የኢትዮጵያን የሆቴልና ቱሪዝም ገበያ እየተቀላቀሉ የሚገኙት ዓለም አቀፍ ሆቴሎች

ራማዳ አዲስ

የፎቶው ባለመብት, Ramada Addis

አዲስ አበባን በዲፕሎማቲክ ማኅበረሰብ መቀመጫነቷ የሚቀድሟት የቤልጄየሟ ብራሰልስ እና የአሜሪካዋ ኒውዮርክ ናቸው።

የአፍሪካ ኅብረት፣ የተባበሩት መንግሥታት ኢኮኖሚክ ኮሚሽን እንዲሁም የበርካታ አገራት ኤምባሲዎች መቀመጫቸውን አዲስ አበባ ማድረጋቸው ለአገሪቱ የሆቴል እና የቱሪዝም ዘርፍ ትልቅ ገበያ ነው።

አገሪቱ ካሏት የቱሪስት መስህቦች አንጻርና በከተማዋ ከሚካሄዱ አህጉራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ስብሰባዎች ጋር ተያይዞ የሆቴል እና ቱሪዝም ዘርፍ በፍጥነት እያደገ እንደሚገኝ ቢቢሲ ያነጋገራቸው ባለሙያዎች ይናገራሉ።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መረጃ በከተማዋ 148 የተለያየ የኮከብ ደረጃ ያላቸው ሆቴሎች እንደሚገኙ ያሳያል።

የአዲስ አበባ ሆቴል ባለቤቶች ፕሬዝዳንት የሆኑት አስቴር ሠለሞን በበኩላቸው በማኅበራቸው ውስጥ ከባለ አንድ እስከ ባለ አምስት ኮከብ የያዙ 174 የሆቴል ባለንብረቶች በአባልነት ተመዝግበው እንደሚገኙ ገልፀው ይህ ግን በከተማይቱ የሚገኙትን ሁሉንም ባለንብረቶች እንደማይጨምር ይናገራሉ።

የአዲስ አበባ ሆቴል ባለንብረቶች ማኅበር መረጃ በበኩሉ በአሁኑ ጊዜ በአዲስ አበባ ብቻ በባለ ኮከብ ሆቴሎች ዘንድ ከ10 ሺህ በላይ መኝታ ክፍሎች እንደሚገኙ ያሳያል።

ዓይናቸውን አዲስ አበባ ላይ የጣሉ ዓለም አቀፍ ሆቴሎች

ራዲሰን ብሉ

የፎቶው ባለመብት, Radison Blu

በርካታ ዓለም አቀፍ ስም እና ዝና ያላቸው ሆቴሎችም የኢትዮጵያን ገበያ ከተቀላቀሉ ከራርመዋል።

በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ ዓለም አቀፍ ስም ያለው ሆቴል የተከፈተው እኤአ በ1969 ሂልተን ሆቴል ነበር።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ከዚያ በኋላ ደግሞ ሸራተን አዲስ እኤአ በ1998 ተከፍቷል።

የኢትዮጵያ ሚሌኒየምን ተከትሎ ግን በርካታ ሆቴሎች ቅርንጫፎቻቸውን በአዲስ አበባ ከፍተው አገልግሎት እየሰጡ ነው።

በሆቴል እና ቱሪዝም ባለሙያነት ላለፉት 15 ዓመታት በመስራት ላይ የሚገኙት ሮማን ታፈሰ ከ10 ዓመታት በፊት ዓለም አቀፍ ስም የያዙት ሸራተን እና ሂልተን ብቻ እንደነበሩ ያስታውሳሉ።

በአገሪቱ በመንግሥት ባለቤትነት የተያዙ እና ጥቂት ባለሃብቶች ያቋቋሟቸው ሆቴሎች ብቻ ይገኙ አንደነበርም ይናገራሉ።

በሆቴል ኢንዱስትሪው ዘርፍ በማማከር የሚሰሩት እና በማሞኮቻ ውስጥ በኃላፊነት እየገለገሉ የሚገኙት አቶ ታሪኩ ኃይሉ፣ ትልልቅ ዓለም አቀፍ ስም ያላቸው ሆቴሎች ወደ አገር ውስጥ መምጣት የጀመሩት ካለፉት ሰባት ዓመታት ወዲህ መሆኑን ይጠቅሳሉ።

