ትግራይ፡ ህመምተኞቹን ለማከም መድኃኒት የሌለው ዶክተር

የፎቶው ባለመብት, AFP
ለ23 ወራት ያህል የርስ በርስ ጦርነት ማዕከል በሆነችውና እገዳ ላይ ባለችው ትግራይ መሰረታዊ የመድኃኒት እጥረት ህሙማንን እየገደለ ነው።
ሁለቱም ወገኖች ደቡብ አፍሪካ ሊደረግ ታቅዶ ለነበረው የሰላም ውይይት ተስማምተናል ባሉበት በዚህ ወቅት አንድ ዶክተር ሰብዓዊ ቀውሱ እልባት እንዲሰጠው እየተማጸኑ ነው።
ዶክተር ፋሲካ አምደስላሴ የሚናገሩት ጉዳይ መሬት ላይ ያሉትን ተጨባጭ እውነታዎች ቢሆንም ሁኔታውን ሲናገሩ በጣም አሳዛኝ ነው።
“የሰመመን መስጫ መድኃኒት፣ በደም ስር የሚሰጡ ፈሳሾች፣ ህመም ማስታገሻ መድኃኒቶች እጥረቶች ምክንያት በህሙማን ላይ የተወሳሰቡ ችግሮች ይፈጠራሉ። ያለ ምንም እርዳታ ሲሞቱ ትመለከታላችሁ። ዝም ብሎ መመልከት ብቻ ነው” በማለት ከትግራይ ዋና ከተማ መቀለ አንዳንዴ በሚገኘው የሳተላይት ኢንተርኔት ግንኙነትን በመጠቀም በዋትስ አፕ መልዕክታቸው የቀዶ ህክምና ባለሙያው ዶክተር ፋሲካ ተናግረዋል
ህሙማኑ አቅመ ቢስ ናቸው ነገር ግን የዶክተሮቹም ሁኔታ ከዚህ የራቀ አይደለም
ሆኖም በመቀለ ዓይደር ሆስፒታል የሚሰሩት ዶክተር ፋሲካ በትግራይ የተከሰተው ጦርነት በክልሉ የጤና አገልግሎት ላይ ያደረሰውን ተጽዕኖ ሲናገሩ ስሜት አይነበበብባቸውም።
ላለፉት ሁለት ዓመታት ትግራይ ከሌላው ዓለም ተነጥላ ትገኛለች።
ጥቅምት 24፣ 2013 ዓ.ም በትግራይ ጦርነት የተጀመረው የፌደራል ሰራዊቱ ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሐትን) ከስልጣን አስወግዶ ክልሉን ለመቆጣጠር መሞከሩን ተከትሎ ነው።
ህወሃት በመልሶ ማጥቃት እርምጃ ባለፈው ዓመት ሰኔ ወር ላይ አብዛኛውን የትግራይ ግዛቶች መልሶ መቆጣጠሩን ተከትሎ እገዳ ተጣለ።

