በኢትዮጵያ እና በኤርትራ ድንበር አካባቢ በርካታ ጦር መከማቸቱን የሳተላይት ምስሎች አሳዩ

የፎቶው ባለመብት, MAXAR TECHNOLOGIES
የመገናኛ ዘዴዎች በተቋረጡበት፣ ጋዜጠኞች በአካባቢው ለመዘገብ ፈቃድ በተከለከሉበት እና በዓለም ስውር ጦርነቶች አንዱ በሆነው በኢትዮጵያ ሰሜናዊ ክፍል ትግራይ ክልል ውስጥ የሚካሄደውን ጦርነት በተመለከተ የሳተላይት ምስሎች ለየት ያለ ዕይታን ሰጥተዋል።
በባለፉት ሳምንታት ከሳተላይት የተነሱት ምስሎች ኢትዮጵያ ከኤርትራ ጋር በሚያዋስናት ድንበር ላይ የጦር ሠራዊት ክምችት እና መሳሪያዎች የተጠመዱባቸውን ቦታዎች አሳይተዋል።
የኤርትራ ጦር ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ጋር በመወገን ክልሉን ከሚቆጣጠረው ህወሓት ጋር ጦርነት ላይ መሆናቸው ይነገራል።
ከሰሞኑ ኤርትራ ተጠባባቂ ጦሯን ለክተት በማዝመት ትግራይ ውስጥ ማጥቃት መፈጸሟ ሪፖርት ተደርጓል።
በነሐሴ ወር ለአምስት ወራት ያህል የዘለቀው የሰብዓዊ የተኩስ አቁም ስምምነት ከፈረሰ በኋላ ጦርነቱ አገርሽቶ ውጊያው በተለያዩ ግንባሮች ቀጥሏል።
በሰሜን ኢትዮጵያ የተከሰተው የእርስ በርስ ጦርነት 13 ሚሊዮን የሚገመቱ ነዋሪዎችን እርዳታ ፈላጊ እንዳደረጋቸው የተባበሩት መንግሥታት የዓለም ምግብ ፕሮግራም ይፋ አድርጓል።
የመጀመሪያዎቹ የሳተላይት ምስሎች የተነሱት መስከረም 16/2015 ዓ.ም. በሰሜን ምዕራብ ትግራይ ውስጥ በምትገኘው ሽራሮ ከተማ ነው። ከተማዋ ቀደም ሲል በትግራይ ኃይሎች እጅ ነበረች።
ከላይ ያለው ምስል ከከተማዋ ወደ ምሥራቅ አቅጣጫ የሚወስደውን ዋና መንገድ ያሳያል።
ታንኮች ከታች በግራ በኩል ባለው ዋና መንገድ ላይ ተጠምደዋል።
በቀኝ በኩል የቀዶ ህክምና ክፍሎች፣ የማህጸን ህክምና፣ የኤክስሬይ መገልገያዎች እና 35 አልጋዎችን የያዘውና በአውሮፓውያኑ 2014 የተከፈተው የማይ አይኒ ሆስፒታል ይገኛል።
ቁጥራቸው ወደ 150 የሚጠጉ ሰዎች ምናልባትም ተዋጊዎች ከሆስፒታሉ መግቢያ እስከ ዋናው መንገድ ድረስ ተሰልፈው ወይም ወረፋ ይዘው ይታያሉ።
ባለፈው ዓመት ሆስፒታሉ ከፍተኛ ጉዳት እንደደረሰበት ዘገባዎች ጠቁመዋል።
የግብረ ሰናይ ድርጅቱ ድንበር የለሸ የሐኪሞች ቡድን ኤምኤስኤፍ ባለፈው ዓመት መጋቢት እንደገለጸው ማይ አይኒን ጨምሮ በትግራይ ክልል ውስጥ ያሉ የጤና ተቋማት “ሆን ተብሎና መጠነ ሰፊ በሆነ መልኩ ጥቃት፣ ዘረፋ እና ውድመት ደርሶባቸዋል” ብሏል።
የግብረ ሰናይ ድርጅቱ ሠራተኞች ከጎበኟቸው 106 የጤና ማዕከላት ውስጥ 13 በመቶው ብቻ በመደበኛነት እንደሚሰሩም ተመልክተዋል።
“አንዳንድ ዘረፋዎች አጋጣሚውን በመጠቀም የተፈጸሙ ቢመስሉም በክልሉ በአብዛኛዎቹ አካባቢዎች የሚገኙ የጤና ተቋማት አገልግሎት እንዳይሰጡ ሆን ተብለው የወደሙ ይመስላሉ” ብሏል ኤምኤስኤፍ።