በአሁኑ ወቅት የዓለም አቀፍ ስም ያላቸው ሆቴሎች መምጣት ቀድመው የነበሩትን በዋጋ፣ በአገልግሎት ረገድ ራሳቸውን እንዲፈትሹ ማድረጉን ያነሳሉ።

በሙያው ላለፉት 16 ዓመታት በሥራ ላይ ለሚገኙት አቶ ታሪኩ የሆቴል ኢንዱስትሪው “እድገት ቢዘገይም ፈጣን የሚባል ነው።”

የሆቴሎች ማደግ ብቻ ሳይሆን ባለሙያዎችም የተለያዩ አማራጮችን እያገኙ ነው የሚሉት አቶ ታሪኩ፣ በአገር ውስጥ ሦስተኛው ኢንተርናሽናል ሆቴል ራዲሰን ብሉ መሆኑን ይናገራሉ።

ከዚያም በኋላ ራማዳ አዲስ፣ ማሪዮት፣ ጎልደን ቱሊፕ፣ ሃያት ሪጀንሲ እና ቤስት ዌስተርን ኢንዱስትሪውን መቀላቀላቸውን አቶ ታሪኩ ያስረዳሉ።

የአዲስ አበባ ሆቴል ባለቤቶች ፕሬዝዳንት በበኩላቸው መንግሥት አዲስ አበባን የኮንፍረንስ ከተማ የማድረግ ዕቅድ ይዞ እየሰራ መሆኑን በማስታወስ፣ ይህንን ተከትሎ በርካታ ሆቴሎች በከተማዋ ተስፋፍተዋል ይላሉ።

ለወ/ሮ አስቴር ግን ብዙ ሆቴሎች ቢኖሩም “ብዙ ቁጥር ያለው አልጋ ያላቸው ሆቴሎች ቁጥር አነስተኛ ናቸው።”

ይህንንም በማስረጃ ሲያስደግፉ፣ “በባለ ኮከብ ሆቴሎች ላይ በግምት ወደ 11 ሺህ አልጋ ነው ያለው” በማለት ነው።

ይህ ደግሞ ትልልቅ ስብሰባዎችን በአንድ ጊዜ ለማስተናገድ ቢታሰብ የአቅም ውስንነት ይከሰታል ባይ ናቸው።

ሮማን በበኩላቸው ሆቴሎች አሁን በቁጥርም፣ በህንጻ ጥራትም በከፍተኛ ደረጃ እያደጉ መጥተዋል ካሉ በኋላ፣ አገልግሎቱ ላይ ግን አሁንም ክፍተት መኖሩን ይጠቅሳሉ።

ታሪኩ ኃይሉ

የፎቶው ባለመብት, Tariku

የምስሉ መግለጫ, ታሪኩ ኃይሉ

አዲስ አበባን ብቻ ያፈቀሩ ዓለም አቀፍ ሆቴሎች

ለአቶ ታሪኩ ግርምት ከሚፈጥሩ ነገሮች መካከል አንዱ ዓለም አቀፍ ስም ያላቸው ሆቴሎች የሚገኙት በአዲስ አበባ ብቻ መሆኑ አንዱ ነው።

በዚህ ሀሳብ የሚስማሙት ወ/ሮ አስቴር በበኩላቸው፣ በአዲስ አበባ በርከት ያሉ ሆቴሎች የሚገኙት በቦሌ እና በካዛንቺስ አካባቢ መሆኑን ያክላሉ።

አቶ ታሪኩ “ይህም ለከተማዋ መጨናነቅ አስተዋጽኦ ካደረጉ ነገሮች መካከል አንዱ ነው ብዬ ነው የማምነው” ይላሉ።

ይህንን የገበያ ድርሻ እንደ ቢሾፍቱ እና ሐዋሳ ያሉ ከተሞች ቢያገኙት የበለጠ መጠቀም እንደሚቻል የሚያስረዱት አቶ ታሪኩ በየክልሎች ማሰባጠር ቢቻል ሲሉ ምኞታቸውን ይገልጻሉ።

