ኔታንያሁ በሐማስ የታገቱት እስራኤላውያን "በሚመጡት ቀናት" ይለቀቃሉ ብለው ተስፋ እንደሚያደርጉ ገለፁ

እስራኤላውያን ሰልፈኞች

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ በጋዛ የታገቱ ዜጎች መለቀቃቸውን "በመጪዎቹ ቀናት" አሳውቃለሁ ብለው ተስፋ እንደሚያደርጉ ተናገሩ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቴሌቭዥን በሰጡት መግለጫ "ሐማስ ትጥቁን ይፈታል እንዲሁም ጋዛ በቀላልም ሆነ በከባድ መንገድ ከወታደራዊ ኃይል ነጻ ትሆናለች፤ይሳካል" ብለዋል ።

ሐማስ ባለፈው አርብ በአሜሪካ የሰላም ዕቅድ መሠረት ታጋቾችን ለመልቀቅ ከተስማማ በኋላ የተሰማ ንግግር ነው።

ነገር ግን ቡድኑ ትጥቅ መፍታትን በሚመለከት የተናገረው ነገር የሌለ ሲሆን በሌሎች ጉዳዮች ላይ መደራደር እንደሚፈልግ አስታውቋል።

ሐማስ ቅዳሜ ዕለት እስራኤል በጋዛ የአየር ድብደባ ማካሄዷን ተከትሎ "እልቂት" መፈጸሟን እንደቀጠለች መሆኗን ገልጾ ዓለም አቀፍ ጫና እንዲደረግባት አሳስቧል።

በእስራኤል እና ሐማስ መካከል ቀጥተኛ ያልሆነ የተኩስ አቁም ንግግር የፊታችን ሰኞ በግብጽ ሊጀመር ቀጠሮ ተይዟል።

የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ስምምነቱን ለመፈጸም በሐማስ በኩል የሚፈጠርን "መዘግየት አልታገስም" ብለዋል።

ትራምፕ በትሩዝ ማኅበራዊ ድረ ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት ልጥፍ "ሐማስ በፍጥነት መወሰን አለበት፣ አለበለዚያ ሁሉም ስምምነት ይቋረጣል… ይህን በፍጥነት እናከናውን" ብለዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

በኋላ ላይ እስራኤል "የመጀመርያውን ጦሯን የማስወጣት እርምጃ ላይ ተስማምታለች" ሲሉ የጻፉ ሲሆን፣ ይህም በአሜሪካ ዕቅድ ውስጥ የተቀመጡትን በተለያየ ዙር የእስራኤል ወታደሮችን ከአካባቢው የማስወጣት እርምጃ የሚያመለክት ይመስላል።

የአሜሪካ ባለ 20 ነጥብ የሰላም ዕቅድ ጦርነቱ ባስቸኳይ እንዲቆም እና በሐማስ ስር ያሉ 20 ታጋቾች፣ እንዲሁም ሞተዋል የተባሉትን ጨምሮ እንዲለቀቁ ሃሳብ አቅርቧል።

በምትኩ በእስራኤል እስር ቤቶች ያሉ ፍልስጤማውያን እንደሚለቀቁ ተቀምጧል።

የእስራኤል መከላከያ በኤክስ ገፁ ላይ ባወጣው መግለጫ "ታጋቾቹን ለማስለቀቅ የትራምፕ እቅድ የመጀመሪያ ምዕራፍ ተግባራዊ ለማድረግ ዝግጁ እንዲሆን ትዕዛዝ መተላለፉን" ተናግሯል። የወታደሮቹ ደህንነት "ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ" መሆኑንም አክሏል።

ሐማስ የትራምፕን እቅድ ቢያንስ አንዳንድ ነጥቦችን እንዲቀበል ግፊት እየተደረገበት ነው።

በዚህም የተነሳ "እሺ፤ ግን" የሚል ምላሽ በመስጠት ድርድር እንደሚፈልግ ጠይቋል።

ቡድኑ በሕይወት ያሉ እንዲሁም የሞቱትን ታጋቾች በሙሉ ለመልቀቅ እና ጋዛ በተማሩ መሪዎች (ቴክኖክራት) እንድትመራ ተስማምቷል።

ነገር ግን፣ የእስራኤል ቁልፍ ፍላጎት የሆነውን ትጥቅ መፍታት መቀበል አለመቀበሉን አልጠቀሰም።

በጋዛ እና በእስራኤል መካከል አሁን ያለው የሰላም ጥረት በመጨረሻ ወደ ስምምነት ሊመራ ይችላል የሚል በጥንቃቄ የሚታይ ተስፋ አለ።

