የእስራኤል የባሕር ኃይል ወደ ጋዛ እየተጓዙ የነበሩ የሰብአዊ እርዳታ ጀልባዎችን ለሦስተኛ ጊዜ አስቆመ

ግሬታ ቱንበርግን ጨምሮ ሌሎችም ሰብአዊ እርዳታውን ይዘው እየተጓዙ የነበሩ የመብት ተሟጋቾች በእስራኤል ባሕር ኃይል ተይዘዋል።

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, ግሬታ ቱንበርግን ጨምሮ ሌሎችም ሰብአዊ እርዳታውን ይዘው እየተጓዙ የነበሩ የመብት ተሟጋቾች በእስራኤል ባሕር ኃይል ተይዘዋል።

የእስራኤል የባሕር ኃይል ወደ ጋዛ ሰብአዊ እርዳታ ይዘው በመጓዝ ላይ የነበሩ ጀልባዎችን ማስቆሙ ተገለጸ።

ስዊድናዊቷ የአየር ንብረት ለውጥ ተሟጋች ግሬታ ቱንበርግን ጨምሮ ሌሎችም ሰብአዊ እርዳታውን ይዘው እየተጓዙ የነበሩ የመብት ተሟጋቾች በእስራኤል ባሕር ኃይል ተይዘዋል።

የእስራኤል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በርካታ ጀልባዎች "ደኅንነቱን በጠበቀ መንገድ እንዲቆሙ ተደርጓል" ብሏል።

የመብት ተሟጋቾቹ ወደ እስራኤል ወደብ መወሰዳቸውም ተገልጿል።

ለጋዛ ሰብአዊ እርዳታ ለማድረስ በጀልባ የሚጓዙት ሰዎች ስብስብ (Global Sumud Flotilla ወይም GSF) እንዲቆም የተደረገው "ወደ ጦር ቀጣና በመቃረባቸው ነው" ሲል የእስራኤል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል።

ወደ ጋዛ እየተጓዙ የነበሩት ጀልባዎች 30 እንደነበሩና ከመዳረሻቸው በ85 ኪሎሜትር ርቀት ላይ ሳሉ እንዲቆሙ መደረጉን ጂኤስኤፍ ገልጿል።

"ሕገ ወጥ ነው። እኛን ለመከላከል የተደረገ ሳይሆን ተስፋ መቁረጣቸውን የሚያሳይ ነው" በማለትም ተቃውሟቸውን ገልጸዋል።

ከጀልባዎቹ አንዱ "ሆነ ተብሎ እንዲጋጭ ተደርጓል" ሲሉ የመብት ተሟጋቾቹ ተናግረዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ከፍተኛ መጠን ያለው ውሃ በሚለቅ መሣሪያ ጀልባዎቹ እንደተመቱም ጠቁመዋል።

ጂኤስኤፍ በማኅበራዊ ሚዲያው ባወጣው መግለጫ "ግዛቱን የሚያስፋፋው ኃይል የጋዛ ሕዝብ እንዲራብ እና ለብቻው እንዲነጠል ለማድረግ ብዙ ርቀት እንደሚጓዝ ማሳያ ነው" ብሏል።

ጨምረውም "ንጹኃን ዜጎች ሰብአዊ እርዳታ ለማድረስ ሲሞክሩ ጥቃት ይሰነዝራሉ። ይህንን የሚያደርጉት ደግሞ ሰብአዊ እርዳታ ከደረሰ ጋዛ ላይ የጣሉት ከበባ ስለሚከሽፍባቸው ነው" ብለዋል።

የእስራኤል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፤ ጀልባዎቹ "የባሕር ላይ ጉዞን የሚከለክል ሕግ" ጥሰዋል ብሏል።

"ክልከላው" የተጣለው ጋዛን በሚያዋስነው የባሕር ክፍል ላይ ነው ተብሏል። ሆኖም ግን ጀልባዎቹ በዚህ ክልል ውስጥ ስለመግባታቸው ግልጽ አይደለም።

ጀልባዎቹ በቁጥጥር ሥር ሲውሉ የሚያሳይ ተንቀሳቃሽ ምሥል የተለቀቀ ሲሆን፣ ስዊድናዊቷ የአየር ንብረት ለውጥ ተሟጋች ግሬታ ቱንበርግ ጀልባ ላይ ተቀምጣ ትታያለች።

