‘በየሳምንቱ 12 የስኳር ህመምተኞች እየሞቱብን ነው’ - አይደር ሆስፒታል

የስኳር ህመምተኛ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ለሁለት አመት ያህል በዘለቀው ጦርነት በተጎዳችው ትግራይ ክልል በህክምና እጥረት ምክንያት በርካታ ነዋሪዎች እየሞቱ ይገኛሉ።

በአይደር ሆስፒታል ሜዲካል ዳይሬክተር የሆኑት ዶክተር ክብሮም ገብረስላሴ በቅርቡ በኢንሱሊን እጥረት ህይወቷን ስላጣችው ወጣት ታሪክ እንዲህ ይናገራሉ።

በቅርቡ ከሰሞኑ አንዲት ወጣት ሴት ከታመሙ እናቷ ጋር ወደ ዓይደር ሆስፒታል መጣች።

ይህች ልጅ በሌላ ህመም ተሰቃይተው የአልጋ ቁራኛ የሆኑትንና በሆስፒታሉ የተኙትን እናቷን ስትንከባከባቸው ለቀናት ቆይታ ነበር።

ሆኖም ይህቺ የእናቷን ህይወት ለማትረፍ የምትጣደፈው ወጣት ራሷን ስታ ወደቀች።

ዶክተሮች ህይወቷን ለማትረፍ የቻሉትን ያህል ሊረዷት ተሯሯጡ።

ራሷን ስታ የወደቀችበት ምክንያትም የጤና ባለሙያዎች እንደተረዱትከ ለስኳር ህመምዋ ማስታገሻ የሚሆን ኢንሱሊን ስላጣች ነበር።

“እኛ እያየን ነበረ የወደቀችው። ከዚያም ተሯሩጠን ወደ ፅኑ ህሙማን ክፍል (አይሲዩ) በፍጥነት አስገባናት። ልናተርፋት ግን አልቻልንም። በድንገት በወደቀች በማግስቱ ሞተች” ይላሉ ዶክተር ክብሮም ገብረስላሴ።

ከሰሞኑም ሌላ ህመምተኛ ወጣት ቤተሰቦቿ ተሸክመው ወደ አይደር አመጧት።

የስኳር በሽታ እንዳለባት እንኳን እንደማታውቅና ምርመራ ሲደረግላትም የስኳር በሽታ እንዳለባት መታወቁን የጤና ባለሙያ ይናገራሉ።

ህመሟ ምን እንደሆነ ቢያውቁም ዶክተሮች መድኃኒት ስላላገኙ በሆስፒታል ውስጥ ከአንድ ቀን በላይ በህይወት መቆየት አልቻለችም።

በመድኃኒትና በህክምና ቁሶች እጥረት ምክንያት እየሞቱ ያሉ ህመምተኞቻው ሁኔታ በአይደር ሆስፒታል ለሚገኙ የጤና ባለሙያዎች ልብ የሚሰብሩ ሆነው ቀጥለዋል።

"ህመምተኞቹ ከአንድ ቀን በላይ በህይወት አይቆዩም!"

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

በኢትዮጵያ ለሁለት ዓመታት በዘለቀው የርርስ በርስ ጦርነትን ተከትሎ መድኃኒትን ጨምሮ መሰረታዊ ቁሶች ውስን የሚገቡት ውስን በሆነባት ትግራይ የጤና ተቋማት ለታካሚዎች ተገቢውን አገልግሎት መስጠት በማይችሉበት አቅም ላይ ይገኛሉ።

በመቀለ የሚገኘው የአይደር ሪፈራል ሆስፒታልም በመድሀኒት ፣በህክምና መሳሪያዎች እና በኤሌክትሪክ አቅርቦት እጥረት ምክንያት ህሙማንም መታደግ ያልቻለ ሲሆን ወሳኝ የሚባሉ የህክምና አገልግሎትን ለማቆም ተገዷል።

ሆስፒታሉ የስኳር ህመምተኞችን ሁኔታ አስመልክቶ በቅርቡ ለኢትዮጵያ ስኳር ህመም ማህበር፣ ለኢትዮጵያ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር እና ለአለም አቀፍ የስኳር ህመም ፌዴሬሽን ደብዳቤ ጽፏል።

በርካቶች እየሞቱ እንደሆነና አስከፊ በሆነ አደጋ ላይ እንደሚገኙም አስታውቋል።

ለህመሙም ማስታገሻ በመርፌ የሚሰጥ ኢንሱሊን እና በአፍ የሚወሰድ ክኒን ነው።

በትግራይ ውስጥ 27 ሺህ የሚጠጉ ህሙማን በነዚህ የህክምና አማራጮች ህይወታቸውን እንደሚያስቀጥሉ ዶክተር ክብሮም ገብረስላሴ ለቢቢሲ ይናገራሉ።