ትራምፕ ይህንን ጦርነት ያስቆሙ ሰው ሆነው መታወስ ስለሚፈልጉ ከፍተኛ ግፊት እያደረጉ ነው።

የበለጠ ወታደራዊ ኃይልን ለመጠቀም በማስፈራራት ሐማስ ስምምነቱን እንዲቀበል በይፋ አሳስበዋል።

እንዲሁም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በእስራኤል አመራር ላይ ያላቸው ብስጭት እየጨመረ መምጣቱን የሚጠቁሙ ምልክቶች አሉ።

ነገር ግን የትራምፕ ተፅዕኖ በቂ መሆን አለመሆኑ ግልጽ አይደለም።ምክንያቱ ደግሞ ቀደም ሲል የተደረጉ ስምምነቶችን ያፈረሱት መሰናክሎች አሁንም ተመሳሳይ ናቸው።

ሐማስ የእስራኤል ጦር ጋዛን ሙሉ ለሙሉ ለቅቆ እንዲወጣ የሚጠይቅ ሲሆን፣ እስራኤል ታጋቾቹ ከተፈቱ በኋላ ጦርነቱን እንደማትቀጥል ዋስትና ማግኘት ይፈልጋል።

ሌላው ጥርጣሬ ደግሞ በእስራኤል ውስጥ እና ከእስራኤል ውጭ ያሉ ብዙዎች ኔታንያሁ ጦርነቱን ለማራዘም ከዚህ ቀደም የተደረጉ ጥረቶች ለፖለቲካ ፍጆታ ሲሉ አጨናግፈዋል ሲሉ በተደጋጋሚ መክሰሳቸው ነው።

ኔታንያሁን የሚደግፉት ጽንፈኛ ሚኒስትሮቻቸው በዚህ ጦርነት ሐማስ ሙሉ በሙሉ ሽንፈት ሳይደርስበት ካበቃ ጥምረቱን ለቀን እንወጣለን ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

ይህ ደግሞ መንግሥታቸው እንዲፈርስ ሊያደርግ ይችላል።

በእስራኤል ውስጥ የተካሄዱ የሕዝብ አስተያየት መስጫዎች ብዙ እስራኤላውያን ታጋቾቹን ለማስለቀቅ እና ጦርነቱን ለማቆም ከሐማስ ጋር ስምምነትን እንዲደረግ እንደሚደግፉ ይጠቁማሉ።

የታጋቾች ቤተሰቦች በቅርቡ ዘመዶቻቸው ተለቅቀው እንደሚቀላቀሏቐቸው ተስፋ እንደሚያደርጉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ቪኪ ኮኸን ልጇ ናምሩድ በጋዛ ውስጥ እስካሁን በሕይወት አሉ ተብለው ከሚታመኑት 20 ታጋቾች መካከል አንዱ ነው።

ቪኪ ኮኸን ቅዳሜ ዕለት ከእንቅልፏ ስትነቃ አንድ ነገር ይሆናል በሚል ጉጉት መሆኑን ተናግራ፣ በሌላ ጎን ደግሞ "ችግር እንዳይፈጠር ስጋት" ውስጥ መሆኗን ተናግራለች።

"ይህ በጣም አስቸጋሪ ሁኔታ ነው እና እንደገና ማዘን አንፈልግም። ነገር ግን በቅርቡ ናምሩድን እንደማየው እና እንደገና ማቀፍ እንደምችል ተስፋ አለኝ" ብላለች።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ትራምፕ አርብ ዕለት በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ ባስተላለፉት መልዕክት እስራኤል "የቦምብ ጥቃቱን በአስቸኳይ እንድታቆም" ቢናገሩም ጦሩ በጋዛ ላይ የሚፈጽመውን ድብደባ ግን ቀጥሏል።

በአልሺፋ ሆስፒታል የሕክምና ምንጮች ቅዳሜ ዕለት በጋዛ ከተማ በተፈጸሙ ሦስት የአየር ድብደባዎች የአንድ ሰው ሕይወት ሲያልፍ በርካቶች መቁሳላቸውን ገልፀዋል።

በጋዛ የሚገኘው በሐማስ የሚመራው የጤና ሚኒስቴር ባለፉት 24 ሰዓታት ውስጥ በእስራኤል ወታደራዊ ዘመቻ 66 ሰዎች መሞታቸውን አስታውቆ፣ ይህም ጦርነቱ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ የሟቾቹን ቁጥር 67,074 አድርሶታል ብሏል።