ቀን እስካሁን አልታወቀም” ማለቱ እንዲሁም አንገቱ እና ጀርባው ላይ ቀዶ ሕክምና ሊያደርግ እንደሆነ መናገሩ ቡጢውን ላናይ ነው የሚል ጥርጣሬ ጭሯል።
ሁለቱ ጉምቱ የማሕበራዊ ሚድያ ባለቤቶች በተለይ ከቅርብ ወራት ወዲህ በቃላት መጎነታተል ሥራቸው አድርገው ይዘውታል።
መስክ የቡጢ ግጥሚያው ኤክስ በተሰኘው የበይነ መረብ ገጽ ላይ በቀጥታ እንደሚተላለፍና ከቡጢው የሚገኘው ገቢ ለተራድዖ ድርጅቶች እንደሚሰጥ ፅፏል።
እንደው የቡጢው ዓላማ ምንድነው ተብሎ በአንድ የኤክስ ተጠቃሚ የተጠየቀው መስክ “ይህ ዘመናዊ ጦርነት ነው። ወንዶች ደግሞ ጦርነት እንወዳለን” የሚል ምላሽ ሰጥቷል።
የኢንስታግራም እና ፌስቡክ ባለቤት የሆነው ሜታ፤ ትሬድስ የተሰኘ አዲስ ማሕበራዊ ሚድያ ይፋ ባደረገ በቀናት ውስጥ 100 ሚሊዮን አዲስ ተመዝጋቢዎች አፍርቷል።
ነገር ግን ትሬድስ ከመዘገባቸው ተጠቃሚዎች ግማሽ ያህሉን ባለፈው ወር መገባደጃ መልሶ ማጣቱን ዛከርበርግ ተናግሯል።
ተቀናቃኙ ኤክስ ደግሞ በኢላን መስክ ቁጥጥር ሥር ከወደቀ ወዲህ በተለያዩ ጊዜያት ትችት እያስተናገደ ነው።
ከግማሽ በላይ የድርጅቱን ሠራተኞች ያሰናበተው መስክ፤ ጎብኚዎች ‘ሎግ ኢን’ ካላሉ በቀር ይዘቶችን ማየት እንዳይችሉ አድርጓል።
ባለፈው ሰኔ ኢላን መስክ ከዛከርበርግ ቡጢ መግጠም የሚፈልገው በፍርግርግ በታጠረ መድረክ ውስጥ መሆኑን ገልጦ ነበር።
ይህንን የተመለከተው ዛከርበርግ “አድራሻውን ላክልኝ” ሲል ፅፎ ነበር።