የፎቶው ባለመብት, MSF
ቢቢሲ ከሽራሮ በስተምሥራቅ 95 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው የሽረ ከተማ አንድ ከፍተኛ የረድዔት ሠራተኛን አነጋግሯል።
ይህ ሠራተኛ ከነሐሴ 26/2014 ዓ.ም. ጀምሮ ወደ 210 ሺህ የሚጠጉ ነዋሪዎች ከሽራሮ እና አካባቢው ቀያቸውን ለቀው ወደ ሽረ መሰደዳቸውን ይናገራል።
“ነዋሪዎች የሽራሮ ከተማን ለቀው ከመፈናቀላቸው በፊት ከለአንድ ሳምንት ያህል በተከታታይ የከባድ መሳሪያ ድብደባዎች ነበሩ። ጥቃቱ ያለሟቀረጥ ለ24 ሰዓታት ይፈጸም ነበር” ሲልም ተናግሯል።
ደኅንነቱን ለመጠበቅ ሲባል የረድዔት ሠራተኛውን ማንነት ቢቢሲ አይገልፅም።
ከሽራሮ ተፈናቅለው የመጡ ነዋሪዎችና በሽራሮ ይሰሩ የነበሩ የረድዔት ሠራተኞችን ዋቢ አድርጎ ለቢቢሲ እንደተናገረው የማይ ዓይኒ ሆስፒታል በአሁኑ ወቅት በኤርትራ እና በኢትዮጵያ መንግሥት ወታደሮች ስር ይገኛል ብሏል።
መስከረም 03/2015 ዓ.ም. የመጨረሻው የሳተላይት ምስሎች ከመነሳታቸው በፊት የትግራይ ኃይሎች ዋና አዛዥ ጄኔራል ታደሰ ወረደ ለክልሉ መገናኛ ብዙኃን እንደተናገሩት “በሽራሮ የሚገኘው የኢትዮጵያ እና የኤርትራ ጦር ጥምር ኃይል ከሽራሮ እስከ አደመይቲ ያሉ ስፍራዎችን ተቆጣጥረዋል” ብለዋል።
በአሁኑ ወቅት የሽራሮ ከተማ በማን ቁጥጥር ስር እንደሆነች ግልፅ አይደለም፤ ለዚህም በሽረ የሚገኘው የረድዔት ሠራተኛ ሁኔታዎች ከቀን ወደ ቀን ተለዋዋጭ መሆናቸውን ለቢቢሲ ተናግሯል።
ከማይ ዓይኒ ሆስፒታል በስተደቡብ ከአንድ ኪሎሜትር ያነሰ ርቀት ላይ “የተጠመደ ከባድ መሳሪያ” ምስሎችን ማክሳር ቴክኖሎጂስ የተሰኘው የሳተላይት ኩባንያ ይፋ አድርጓል።
የተጠመደው መድፍ ያነጣጠረበት ኢላማ ምን እንደሆነ ግን ግልፅ አይደለም።

የፎቶው ባለመብት, MAXAR TECHNOLOGIES
የኢትዮጵያ እና የኤርትራ መንግሥት ጦራቸው በሽራሮ ስለመገኘቱ የሰጡት አስተያየት የለም።
ነገር ግን ባለፈው ሳምንት የአሜሪካ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ማይክ ሐመር ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት አገራቸው የኤርትራ ወታደሮች ወደ ኢትዮጵያ ድንበር ተሻግረው መግባታቸው እንዳሳሰባት እና “ሊቆም እንደሚገባም” አሳስበዋል።
“የኤርትራ ወታድሮች ድንበር አቋርጠው የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ ስንከታተል ነበር። የኤርትራ ጦር በኢትዮጵያ መገኘት ጦርነቱን ከማወሳሰብ ባሻገር አሳዛኝ የሆነውን ሁኔታ ወደከፋ ደረጃ ያደርሰዋል” ብለዋል ማይክ ሐመር።
ከሽራሮ ስድስት ኪሎ ሜትር ርቀት በሌላ አቅጣጫ ማክሳር ወደ 45 የሚጠጉና ረዘም ያለ ሰልፍ የያዙ ተሽከርካሪዎችን ምስል አሳይቷል። ከእነዚህ ተሽከርካሪዎች መካከል አውቶብሶች የሚገኙበት ሲሆን ወደ ከተማዋም የሚያቀኑ ይመስላል።

የፎቶው ባለመብት, MAXAR TECHNOLOGIES
በዚያው መንገድ አምስት ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ሌላ አነስተኛ ወደ 20 የሚጠጉ ወታደራዊ ተሽከርካሪካሪዎች እና አውቶብሶች አቅጣጫቸውን ወደ ሽራሮ አድርገው ነበር።
ይህ የአዲ ጎሹ መንገድ ከሽራሮ ተከዜን አቋርጦ ወደ ምዕራብ ትግራይዋ ትልቋ ከተማ ሁመራ የሚወስድ ሲሆን፣ በመጨረሻም 180 ኪሎ ሜትር ርቀት ወዳላት ኤርትራ የሚያገናኝ ነው። በመኪናም ሦስት ሰዓት ያህል ይፈጃል።