“እነዚህ ታካሚዎች በየአካባቢያቸው ወደሚገኙ ሆስፒታሎች እየሄዱ ነበር ህክምናውን የሚያገኙት። ጦርነቱ እንደአዲስ ማገርሸቱን ተከትሎ ግን መድኃኒቶቹ ትግራይ ሊገቡ አልቻሉም። በክምችት ውስጥ የነበረንን ጨርሰን ሌላ እንዲላክልን በምንጠብቅበት ጊዜ ነበር ጦርነቱ ዳግም የተቀሰቀሰው” ብለዋል ዶክተሩ።

እሳቸው እንደሚሉት በተለይም በኢንሱሊን የሚታገዙ ሕመምተኞች ያሉበት ሁኔታ ጊዜ የሚሰጥ አይደለም። ኢንሱሊን በጊዜው ካላገኙ ለሞት እና ለሌሎች ውስብስብ የጤና እክሎች ተጋላጭ ሊሆኑ ይችላሉ እንደሚችሉም ያስረዳሉ።

ወደ 27,000 ከሚጠጉት የስኳር ህመምተኞች ውስጥ ከ8 ሺህ በላይ የሚሆኑት እድሜያቸው ከ 14 ዓመት በታች የሆኑ ህጻናት ናቸው።

ዶክተሮች ለእነዚህ ሕጻናት ስቃይ መስታገሻ የሚሆን መድኃኒት ስለሌላቸው ከሕመምተኞች ጋር ከማዘን ውጪ ሌላ ምንም አቅም የላቸውም።

ከዚህ ቀደም ለስኳር ህመምተኞች በተለይም ለህፃናቶች የሚሆን ኢንሱሊን ከዓለም አቀፍ የስኳር በሽታ ፌዴሬሽን ነበር በነፃ የሚቀርብላቸው።

ነገር ግን በአሁኑ ወቅት ከ8 ሺህ በላይ እድሜያቸው ከ14 ዓመት በታች የሆኑ በትግራይ የሚገኙ ህጻናት በችግሩ ምክንያት ለከፋ አደጋ እንደተጋለጡ ዶክተር ክብሮም ያስረዳል።

አክለውም "ህፃናት በተከታታይ እየሞቱብን ነው። ብዙ ሰዎች መድሃኒት ወይም ኢንሱሊን እንደሌለን ስለሚያውቁ ወደ እኛ መምጣት አቁመዋል። ታድያ ብዙዎች ወደዚህ ሳይመጡ ቤት ውስጥ ሞተዋል ማለት ነው” ይላሉ።

ህይወት ከመቀጠፍ በተጨማሪ በርካቶች ለከባድ የአይን ህመም፣ ለኩላሊት እና ለሌሎች በሽታዎች ተጋላጭ እየሆኑ ናቸው።

"ክኒን ወይም ኢንሱሊን ቶሎ የማይገኝ ከሆነ ብዙ ሰዎች የመዳን እድላቸው ጠባብ ነው። በቤት ውስጥ ያሉ ህሙማን መድሀኒት ካለቀባቸው ህይወታቸውን ማስቀጠል ከባድ ነው የሚሆንባቸው” በማለት ያለውን ሁኔታ ለቢቢሲ ይናገራሉ።

ዶክተር ክብሮም ገብረሥላሴ

የፎቶው ባለመብት, Dr Kibrom Gebreselassie

ታካሚዎቹ ምን ይላሉ?

ዶክተር ክብሮም እንደሚሉት ረጅም ጊዜ የቆየ በሽታ ያለባቸው ሰዎች ወደ አይደር ሆስፒታሉ መምጣት ስለሚያዘወትሩ በታካሚዎችና በጤና ባለሙያዎች መካከል ያለው ግንኙነት ጠንካራ እንደሚሆን ይታወቃል።

"እና እነዚህ የስኳር ህመምተኞች ለብዙ አመታት ከእኛ ጋር የቆዩ ናቸው። ከነርሶች እና ከሌሎች የጤና ባለሙያዎች ጋር እንደቤተሰብ ነው የሚቀራረቡት። በሁሉም ሆስፒታሎች በስም ሳይቀር ይተዋወቃሉ›› በማለት ሁኔታውን ያስረዳሉ።

ትግራይ ውስጥ የስልክም ሆነ መሰረታዊ አገልግሎቶች በመቋረጣቸው ህመምተኞችን ለማግኘት ቢቢሲ ቢያዳግተውም ዶክተር ክብሮምን ህሙማኑ መድኃኒት የለም ሲባል ምን እንደሚሰማቸው ጠይቀናቸዋል።

ከጦርነቱ በፊት በየወሩ ወደ ሆስፒታል እየመጡ መድሃኒት እና ምክር ይሰጣቸው የነበረ ሲሆን ዛሬ ያለው ሁኔታ ግን ከዚህ የተለየ ነው።

“ወደኛ መጥተው ‘መድሀኒት የለም’ ብለው ሲሸኟቸው በጣም እንደሚደነግጡ የሚናገሩት የጤና ባለሙያው ምክንያቱም መድኃኒት ካልወሰዱ በሕይወታቸው ስለሚያስከትለው አደጋ ለረጅም ጊዜም ሲነግሯቸው ስለነበር ነው።