ለሆቴል ቢዝነስ የሚከፈትበት አካባቢ ወሳኝ ነው የሚሉት ወ/ሮ አስቴር ደግሞ፣ አየር መንገዱ አቅራቢያ የሚገኙትን በማንሳት የሆቴሎች በአንድ ስፍራ ተሰብስቦ መገኘት በእኛ አገር ብቻ የሚታይ አይደለም ይላሉ።

በአዲስ አበባ ከቦሌ ባሻገር በርካታ ሆቴሎች የሚገኙት ካዛንቺስ አካባቢ ነው የሚሉት ባለሙያዎቹ፣ ይህም ሊሆን የቻለው የተባበሩት መንግሥታት እና የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽንን ቢሮዎችን ተከትሎ መሆኑን ይጠቅሳሉ።

“አሁን አሁን ግን ፈንጠር ፈንጠር እያሉም እየመጡ ነው” የሚሉት ወ/ሮ አስቴር ዓለም አቀፍ ስም ይዘው የመጡ ሆቴሎችም ከአዲስ አበባ ውጪ እየተሰሩ ናቸው ብለዋል።

ሮማን በበኩላቸው አዲስ አበባ የአፍሪካ መዲና ከመሆኗ ባሻገር በከተማዋ ውስጥ የሚካሄዱ ኮንፍረንሶች እና ኤቨንቶች፣ ሆቴሎች በአዲስ አበባ እንዲበዙ ምክንያት መሆናቸውን ያምናሉ።

ወ/ሮ ሮማን የግል ልምዳቸውን በመጥቀስ በአሁኑ ወቅት የአገር ውስጥ ጎብኚዎች በከፍተኛ ደረጃ በሳምንት መጨረሻዎች ላይ ከከተማ እንደሚወጡ ያስረዳሉ።

ድርጅቶችም ቢሆኑ ሠራተኞቻቸውን ለማዝናናት እግረ መንገዳቸውንም ስብሰባዎችን ለማካሄድ ከከተማ ውጪ ያሉ አካባቢዎችን እየመረጡ እንደሆነ በማንሳት፣ ዓለም አቀፍ ሆቴሎች ዐይናቸውን ወደ ክልል ከተሞችም ጣል ቢያደርጉ ሲሉ ይመክራሉ።

የሆቴል እና ቱሪዝም ባለሙያዋ ሮማን፣ አንድ መረሳት የሌለበት ነገር በማለት፣ የፀጥታ እና ሰላም መደፍረስ የሆቴል ኢንዱስትሪውን በቀላሉ ድንጉጥ ከሚያድጉት ነገሮች መካከል አንዱ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ሂልተን ሆቴል

የፎቶው ባለመብት, Hilton

የዓለም አቀፍ ሆቴሎች የመምጣት በረከቶች

ኢትዮጵያ ውስጥ ሥራ ከጀመሩ ዓለም አቀፍ ሆቴሎች በተጨማሪ በቅርቡ የአገሪቱን ገበያ ይቀላቀላሉ ተብለው የሚጠበቁት አይቪውአይ፣ ፎር ፖይንትስ ባይሸራተን፣ ፑል ማን፣ ደብል ትሪ ባይ ሂልተን እንደሚገኙበት አቶ ታሪኩ ያስረዳሉ።

እነዚህ ዓለም አቀፍ ሆቴሎች በኢትዮጵያውያን ባለሃብቶች የተከፈቱ እና አስተዳደሩን ግን ዓለም አቀፍ ስም ያላቸው አስተዳዳሪዎች እንደሚመሩት የሆቴል ባለንብረቶች ፕሬዝዳንቷ አስቴር ይናገራሉ።

