የዕጣ አሸናፊ የሆኑት እናት እና ልጅ ለመጀመሪያ ጊዜ በጋራ ወደ ጠፈር ለጉብኝት ሊጓዙ ነው

የፎቶው ባለመብት, VIRGIN GALACTIC
የዕጣ ዕድል አሸናፊ የሆኑት የ18 ዓመቷ የዩኒቨርሲቲ ተማሪ እና እናቷ በጋር በመሆን በዚህ ሳምንት መጨረሻ ወደ ጠፈር ለጉብኝት ሊጓዙ ነው።
ቨርጂን ጋላክቲክ በተባለ ተቋም በሚደረገው ጉዞ በስኮትላንድ የሚገኘው የአበርዲን ዩኒቨርሲቲ ተማሪዋ እና እናቷ ዕጣ ደርሷቸው ነው በነጻ ይህንን ዕድል ያገኙት።
አናስታቲያ ሜየርስ እና እናቷ ኬይሻ ሻሃፍ ወደ ሕዋ ሲጓዙ በእናት እና ልጅ ደረጃ የመጀመሪያዎቹ ናቸው።
ከካሪቢያን አካባቢ ወደ ሕዋ በመጓዝም የመጀመሪያዎቹ ይሆናሉ።
እናት እና ልጅ ይህን ዕል ያገኙት እናት ኬይሻ በአጋጣሚ ዕጣ ውስጥ ለመካተት ቅጽ ከሞላች በኋላ ነው።
ኬይሻ ለልጇ አናስታቲያ የዩናይትድ ኪንግደም ቪዛ ለመጠየቅ ወደ ለንደን በቨርጂን አትላንቲክ አየር መንገድ ከአንቲጓ ወደ ለንደን እየተጓዘች በነበረበት ወቅት ነበር የጠፍር ጉዞ ማስታወቂያው ሲነገር የሰማችው።
“መጀመሪያ የተሰጠኝን ፎርም ሞላሁ፣ ከዚያ ከወራት በኋላ ከ20 ተመራጮች መካከል አንዷ እንደሆንኩ ተነገረኝ። ከዚያ የመጨረሻዎቹ አምስት ውስጥም መካተት ቻልኩ። መጨረሻ ላይም አሸነፍኩ” ብላለች ኬይሻ።
ከዚያም የቨርጅን ጋላክቲክ መሠራች ሪቻርድ ብራንሰን እና የቡድኑ አባላት መኖሪያ ቤቷ ድረስ በመምጣት አሸናፊ መሆኗን እንዳበሰሯት ትናገራለች።
አናስታቲያ ደግሞ ወደ ጠፈር ለጉብኝት እንድትሄድ ለዚህ ዕድል ያበቃት ስኮትላንድ ለመማር መወሰኗ መሆኑን ትናገራለች።
“አበርዲን ዩኒቨርስቲ ለመማር ባላመለክት እና ቪዛ ለማግኘት ብዙ እርቀት ዋጋ ባንከፍል ኖሮ ይህ ዕድል አይገኝም ነበር” ብላለች።
ለአናስታቲያ ወደ ስኮትላንድ በማምራት መማር ትልቅ ስኬት ቢሆንም ይህ ደግሞ ሌላ ምናልባትም ጥቂቶች ብቻ የሚያገኙትን ዕድል አስገኝቶላታል።
እናት እና ልጅ በቀጣይ ሐሙስ ጉዟቸውን ከአሜሪካዋ ኒው ሜክሲኮ ግዛት ወደ ጠፈር ያደርጋሉ።
ጋላክቲክ 02 ሁለተኛው የጠፈር ለጉብኝት የሚደረግ የንግድ በረራ ሲሆንደንበኞች በክፍያ የሚበሩበት ነው።
ሰዎች በዚህ ሮኬት አውሮፕላን ለመጓዝ እስከ 450 ሺህ ዶላር ይጠየቃሉ።
ጋላክቲክ 01 የበረረችው ባለፈው ሰኔ ወር ነበር። 85 ኪሎ ሜትር ከፍታ ላይ ደርሳ ነበር። ሁለተኛው ጉዞም ተመሳሳይ ከፍታ ይኖረዋል ተብሎ ይታሰባል።
ወደ ሕዋ በመብረር በዕድሜ ሁለተኛዋ ወጣት ሴት የሆነችው አናስታቲያ ጨረቃ ላይ የምታየውን ነገር ሌሎችን ለማበረታታት እንደምትጠቀምበት ተናግራለች።












