“ዩክሬን ውስጥ ከምዋጋ እስር ቤት ብገባ ይሻለኛል” ሩሲያዊው

ከሞስኮ 500 ማይልስ በምትርቀው ፖድፖሮዥይ ከተማ ባለሥልጣናት በአንድ የወታደር ምልመላ ቢሮ ተሰብስበዋል።
ስብሰባው የከተማዋ ነዋሪ የሆነው ሚካይል አሽችቭ ለውጊያ ወደ ዩክሬን መሄድ እንዳለበት ለመወሰን ነው።
ሚካይል ደግሞ ይሟገታል።
“እኔ ጦርነት ትክክል አይደለም ብሎ የሚያምን ሰው አይደለሁም።አንድ አገር እናት አገሬን ለመያዝ ከሞከረ ወይም በሩሲያ ላይ ጥቃት ለመሰንዘር ከሞከረ ቀጥታ ወደ ጦር ምልመላ ቢሮ ሄጄ ነው የምመዘገበው። ምንም ጥሪ ሳልጠብቅ። ነገር ግን አሁን ባለው ሁኔታ እናት አገሬ ላይ የተቃጣ የጦርነት ስጋት አለ ብየ አላምንም” ሲል ያብራራል።
ንግግሩን ተከትሎ አንድ ባለስልጣን “ ግን እኮ እናት አገራችን አደጋ ላይ ናት” ይላል።
ሚካይል ሩሲያ ዩክሬንን የወረረችበትን ቀን ጠቅሶ “አገራችን ከየካቲት 24 በፊት አደጋ ላይ አልነበረችም” ሲል ይመልሳል።
የ34 ዓመቱ ሚካሄል መካኒክ ነው።
ምንም እንኳን ሩሲያ የሲቪል እና ሰብዓዊ መብቶች የሚጣሱባት አገር እየሆነች ብትመጣም ሚካይል ግን የሩሲያ ሕገ መንግሥት የመቃወም መብት እንደሰጠው ይናገራል። በመሆኑም ዩክሬን ውስጥ እንዲዋጋ የቀረበለትን ጥሪ ለመቀበል አሻፈረኝ ብሏል።
“መዋጋት እንደማልፈልግ ስገልጽ በጣም ፈርቼ ነበር፤ ነገር ግን በኋላ ላይ ስናገር የተቀረፀውን ቪዲዮ ስመለከተው በተቃራኒው ሲያዳምጡኝ በነበሩ ሰዎች ዐይን ውስጥ ነበር ፍርሃት የተመለከትኩት።
“ሰዎችን እንደ ግዑዝ አካል ከአንድ ቦታ ወደ አንድ ቦታ በቀላሉ ማንቀሳቀስ ወይም እንደፈለጉ የሚያዙት አድርገው ማየት ስለለመዱ ይመስለኛል የእኔ ንግግር ያስደነገጣቸው። እኔ በድንገት ያልኩትን ብያለሁ” ይላል ሚካይል በወቅቱ የተሰማውን ሲገልጽ።
ከዚያ በኋላ ግን ማስፈራሪያዎች እንደተከተሉት ሚካይል ይናገራል።
“'ለፖሊስ እናመለክታለን ከዚያም ምርመራ ያካሂዱብሃል' አሉኝ” ይላል።
“እንደዚህ ሲሉኝ ነገሮች ከአቅማቸው በላይ እንዳይሆንባቸው እንደሰጉ ገባኝ። ምክንያቱም ይህ ያልለመዱት ነገር ነው። እነርሱ ሁሉንም ነገር መቆጣጠር የለመዱ ናቸው” ይላል ሚካይል።
እንደ ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ከሆነ “ከፊል ክተት” በሚል ባለፈው ወር ካወጁ በኋላ ከ220 ሺህ በላይ የሩሲያ ተጠባባቂ ኃይሎች ጥሪ ተደርጎላቸዋል።
የክሬምሊን መሪ ቅስቀሳው በቅርቡ እንደሚጠናቀቅ ቢያመላክቱም ቀነ ገደብ ግን አልተቀመጠም።