አቶ ታሪኩ የእነዚህ ሆቴሎች ወደ አገር ወስጥ መምጣት በቅድሚያ የክህሎት ሽግግር ለማድረግ እንደሚያግዝ ያብራራሉ።

አክለውም እነዚህ ዓለም አቀፍ ሆቴሎች በዓለም ላይ ያላቸውን ልምድ እና የአገልግሎት ጥራት ደረጃ ወደ አገር ውስጥ በሚያመጡበት ወቅት ባለሙያው ያንን የመልመድ እና የመማር ትልቅ ዕድል ይኖረዋል።

ወ/ሮ አስቴር በበኩላቸው የእነዚህ ትላልቅ ስም ያላቸው ሆቴሎች በከተማይቱ መስፋፋት አገልግሎትን በጥራት ለተጠቃሚ ለማድረስ ይረዳሉ ይላሉ።

“በተጨማሪም ደግሞ የእነርሱን የሆቴል አስተዳደር ልምድ ለሌሎች ሆቴሎች የማዳረስ ነገር ስላለ” ዓለም አቀፍ ስም ያላቸው ሆቴሎች ወደ አገር ውስጥ መግባታቸው ጥቅሙ ሰፊ መሆኑን ያስረዳሉ።

ሌላኛው ደግሞ በረከታቸው ይላሉ አቶ ታሪኩ፣ “ኢኮኖሚያዊ” መሆኑን ገልፀው፣ ሆቴሎች የውጪ ምንዛሬን ወደ አገር ውስጥ በማምጣት ረገድ ድርሻቸው ከፍተኛ መሆኑን ይጠቅሳሉ።

ለአቶ ታሪኩ እነዚህ ዓለም አቀፍ ስም ያላቸው ሆቴሎች ወደ አገር ውስጥ ሲመጡ ቀድሞ የሚያተርፈው ባለሙያው ነው።

ሆቴሎቹ በዓለም ላይ ያላቸውን ስም እና ዝናን ለመጠበቅ ሲሉ በርካታ ሥልጠናዎችን ለሠራተኞቻቸው እንደሚሰጡ የሚገልፁት ባለሙያው፣ ከዚያ ተምረው የወጡ ደግሞ በሂደት አስተዳደሩንም ሆነ የአገልግሎት ዘርፉን ተረክበው መስራት ይችላሉ።

ከዚያም ባሻገር ከእነዚህ ሆቴሎች ወጥተው ሌሎች ሆቴሎች ማደራጀት እና መምራት የቻሉ መኖራቸውንም በመጥቀስ ለክህሎት ሽግግር የራሱ ድርሻ አለው ይላሉ።

ወ/ሮ አስቴር በበኩላቸው ዓለም አቀፍ ሆቴሎች ወደ አገር ውስጥ ሲገቡ የሚጠብቁት ምን አንደሆነ ሲናገሩ “በርካታ የሰው ኃይል ሰልጥኖ ወደ ሌሎች ሆቴሎች እንዲመጣ ነው” ይላሉ።

ነገር ግን እስካሁን የተመለከቱት የአገር ውስጥ ባለሃብቶች ያሰለጠኗቸውን የሰው ኃይል መቀራመት መሆኑን ይናገራሉ።

የሆቴል እና ቱሪዝም ባለሙያዋ ሮማን በአስቴር ሃሳብ ይስማማሉ።

እነዚህ ዓለም አቀፍ ሆቴሎች በክህሎት ሽግግር ላይ ያላቸው ክፍተት “የሚያሳዝነኝ ነው” በማለት መሻሻል እንዳለበት ያምናሉ።

የሆቴልና ቱሪዝም ባለሙያ ሮማን
የምስሉ መግለጫ, የሆቴልና ቱሪዝም ባለሙያ ሮማን

 የዓለም አቀፍ ሆቴሎች በጎ ተጽዕኖ

የእነዚህ ዓለም አቀፍ ሆቴሎች ልምድ በአገር ውስጥ ባለሀብቶች በተቋቋሙ ሆቴሎች ላይም ተጽዕኖው በበጎ ሁኔታ አንደሚታይ አቶ ታሪኩ ያነሳሉ።