የፎቶው ባለመብት, MAXAR TECHNOLOGIES
ጦርነቱን ተከትሎ ምዕራብ ትግራይ በኤርትራ፣ በኢትዮጵያ፣ በአማራ ልዩ ኃይል እንዲሁም በአማራ ሚሊሻ ፋኖ ቡድን ቁጥጥር ስር ይገኛል።
የአማራ ክልል ምዕራብ ትግራይ የእኔ ግዛት ነው ይላል።
በዚህ ሽራሮ አካባቢ ከመንገድ ወጣ ያለ ቦታ ላይ የሳተላይት ምስሉ እንደሚያመለክተው ከዚህ ቀደም በአዲ ጎሹ መንገድ ላይ አንዳንድ ህንፃዎች አቅራቢያ እና መካከል የቆሙ ተመሳሳይ አይነት አውቶብሶች እና ተሽከርካሪዎች ናቸው።

የፎቶው ባለመብት, MAXAR TECHNOLOGIES
በማግሥቱ ጥዋት በስፍራው የነበሩትን ተሽካርካሪዎች የሳተላይት ምስሎቹ አያሳዩም። ይህም ተሽከርካሪዎቹ ወደ ሌላ ቦታ እንደተወሰዱ የሚጠቁም ነው።
ይህም ከሽረ የሸሹ ሰዎች በተገኘው መረጃ መሠረት በከተማዋ የተፋላሚ ኃይሎች መካከል እየተቀያየሩ መሆኑን ይጠቁማል።
ቢቢሲ የተመለከተው የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት የውስጥ ሰነድ እንደሚያሳየው መስከረም 14/2015 ዓ.ም. በሽራሮ እና አካባቢው በነበረው ጦርነት ቢያንስ 10 ሰዎች ተገድለዋል።
እንደ ረድዔት ሠራተኛው ሰነዱ ከዚህ ቀደም ከምዕራብ ትግራይ የተሰደዱ 45 ሺህ ተፈናቃዮችን ጨምሮ 210 ሺህ ሰዎች ቀያቸውን ለቀው እንደተሰደዱም አስፍሯል።
ማክሳር መስከረም 09/2015 ዓ.ም. ዕለት ከኢትዮጵያ ድንበር አንድ ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኛውና ከዛላምበሳ ከተማ በቅርብ ርቀት የምትገኘው የኤርትራዋ ሰርሃ ከተማ ዙሪያ የተነሱ ምስሎችን አውጥቷል።
እነዚህ ምስሎች በተወሰዱ በማግስቱ የትግራይ ባለሥልጣናት በሰጡት መግለጫ የኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ “የኤርትራን መላ የጦር ሠራዊት፣ የተጠባባቂ ኃይሎቹን እና ሚሊሻዎችን በማሰባሰብ በዛላምበሳ በኩል ከፍተኛ ጥቃት ፈፅመዋል” እንዲሁም በሌሎችም አካባቢዎችም ጥቃት መፈጸሙን ተናግረዋል።
ማክሳር ይህንን ኤም 46 የተሰኘው ከባድ መሳሪያ ከሰርሃ ከተማ በስተሰሜን ተጠምዶ እንደሚገኝ ገልጿል።

የፎቶው ባለመብት, MAXAR TECHNOLOGIES
ወደ ደቡብ ትንሽ ራቅ ብሎ ባለ በመካነ መቃብር አጠገብ ማክሳር ይህንን ኤስ ኤስ ፒ ሃዊቲዘር የተሰኘውን ከባድ መሳሪያ መለየት ችሏል። መሬቱ ላይ ያሉትና ስፍራቸውን እየያዙ ያሉ ተሽከርካሪዎች ከምስሉ በስተግራ በኩል በግልፅ ይታያሉ።

የፎቶው ባለመብት, MAXAR TECHNOLOGIES
ወደ ኢትዮጵያ ድንበር በጣም ተጠግቶ ማክሳር ዋና የጦር ታንክ መሰማራቱን አይቷል። እነዚህ ስፍራዎች ከድንበሩ አንድ ኪሎሜትር ርቀት ላይ የሚገኙ ሲሆን በ15 ደቂቃ የእግር መንገድም ወደ ኢትዮጵያ መግባት ይቻላል።

የፎቶው ባለመብት, MAXAR TECHNOLOGIES

የፎቶው ባለመብት, MAXAR TECHNOLOGIES