“ስለዚህ ዛሬ ‘መድሀኒት የለንም’ ስንላቸው የምንመክራቸው ነገር ሁሉ ወደ አእምሮአችን ይመጣል” ይላሉ ዶክተሩ።

አንዳንዶቹ እንባቸውን ሲያፈሱ፣ ሌሎች ደግሞ ዶክተሮቹን ‘አድኑን። . . . . .! ችግራችንን ለአለም አሳውቁ’ በማለት ተማፅኖ እንደሚያቀርቡም ነው የጤና ባለሙያው የሚናገሩት።

በዚህ ሁኔታ እንቅልፍ ያጡ ባለሙያዎቹም የተለያዩ አካላትን አግኝቶ ሁኔታውን ለማስረዳት ከመሞከር በተጨማሪ፡ የታካሚዎች አጫጭር የቪዲዮ መልእክቶችን በማዘጋጀትና በማሰራጨት ሊረዷቸው የሚችሉ አካላትን በማፈላለግ ላይ ናቸው።

“በየቀኑ በስኳር ህመም ክሊኒክ ውስጥ ያለው ሀዘን እና ልቅሶ ልብ የሚሰብር ነው። በተቻለ መጠን መድሃኒቶችን ለማግኘት እየሞከርን ነው። በተለይ ለአካለ መጠን ያልደረሱ ሕፃናትን ጉዳይ ብንመለከት ስቃዩ ወላጆቻቸውንም የሚጨምር ነው የሚሆነው” ይላሉ የአይደር ሆስፒታል ሜዲካል ዳይሬክተር።

ወደ 27 ሺህ የሚጠጉት የስኳር ህመምተኞች ከጦርነቱ በፊት በሽታው እንዳለባቸው ያወቁ መሆናቸውን የሚያስታውሱት ዶክተሩ በአሁኑ ጊዜ ግን በቂ የህክምና አገልግሎት እና የመመርመሪያ መሳሪያዎች ባለመኖራቸው በበሽታው ቢያዙም እንኳን ሊያውቁ ያልቻሉ በሺዎች የሚቆጠሩ እንዳሉ ያምናሉ።

የአይደር አምቡላንስ

የፎቶው ባለመብት, MU

ደብዳቤው እና መልስ....?

አይደር ሆስፒታል ከቀናት በፊት ለኢትዮጵያ የስኳር ህመም ማህበር፣ ለአለም አቀፍ የስኳር ህመም ፌዴሬሽን እና ለኢትዮጵያ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ደብዳቤ ጽፎ ነበር። ደብዳቤው የስኳር በሽተኞችን ሁኔታ በማብራራት አስቸኳይ እርዳታ ይጠይቃል።

እንደ ዶክተር ክብሮም ገለጻ የአለም አቀፍ የስኳር ህመም ፌዴሬሽን መድሀኒቶችን ወደ ኢትዮጵያ ልኮ ነበር ወደ ትግራይ የሚደርሰው።

“መድሀኒቱ በተለይም ኢንሱሊን ለሁሉም ኢትዮጵያዊያን የስኳር ህመምተኞች በነጻ እንዲዳረስ ነው የሚላከው። ስለዚህ የእኛ ድርሻም በዛ ውስጥ ተካትቶ ነው የሚመጣው” በማለት የኢትዮጵያ የስኳር ሕመም ማኅበር መድኃኒቱን ወደ ትግራይ ለማድረስ ሲተባበር መቆየቱን ገልጿል ዶክተር ክብሮም።

የአለም አቀፍ የስኳር ህመም ፌዴሬሽን ባለፈው ሳምንት ባወጣው መግለጫ የኢንሱሊን እና ሌሎች የስኳር መድሀኒቶችን በፍጥነት ወደ ትግራይ ለማድረስ ለኢትዮጵያ መንግሥት ጥያቄ መላኩን አስታውቋል።

ፌዴሬሽኑ ህሙማን በከፍተኛ ስጋት ውስጥ መሆናቸውን ገልጾ የመድሃኒት አቅርቦትን ለማረጋገጥ ሁኔታዎች እንዲመቻቹ ጠይቋል።

አይደር ሆስፒታል ለፃፈው ደብዳቤ ከኢትዮጵያ ስኳር ህመም ማህበር ምላሽ እንዳገኘ የገለፀው ዶክተር ክብሮም “ዓለም አቀፉ ፌደሬሽን ከላከላቸው የስኳር መድሀኒቶች የትግራይ ድርሻ አዲስ አበባ እንዳለ ተነግሮናል” ብሏል።

“መንገድ ካገኘን እንልክላቹሃለን ብለው መልስ ልከውልናል። ይህን ማለታቸው መልካም ነው። ሆኖም ቀይ መስቀል ወደ መቀለ በፍጥነት እንዲያመጣ ፈቃድ ሊሰጠው ይገባል” ሲሉ ጥሪውን አቅርቧል።