የእስራኤል ወታደሮች ጃኬትና ውሃ ሲያቀብሏትም ይታያል።

የእስራኤል መንግሥት ጂኤስኤፍ ወደ ጋዛ ሰብአዊ እርዳታ ለማስገባት የሚያደርገውን ጥረት "ትንኮሳ" ሲል በመጥራት "ግሬታ እና ጓደኞቿ ደኅና ናቸው" ብሏል።

'ዘ አልማ' የተባለችውን ዋነኛ ጀልባ ጨምሮ 'ዘ ሱሪየስ' እና 'ዘ አዳራ' የተባሉ የሰብአዊ እርዳታ ጀልባዎችን የእስራኤል ባሕር ኃይል በቁጥጥር ሥር አውሏል።

ጂኤስኤፍ፤ የእስራኤል ጦር "ሆነ ብሎ የመርከብ መገናኛ መስመሮች ላይ ጉዳት አድርሷል። የአደጋ ጊዜ ጥሪ ማስተላለፊያ መሣሪያው የሚያስተላልፈውን መልዕክት አግዷል። የጀልባዎቹን ጉዞ የሚያሳይ የቀጥታ ሥርጭትንም አቋርጧል" ብሏል።

ጀልባዎቹ ዛሬ ጋዛ ይደርሳሉ ተብሎ ይጠበቅ ነበር።

የጀልባዎቹን መያዝ የሚቃወሙ እንቅስቃሴዎች በግሪክ፣ በጣልያን፣ በጀርመን፣ በቱኒዚያ እና በቱርክ ተጀምረዋል።

ጀልባዎቹ መያዛቸውን እንዲሁም "መብታቸው መጣሱን" በመቃወም የጣልያን ሠራተኞች ማኅበራት የሥራ ማቆም አድማ ጠርተዋል።

የቱርክ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጀልባዎቹ በቁጥጥር ሥር መዋላቸው "የሽብር ድርጊት ነው" በማለት "የዚህ ጥቃት አድራሾች ሊጠየቁ ይገባል" ሲል አሳስቧል።

የኮሎምቢያ ፕሬዝዳንት ጉስታቮ ፔድሮ የእስራኤል ዲፕሎማቶችን በአጠቃላይ ከአገራቸው አባረዋል።

ጀልባዎቹ መያዛቸውን ተቃውመው "የኔታንያሁ ዓለም አቀፍ ወንጀል" ነው ብለውታል።

በተጨማሪም ከ2020 አንስቶ ኮሎምቢያ ከእስራኤል ጋር ያላትን ነጻ የንግድ ስምምነት ሰርዘዋል።

በሰብአዊ እርዳታ ጀልባዎቹ ላይ የሚገኙ ሁለት ኮሎምቢያውያን እንዲለቀቁ ፕሬዝዳንቱ ጠይቀዋል።

የጀልባዎቹን መያዝ የሚቃወሙ እንቅስቃሴዎች በግሪክ፣ በጣልያን፣ በጀርመን፣ በቱኒዚያ እና በቱርክ ተጀምረዋል።

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, የጀልባዎቹን መያዝ የሚቃወሙ እንቅስቃሴዎች በግሪክ፣ በጣልያን፣ በጀርመን፣ በቱኒዚያ እና በቱርክ ተጀምረዋል።

የአየርላንድ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ሳይመን ሀሪስ ጀልባዎቹ መያዛቸው "አሳሳቢ ነው" ብለው እስራኤል ዓለም አቀፍ ስምምነትን እንድታከብር ጠይቀዋል።

ከተያዙት ሰዎች መካከል የሕዝብ እንደራሴው ክሪስ አንድሪውስ እና ሌሎችም አየርላንዳውያን ይገኙበታል።

ከዚህ ቀደም በሰኔ እና ሐምሌ ወራት ወደ ጋዛ ይጓዙ የነበሩ የሰብአዊ እርዳታ ጀልባዎችን እስራኤል አስቁማለች።

እስራኤል የጀልባዎቹ ጉዞ "ለሰልፊ ነው" ብላ ለማጣጣል ብትሞክርም ግሬታ ቱንበርግ ባለፈው ሳምንት ከቢቢሲ ጋር ባደረገችው ቃለ ምልልስ "የሰዎችን ትኩረት ለማግኘት ብሎ ማንም ሕይወቱን አደጋ ላይ አይጥልም" ብላለች።

