በአረብ ኤምሬቶች የጠፉት የአይሁድ ሃይማኖት መምህር መገደላቸውን አስራኤል አስታወቀች

የፎቶው ባለመብት, Chabad
የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ውስጥ ጠፍተዋል የተባሉት አይሁድ እምነት መምህርት ወይም ራባይ መገደላቸውን እስራኤል ገለጸች።
ዝቪ ኮጋን የተባሉት የአይሁድ እምነት መምህርት መገደል ከታወቀ በኋላ እስራኤል የራባዩን ገዳዮቹን እንደምትፋረድ ቃል ገብታለች።
የሃይማኖት መምህሩ አስክሬን መገኘትን ተከትሎ “የዝቪ ኮጋን የግድያ ወንጀል ፀረ ሴማዊ የሽብር ድርጊት ነው። የእስራኤል መንግሥት ለሞቱ ተጠያቂ የሆኑትን ወንጀለኞች ለፍርድ ለማቅረብ ያለውን አቅም ሁሉ ተጠቅሞ እርምጃ ይወስዳል” ሲል የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ገልጿል።
ከግድያው ጋር በተያያዘ ሦስት ሰዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የተባበሩት አረብ ኢምሬቶች የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር እሑድ ማምሻውን አረጋግጧል።
የአይሁድ ድርጅት የሆነው የቻባድ ሉባቪች ባልደረባው ራባይ ኮጋን ከሐሙስ ጀምሮ ዱባይ ውስጥ መጥፋታቸው ከተገለጸ ጀምሮ የእስራኤል የስለላ ድርጅት ሞሳድ እና የተባበሩት አረብ ኢምሬቶች ባለሥልጣናት ምርመራ ጀምረዋል።
ከጠፉበት ጊዜ ጀምሮ የእስራኤል ባለሥልጣናት ከእስራኤል-ሞልዶቫዊ ቤተሰብ ጋር ሲገናኙ እንደነበር የእስራኤል መግለጫ አክሎ አስታውቋል።
የዝቪ ኮጋን አስከሬን የተገኘው መኪናቸው ከመኖሪያ ቤታቸው የአንድ ሰዓት የመኪና መንገድ ርቆ ከተገኘ በኋላ ነው።
የእስራኤል ፕሬዝዳንት አይዛክ ሄርዞግ ግድያውን “አሳፋሪ ፀረ ሴማዊ ጥቃት” ብለውታል።
የሞሳድ መርማሪዎች ለራባዩ ሞት ተጠያቂ የሆኑትን ለመለየት እየሠሩ ነው።
ቻባድ ከዓለማዊ አይሁዶች ወይም ከሌሎች የአይሁድ እምነት ተከታዮች ጋር ግንኙነት ለመፍጠር የሚፈልግ ሃይማኖታዊ ተቋም ነው።
በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች የሚገኘው የተቋሙ ቅርንጫፍ በሺዎች የሚቆጠሩ አይሁዳውያን ጎብኚዎችን እና ነዋሪዎችን ይደግፋል ሲል በድረ-ገጹ ላይ ሰፍሯል።
የ28 ዓመቱ ራባይ ኮጋን ከሌሎች የቻባድ አባላት ጋር “በኤምሬቶች ውስጥ የአይሁዶችን ሕይወት በማቋቋም እና በማስፋፋት” ሠርቷል ሲል ድርጅቱ ገልጿል። በዱባይ የአይሁዳውያን ምግብ እና ቁሶች የሚሸጠው ‘የኮሸር ሱፐርማርኬትም’ አስተዳድረዋል ሲል አክሏል።
“የተባበሩት አረብ ኢምሬቶች ወንጀለኞችን ለፍርድ ለማቅረብ ከአካባቢው አገራት ጋር እንደምትሠራ እናምናለን። በዚህ አስከፊ እኩይ ተግባር የተሳተፉትን ሁሉ ተጠያቂ እንደምታደርግ እናምናለን” ሲሉ የቻባድ ሉባቪች ሊቀመንበር የሆኑት ራባይ ይሁዳ ክሪንስኪ ተናግረዋል።
የእስራኤል መንግሥት ዜጎቹ ወደ ተባበሩት አረብ ኢምሬቶች “በቂ ምክንያት ካላቸው ብቻ” አንዲጓዙ ሲል የጉዞ ማሳሰቢያ ካወጣ ሰነባብቷል።
በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ውስጥ “የሽብር ተግባር” ስላለ “በአገሪቱ ውስጥ ለሚቆዩ/ለሚጎበኙ እስራኤላውያን አደጋ ይኖረዋል” ሲሉ አክሏል።
አቡ ዳቢ ከእስራኤል ጋር መደበኛ ግንኙነት የመሠረተችው በአሜሪካ አደራዳሪነት በተደረገው ስምምነት ሲሆን የአብርሃም ስምምነት በመባልም ይታወቃል።
አንድ ዓመት ያለፈው እና በርካታ ተቃውሞ እየገጠመው ያለው እስራኤል በጋዛ ከሐማስ ጋር እያካሄደቸው ያለው ጦርነት በቀጠለበት በአሁኑ ወቅትም ግንኙነቱ ቀጥሏል።