ከሳምንት በፊት ፕሬዝዳንት ፑቲን በቅስቀሳ ከተመለመሉ ወታደሮች ጋር በርያዛን ክልል በሚገኝ የሥልጠና ሥፍራ ላይ ስብሰባ ሲያካሂዱ የሚያሳይ ነው በሚል በመንግሥት ቴሌቪዥን ታይተዋል። ይህም ለሚያካሂዱት ቅስቀሳ የሕዝብ ድጋፍ ለማግኘት የተደረገ ሙከራ ነው ተብሏል።
ይሁን እንጂ በሩሲያ ውስጥ የሚካሄደው የክተት ቅስቀሳ በኅብረተሰቡ ዘንድ ስጋት ሳይፈጥር እንዳልቀረ ተነግሯል።
ባለፈው መጋቢት ወር ቭላድሚር ፑቲን ከዚህ በኋላ ምንም ዓይነት ቅስቀሳ እንደማይኖርና በጦርቱ ውስጥ የሚሳተፉት የሰለጠኑ ወታደሮች ብቻ ናቸው ሲሉ ቃል ገብተው ነበር።
“ከፊል የክተት አዋጅ” ባሉትና በመቶ ሺዎች ለሚቆጠሩ ተጠባባቂ ኃይሎች ጥሪ ካቀረቡ በኋላ ግን ይህ ሁሉ ተለውጧል።
በድንገትም ባሎች፣ አባቶች እና ልጆች ተመልምለው ወደ ጦር ግንባር ዘምተዋል። በአንዳንድ ሁኔታዎችም ያለምንም በቂ መሣሪያና ሥልጠና ጦርነቱን የተቀላቀሉ አሉ።

የፎቶው ባለመብት, kremlin pool
ከቅርብ ሳምንታት ወዲህም በቅስቀሳ ወደ ጦርነቱ የተቀላቀሉ ሩሲያውያን ስላሉበት መጥፎ ሁኔታ እና የመሣሪያ እጥረት ቅሬታቸውን በማኅበራዊ ሚዲያ ባጋሯቸው ቪዲዮዎች እየገለጹ ነው።
ሚካይል እንደሚለው በዙሪያው ያሉ ሰዎች በቅስቀሳው ምክንያት ስጋት ገብቷቸዋል። ምክንያቱን ሲገልጽም ይህ አሁን የሁሉንም ደጅ እያንኳኳ ስለሆነ ነው ይላል።
ሚካይል አልዘምትም ካለ በኋላ በሩሲያ ማኅበራዊ ሚዲያ መነጋገሪያ ሆኗል።
የተወሰኑ ተገቢ ያልሆኑ አስተያየቶች ተሰንዝረውበታል።
ከእነዚህ መካከል “ይህንን የሚያደርግ ሰው ራሱን ወንድ ብሎ መጥራት አይችልም” የሚሉት ይገኝበታል።
በተቃራኒው ደግሞ በርካቶች “መግደልን መቃወም ሰብዓዊነት ነው” የሚሉና ሌሎች አስተያየቶችን በመስጠት ደፋርነቱን እና ታማኝነቱን በመግለጽ አሞግሰውታል።
ሚካይል ማንኛውንም ሕጋዊ መንገድ ተጠቅሞ አቋሙን ለማስጠበቅ ቁርጠኛ ነው።
ይህ ካልተሳካልህስ? ተብሎ የተጠየቀው ሚካይል፣ “እንደዚህ ዓይነት ሁኔታ ከተፈጠረ ወደ እስር ቤት ቢወረውሩኝም ላለመዝመት ከቤተሰቤ ጋር ተነጋግረን ወስነናል። ማድረግ ግድ ነው ከተባለ ግን እስር ቤትን እመርጣለሁ። ምንም የሚያስፈራ ነገር የለውም።
“ዩክሬን ውስጥ ሰዎች ፍርስራሽ ውስጥ እየሞቱ እና ወላጆች ልጆቻቸውን እየቀበሩ እንደሆነ እናውቃለን። ካልሄድኩና በዚህ ጦርነት ካልተዋጋሁ መንግሥት እንደ ወንጀለኛ ሊያየኝ ይችላል፤ ይሁን እንጂ ከሰብዓዊነት እና ከራሴ አመለካከት አንጻር እኔ ወንጀለኛ አይደለሁም” ሲል ምላሽ ሰጥቷል።












