ሩሲያ ተቃውሞ እየገጠመው ባለው የክተት ጥሪ ላይ ስህተት መኖሩን አመነች

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ተቃውሞ እያስተናገደ የሚገኘው እና የሩሲያ ተጠባባቂ ጦር በዩክሬን ጦርነት እንዲሳተፍ የተደረገው የክተት ጥሪ ላይ ስህተት መኖሩን ክሬምሊን አምኗል።
የፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ቃል አቀባይ ህጎች የተጣሱበት አጋጣሚዎች አሉ ያሉ ሲሆን ስህተቶቹ በሙሉ ይታረማሉ ብለዋል።
በሩሲያ ወታደራዊ ልምድ የሌላቸው፣ እድሜያቸው የገፋ ወይም የአካል ጉዳት ያለባቸው ሰዎች ጦሩን እንዲቀላቀሉ እየተደረገ መሆኑን በርካታ ሪፖርቶች አመላክተዋል።
ባለፈው ሳምንት የቀረበው የክተት አዋጅ ከፍተኛ ህዝባዊ ተቃውሞን ቀስቅሷል።
ከቀናት በፊት ፕሬዝዳንት ፑቲን ከፊል የክተት ጥሪ ሲሉ የገለጹትን አዋጅ ይፋ አድርገዋል። ይህንንም ተከትሎ የመከላከያ ሚኒስትሩ ሰርጌ ሾዩጉ 300 ሺህ የሚሆን ተጠባባቂ ጦር ጥሪ ሊደረግለት ይችላል ብለዋል።
ሆኖም በጥሪው እስከ 1 ሚሊዮን ሰው ሊካተት እንደሚችል በክሬምሊን ድረገጽ ወጥቶ የነበረው የፑቲን የክተት አዋጅ ላይ ተጠቅሶ እንዲወጣ ወይም በሚስጥር እንዲያዝ የተደረገ አንቀጽን በማስረጃነት በመጠቀስ በተቃውሞ ጎራ ያሉ የሩሲያ ሚዲያዎች ገልጸዋል።
ዩክሬን እና በምዕራቡ ዓለም የሚገኙ በርካታ የወታደራዊ ሳይንስ አዋቂዎች ፑቲን ተጠባባቂ ጦራቸውን ለመጥራት የተገደዱት ከ7 ወራት በፊት በዩክሬን ላይ በቀሰቀሱት ወረራ በጦርነት ሜዳዎች ክፉኛ እየተሸነፉ ስለሆነ ነው ይላሉ።
የክተት አዋጁ ይፋ ከሆነበት ጊዜ ጀምሮ በተቃውሞ የተሳተፉ ከ 2 ሺህ የሚልቁ ሰዎች በመላው ሩሲያ መታሰራቸው ተሰምቷል።
ትላንት በነበረ ጋዜጣዊ መግለጫ የፑቲን ቃል አቀባይ ዲሜትሪ ፔስኮቭ ስህተቶች ተፈጽመዋል ብለዋል።
በተወሰኑ አካባቢዎች የግዛት አስተዳዳሪዎች ችግሩን ለማስተካከል በትጋት እየሰሩ ነው ብለዋል።
የተለያዩ መገናኛ ብዙሃን የክተት ጥሪውን ሸሽተው የሚወጡ ሰዎችን ለመቆጣጠር ሩሲያ ድንበሮቿን ዘግታለች የሚል ዘገባ እየወጡ ይገኛሉ።
ቃል አቀባዩ ግን ይህ ስለመሆኑ መረጃ የለኝም ብለዋል።
የክተት ጥሪው ከተሰማበት ጊዜ ጀምሮ በርካታ ወጣት ሩሲያውያን ሀገራቸውን ጥለው ለመሸሽ እየሞከሩ ነው።
የሳተላይት ምስሎች በጆርጂያ ድንበር አቅራቢያ የሩሲያውን መኪና ረጀም ሰልፍ ሰርተው ያሳያሉ።