ዓለም አቀፍ የተራድኦ ድርጅቶች ወደ ጋዛ ምግብ እና መድኃኒት ለማስገባት ቢሞክሩም እስራኤል አልፈቀደችም።

ሰብአዊ እርዳታው "በሐማስ እጅ እንዳይወድቅ" ክልከላው እንደተጣለ እስራኤል ትገልጻለች።

ስዊድናዊቷ የአየር ንብረት ለውጥ ተሟጋች ግሬታ ቱንበርግ

የፎቶው ባለመብት, Israeli foreign ministry

የምስሉ መግለጫ, ስዊድናዊቷ የአየር ንብረት ለውጥ ተሟጋች ግሬታ ቱንበርግ በእስራኤል ባሕር ኃይል ተይዛለች

እስራኤል እና አሜሪካ በጥምረት ምግብ ማከፋፈያ ማዕከላት አቋቁመናል ቢሉም የተባበሩት መንግሥታት የጋዛ ሰብአዊ እርዳታ ክፍል ማዕከላቱ "ሥነ ምግባር የጎደላቸው ናቸው" በሚል እንደማይተባበር አስታውቋል።

የመንግሥታቱ ድርጅት በጋዛ ረሃብ መስፋፋቱን አውጇል። የድርጅቱ የሰብአዊ እርዳታ ኃላፊ እስራኤል "በስልታዊ መንገድ እርዳታ እንዳይገባ አግዳለች" ብለዋል።

የፈረንሳይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዣን-ኖኤል ባሮት "ፈረንሳይ ማንኛውም የጀልባ እንቅስቃሴ ደኅንነቱ የተጠበቀ እንዲሆን አድርጋለች" የሚል መግለጫ አውጥተዋል።

የጣልያን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒዮ ታጃኒ እንዳሉት፣ ጣልያናውያን እና ፈረንሳውያን ፖለቲከኞችን ጨምሮ በጀልባዎቹ የተሳፈሩ 500 ሰዎች ላይ ጥቃት እንደማይደርስ ከእስራኤል ማረጋገጫ ተሰጥቷቸዋል።

"የጀልባዎቹ ጉዞ በዕቅድ ነው የተከናወነው። በእስራኤል ወታደሮች ጥቃት እንደማይፈጸምም ማረጋገጫ ተሰጥቶኛል" ብለዋል።

እስራኤል በጋዛ ላይ የምታደርሰውን ጥቃት አጠናክራ ቀጥላለች።

በአሜሪካ እና በእስራኤል የተረቀቀውን አዲስ የሰላም ዕቅድ በተመለከተ ከሐማስ ይፋዊ ምላሽ እየተጠበቀ ይገኛል።

የቱርክ እና የአረብ አገራት አሸማጋዮች ሐማስ ዕቅዱን እንዲቀበል ጫና እያደረጉ መሆኑ ተሰምቷል።

ከፍተኛ የሐማስ አመራር እንደሚሉት ግን ዕቅዱ ውድቅ የሚደረግበት ዕድል ሰፊ ነው።

የእስራኤል መከላከያ ሚኒስትር እስራኤል ከርትዝ፤ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ የጋዛ ነዋሪዎች ወደ ደቡባዊ ጋዛ እንዲሄዱ የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ ሰጥተዋል።

በጋዛ የሚቀሩት ሰዎች "ሽብርተኞች እና የሽብር ደጋፊዎች ናቸው" ብለዋል።

ዓለም አቀፉ የቀይ መስቀል ማኅበር እንዳለው፣ የጋዛ ነዋሪዎች በጋዛ ቢቆዩም ይሁን ጋዛን ለቀው ቢወጡ ከለላ ሊደረግላቸው እንደሚገባ ዓለም አቀፍ ሰብአዊ ስምምነት ያስገድዳል።