የፎቶው ባለመብት, AFP
ይህንንም ተከትሎ በመሬት ላይ ያሉ አቅርቦቶች ቀጥ ብለዋል፤ የባንክ አገልግሎቶች ቆመዋል እንዲሁም የስልክ ግንኙነቶች በመቋረጣቸውን ለማንም ስልክ መደወል የማይቻል ነው።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በአሁኑ ወቅት ¾ኛው የሚሆነው 5.4 ሚሊዮን ህዝብ ጦርነቱ የምግብ አቅርቦቱን በማስተጓጎሉ እርዳታ ፈላጊ ሆኗል።
በጦርነቱ ውስጥ ቀጥተኛ ተሳትፎ ባይኖራቸውም ህሙማንም የገፈቱ ቀማሸ ናቸው።
በአለም ጤና ድርጅት እና በዓለም አቀፍ የቀይ መስቀል ኮሚቴ በኩል የተወሰኑ መድኃኒቶችና መሰረታዊ የህክምና መሳሪያዎች አልፎ አልፎ ጠብ ጠብ እያሉ መግባት ችለው ነበር።
ሆኖም የአምስት ወር ሰብዓዊ የተኩስ አቁም ስምምነት ፈርሶ ነሐሴ ወር ላይ ጦርነቱ ማገርሸቱን ተከትሎ አቅርቦቶች ሙሉ በሙሉ ቀጥ ብሏል።
“ለታካሚዎቻችን መድኃኒት የለንም፣ለቀዶ ህክምና የሚረዱ መሳሪያዎች የሉንም። ህፃናትን ለመክተብ ክትባት የለንም። ለስኳር ህመምተኞች የሚሰጠው ኢንሱሊንም የለንም” በማለት ያለፉት 16 ወራት ያስከተሉትን ተፅእኖ ለቢቢሲ ኒውስደይ ፕሮግራም ዶ/ር ፋሲካ ተናግረዋል።
“ሁሉም ዓይነት ህሙማን እየተሰቃዩ ነው። ህክምና ሳያገኙ ወደ ቤታቸው እንዲመለሱ እያደረግናቸው ነው”
የካንሰር ህሙማንን ለማከም የሚጠቅሙ መድኃኒቶች በፍፁም ሊገኙ አልቻሉም። የራዲዮ ቴራፒ መሳሪያም በአዲስ አበባ በመሆኑ ወደዚያም መጓዝ ስለማይቻልም በርካቶች እየተሰቃዩ ነው።
“በመሰረቱ የካንሰር ህሙማን እንዲሞቱ ተፈርዶባቸዋል” በማለት በአንድ ወቅት የህክምና ትምህርት ቤት ዲን የነበሩት የ41 ዓመቱ ዶክተር ፋሲካ ይናገራሉ።
“ታካሚዎች ጊዜ እያከተመባቸው ነው”
በኩላሊት ችግር ለሚሰቃዩ ህመምተኞች የዲያሊሲስ አቅርቦቶች መመናመናቸውን ተከትሎ የህክምና ባለሙያዎች ዝም ብለው ለመመልከት ተገድደዋል።
“የመጨረሻው መድኃኒት የገባው ሰኔ ወር ላይ ሲሆን ከነሐሴ ወር ጀምሮ ሙሉ በሙሉ በመታገዱ በሆስፒታላችን ላሉ 25 ህሙማን የሚሆን መድኃኒትና ቁሳቁስ በዚህ ሳምንት እያለቀብን ነው” ይላሉ ዶክተር ፋሲካ
90 የኩላሊት ታማሚዎች በዶክተሮች ፊት ሞተዋል እንዲሁም የተቀሩት 25 ሰዎች እጣ ፈንታቸው ምን እንደሆነ ግራ ገብቷቸዋል።
ምርመራን በሚመለከት የሆስፒታሉ ላቦራቶሪ ለምርመራዎቹ አስፈላጊ የሆኑ የኬሚካል ግብዓት የላቸውም። ይህም ማለት የህክምና ባለሙያዎቹ ታካሚዎች ሲመጡ ያለባቸውን ህመምም ማወቅ አይችሉም።
ይባስ ብሎ አስተማማኝ ያልሆነው የኤሌክትሪክ አቅርቦት እና ለጄነሬተሮች ነዳጅ ባለመኖሩ ሆስፒታሉ ለቀናት የኤሌክትሪክ ኃይል አያገኝም።
ዶክተር ፋሲካ እና የስራ ባልደረቦቻቸው እያስተናገዱት ያለው አስከፊ ሁኔታ የሰቆቃውን ክብደት አይገልፅም።
“ያለኝ ስሜት ሁሉ ጠፍቷል። ይኸው ነው እውነታችን ፤በየቀኑ የሚያጋጥሙኝን ነገሮች እየገለጽኩ ነው።
“ስሜታችንን በተወሰነ መልኩ እየጠበቅን ነው። ችግሩ እስካልተቀረፈ ድረስ ምን ያህል ሸክም እንደተጫነብን አናውቅም። በእንዲህ አይነት መከራ ውስጥ አለማሰብ ተፈጥሯዊ የመከላከያ ዘዴ ነው። ማድረግ ያለብንን እናደርጋለን። በማሰብና በማሰላሰል ጊዜያችንን አናሳልፍም።” ይላሉ።

የፎቶው ባለመብት, Fassika Amdeselassie
ዶክተሮቹ እና ነርሶች የፌደራሉ መንግሥት ሰራተኞች ቢሆኑም ካለፈው ዓመት ግንቦት ወር ጀምሮ ደመወዝ አልተከፈላቸውም። ዶክተር ፋሲካ በውጭ አገር ካሉ ወዳጅ ዘመዶቻቸው ገንዝብ ይላክላቸዋል ነገር ግን ገንዘብ የሚቀይሩ ሰዎች ወደ ትግራይ ለማሸጋገር ከፍተኛ ኮሚሽን ስለሚጠይቁ ዋጋ ያስከፍላል።
“ይህ ሆስፒታል ህይወቴ ነው” የሚሉት ዶክተር ፋሲካ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ቢገጥሟቸውም ሊበገሩ አልቻሉም።
“ሙያህ ይጠራሃል ። ህሙማንን አናግረህ መስጠት የምትችለውን ምክር ከለገስክና ማድረግ የምትችለውን ካደረግክ ዋናው እሱ ነው ። ይህ ለኔ ብቻ ሳይሆን ለሁሉም በተለያዩ የሙያ ዘርፎች ላይ ለተሰማሩ ነው “ ይላሉ።
በፌደራል መንግሥት እና በህወሓት መካከል ሊኖር የሚችለውን የሰላም ድርድር በተመለከተ ዶክተር ፋሲካ በፖለቲካው አስተያየታቸውን ከመስጠት ይቆጠባሉ።
ነገርግን የሰላም ንግግሮቹ የፖለቲካ ሂደት እንደ መሆናቸው መጠን የተለያዩ ወገኖች የተለያዩ ነገሮችን ማምጣታቸው የማይቀር መሆኑ ጋር ተያይዞ ስጋት ፈጥሯባቸዋል።
“የሰላም ንግግሮቹ ጊዜ ሊወስዱ ይችላሉ። ነገር ግን ህይወታችን ፣ የህፃናት እና የታካሚዎች ህይወት ያ ጊዜ ላይኖራቸው ይችላል። ስለዚህ በመጀመሪያ የሰብዓዊ ሁኔታዎችን ቅድሚያ እንዲሰጧቸው እመኛለሁ”
“የሰብዓዊ እርዳታ ህግ መከበር አለበት። በዩክሬን ተግባራዊ መሆን ከቻለ በትግራይ ለምን ተጣሰ? እኛ ጠቃሚ ሰዎች ስላልሆንንን ነው?” ዶክተሩ ይጠይቃሉ።