በአገር ውስጥ በተለያየ ስፍራ 11 ሆቴል ያለው ኩሪፍቱ ሪዞርትስን እንዲሁም ኃይሌ ሆቴልስ ኤንድ ሪዞርትስን በመጥቀስ እነዚህ ሆቴሎች ተወዳዳሪ ለመሆን እየሰሩት ያለው ሥራ ከዓለም አቀፍ ሆቴሎች የተወሰደ በጎ ተሞክሮ መሆኑን ያነሳሉ።

ለአቶ ታሪኩ እነዚህ ሆቴሎች በአገልግሎት ጥራት ብቻ ሳይሆን፣ በሕንጻ አገነባብ ጭምር ተፎካካሪ ሆነው በመምጣት ላይ መገኘታቸውም የዚሁ አንዱ ማሳያ ነው።

በአቶ ታሪኩ ሃሳብ የሚስማሙት ወ/ሮ ሮማን፣ ሆቴሎች ተከታታይነት ሥልጠና ላይ በቂ በጀት መድበው መስራት እንዳለባቸውም ይናገራሉ።

ወ/ሮ አስቴር በበኩላቸው እነዚህ ዓለም አቀፍ ሆቴሎች ለአገር ውስጥ ባለሀብቶች ካበረከቱት በጎ ተጽዕኖ መካከል ተከታታይነት ያለው ሥልጠና አንዱ ነው።

ሆቴል ሲባል ትልቁን ድርሻ የሚይዘው አገልግሎቱ ነው የሚሉት ወ/ሮ አስቴር፣ መገንባቱ እና ቁሳቁስ ማሟላቱ ብቻ ሳይሆን፣ የሰው ኃይሉ የተሟላ አገልግሎት በመስጠት ረገድ ትልቅ ድርሻ እንዳለው ይናገራሉ።

የሆቴልና ቱሪዝም ማሰልጠኛዎቻችን በጥራት እና በአቅም ደረጃ በሚፈለገው መጠን አይደሉም የሚሉት አቶ ታሪኩ፣ ከጎረቤት ኬንያ አንጻር እንኳ በርካታ ሥራ የሚፈልግ ዘርፍ ነው ይላሉ።

ወ/ሮ ሮማን ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተመርቀው የሚወጡ የሆቴል እና ቱሪዝም ባለሙያዎች በበቂ ሁኔታ ተግባራዊ እውቀት ስለማይቀስሙ ለተጨማሪ የሥልጠና ወጪ የተዳረጉ መኖራቸውን በማንሳት ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ መሆኑን ይናገራሉ።

በርካታ ዩኒቨርስቲዎች በሆቴል አስተዳደር ዘርፍ ሥልጠና እንደሚሰጡ የሚናገሩት አቶ ታሪኩ፣ የትምህርት ጥራቱን ለማሻሻል መንግሥት ትኩረት ሰጥቶ በባለሙያ፣ በቁሳቁስ ማደራጀት ቢቻል በዘርፉ ላይ የተሻለ ለውጥ መስጠት እንደሚችል ይናገራሉ።

የአዲስ አበባ ሆቴል ባለንብረቶች ማኅበር በዘርፉ ላይ የታየውን የሥልጠና ክፍተት ለመሙላት በማሰብ ራሱን ባለ አምስት ኮከብ ሆቴል ያዘ የሥልጠና ማዕከል ለማቋቋም ጥናቱን አጠናቅቆ መቀመጡን ይናገራሉ።

በአገሪቱ ውስጥ ቀደምት የሆነው ሥልጠና ተቋም የሆቴል እና ቱሪዝም ማሰልተኛ ኢንስቲትዮት መሆኑን የሚያስታውሱት ባለሙያዎቹ፣ የሥልጠና ልኅቀት ማዕከል ለማድረግ ዕቅድ እንዳለ ወ/ሮ አስቴር እንደሚያውቁ ጠቅሰዋል።

እስካሁን ግን ክፍተቱን በመሙላት ረገድ ሆቴሎቹ ሚናቸውን እየተወጡ መሆኑን ባለሙያዎቹ ያስረዳሉ።