ሙሴቪኒ ልጄ ከአሁን በኋላ ትዊተር ላይ አወዛጋቢ ጉዳዮችን አይጽፍም አሉ

የፎቶው ባለመብት, MUHOOZI KAINERUGABA/TWITTER
የኡጋንዳው ፕሬዝዳንት ዩዌሪ ሙሴቪኒ ልጃቸው ከአሁን በኋላ አወዛጋቢ መንግሥታዊ ጉዳዮችን በተመለከተ ትዊተር ላይ እንደማይጽፍ አስታወቁ።
ፕሬዝዳንቱ ይህን ያሉት ልጃቸው ጄነራል ሙሆዚ ካይኒሩጋባ ትዊተር ላይ ብዙ አነጋጋሪ የሆኑ አስተያየቶችን መስጠታቸውን ተከትሎ ነው።
ከቅርብ ቀናት በፊት በአገሪቱ ሠራዊት ውስጥ ከፍተኛ የማዕረግ ደረጃ ነው የተባለ ሙሉ የጄኔራልነት ማዕረግ የተሰጣቸው ሙሆዚ ካይኒሩጋባ፤ ኢትዮጵያን ጨምሮ የተለያዩ አገራትንና መሪዎችን የሚመለከቱ ጉዳዮችን በመጻፍ ቅሬታን ሲፈጥሩ ቆይተዋል።
አወዛጋቢው ሙሆዚ ካይኒሩጋባ ከሁለት ሳምንታት በፊት ከስልጣናቸው ከመነሳታቸው በፊት የኡጋንዳ የምድር ጦር ኃይል አዛዥ ነበሩ። ጄኔራሉ ከዚህ ስልጣናቸው የተነሱት ትዊተር ላይ ካሰፈሯቸው አወዛጋቢ መልዕክቶች ጋር ስለመያያዙ የታወቀ ነገር የለም።
ጄኔራሉ በተለይ የጎረቤት አገር ኬንያ መዲና ናይሮቢን በተመለከተ በትዊተር ገጻቸው ላይ የለጠፉት ሐሳብ ስላቅ ይሁን ጽኑ ፍላጎት ኬንያውያን ያስደሰተ አልነበረም።
ጄኔራሉ “እኔ እና ሠራዊቴ ናይሮቢን ለመያዝ ሁለት ሳምንት ቢወስድብን ነው” ብለዋል። ቀጠል አድርገውም “ጦራችን ናይሮቢን ከተቆጣጠረ በኋላ የት መኖር መጀመር አለብኝ? ዌስትላንድስ ወይስ ሪቨርሳይድ?” ሲሉ የናይሮቢ አካባቢዎችን በመጥቀስ ትዊት አድርገው ነበር።
ይህን ተከትሎ የኡጋንዳ ፕሬዝዳንት ልጃቸው በትዊተር ላይ ለጻፉት ጉዳይ ይቅርታን ጠይቀዋል።
“ከትዊተር ራሱን ያገላል። በዚህ ላይ ተወያይተናል። ችግሩ ትዊተር አይደለም። ችግሩ ትዊት የምታደርገው ነገር ነው” ሲሉ ፕሬዝዳንት ሙሴቪኒ ለአንድ የኡጋንዳ ቴሌቪዥን ተናግረዋል።
ፕሬዝደንቱ ስለ ሌሎች አገራት እና ገለልተኛ ባልሆኑ የኡጋንዳ ፖለቲካዊ ጉዳዮች መናገር የሌለበት እና የማይናገርበት ጉዳይ ነው” ሲሉ ጨምረው ተናግረዋል።
ፕሬዝደንቱ ልጃቸው ትዊተር ላይ መጻፍ የሚችሉት ስለ “ስፖርት እና አወዛጋቢ ስላልሆኑ ጉዳዮች ብቻ” ይሆናል ብለዋል።
ፕሬዝዳንት ሙሴቪኒ ይህን ካሉ በኋላ ጄኔራሉ በትዊተር ገጻቸው ላይ፤ “ከኬንያ የሆኑ ጋዜጠኞች አባቴ ከትዊተር እንዲያግደኝ እየጠየቁ እንደሆነ እየሰማሁ ነው። ይህ ቀልድ መሆኑ ነው? እኔ ህጻን አይደለሁም ማንም ሰው ከምንም አያግደኝም!” ሲሉ የ48 ዓመቱ ጎልማሳ ጽፈዋል።
የኡጋንዳ መንግሥት በበኩሉ የፕሬዝዳንቱ ልጅ በተከታታይ በትዊተር ገጻቸው ላይ በሚለቋቸው ጽሁፎች ከተቀሰቀሱ ውዝግቦች ራሱን አርቆ ቆይቷል።
የኡጋንዳ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ መንግሥት ማኅበራዊ ሚዲያን የተመለከተ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ እንዳላዘጋጀ ገልጾ፣ ኡጋንዳ ከኬንያ ጋር ያላትን ጠንካራ የሁለትዮሽ ግንኙነት ከፍ አድርጋ እንደምትመለከተው ገልጿል።
'ትግራይን እከላከላለሁ' . . . 'ዳግማዊ ሚኒሊክ አያታችን ናቸው።'
የፕሬዝዳንት ሙሴቬኒ ልጅ ጄኔራል ሙሆዚ ቀጠናዊ እና ዓለም አቀፋዊ የሆኑ አነጋጋሪ ጽሁፎችን በትዊተር ገጻቸው ሲያጋሩ ይህ የመጀመሪያቸው አይደለም።
ሙሆዚ ኢትዮጵያን የተመለከቱ አወዛጋቢ ጽሑፎችን በትዊተር ገጻቸው ላይ ሲለጥፉ ነበር።
እሁድ መስከረም 22/2015 ዓ.ም. በትዊተር ገጻቸው ላይ ባሳፈሩት ጽሑፍ፤ “ትግራይ ሁሌም በልቤ አለች! ትግራይን እንድወድ እና እንድከላከል ከፈጣሪዬ ከእየሱስ ክርስቶስ የመጣ ትዕዛዝ ነው” ብለው ነበር።
በተመሳሳይ ዕለት ከሰዓታት በኋላ ደግሞ ጄኔራሉ ኢትዮጵያን በተመለከተ ባሰፈሩት ሌላኛው ጽሑፍ፤ “ዳግማዊ ሚኒሊክ አያታችን ናቸው። ኢትዮጵያ የምሥራቅ አፍሪካ አካል ናት። እንድትወድም አንፈቅድም። ሁሉንም የኢትዮጵያ ሕዝብ እንወዳለን!” ሲሉ ጽፈዋል።
ጄኔራሉ የኢትዮጵያው የእርስ በእርስ ጦርነት አንድ ዓመት በደፈነበት ጥቅምት 2014 ዓ.ም. ላይ የትግራይ ኃይሎችን ደግፈው ትዊት አድርገው ነበር።
“የትግራይ መከላከያ ኃይሎች . . . የቆማችሁበትን ዓላማ እደግፋለሁ። የትግራይ እህቶቻችንን የደፈሩ እና ወንድሞቻችንን የገደሉ መቀጣት አለባቸው” ሲሉ ጽፈው ነበር።












