ሱዳን የከሸፈች አገር የመሆን ስጋት ላይ ናት ሲሉ የረድዔት ኃላፊ አስጠነቀቁ

ሱዳናዊ ሴት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በእርስ በርስ ጦርነት እየታመሰችው ያለችው ሱዳን ሌላ የከሸፈች አገር የመሆን ስጋት ላይ ናት ሲሉ አንድ የዓለም አቀፍ የረድዔት ድርጅት ኃላፊ ለቢቢሲ ተናገሩ።

በአገሪቱ ያሉ የሲቪል ማህበረሰብ በታጣቂ ኃይሎች እየፈራረሱ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በሱዳን ውስጥ ያሉት ዋነኛ ተፋላሚዎች የጦር ሰራዊቱ እና የፈጣን ደራሽ ኃይሉ እንዲሁም በርካታ አነስተኛ ታጣቂ ቡድኖች በሰላማዊ ነዋሪዎች ላይ መጠነ ሰፊ ዘረፋዎችን እየፈጸሙ ነው ሲሉ የኖርዌይ የስደተኞች ምክር ቤት (ኤንአርሲ) ኃላፊ ጃን ኤጌላንድ ገልጸዋል።

“ታጣቂዎቹ የራሳቸውን እና የህዝባቸውን ቤቶች እያወደሙ ነው። ወገኖቻቸውን እየጨፈጨፉ ነው” ብለዋል።

ለአስራ ዘጠኝ ወራት በዘለቀው የሱዳን የጦር ሰራዊት እና ፈጥኖ ደራሽ ኃይል የሚደረገው የስልጣን ሽኩቻ ጦርነት ከ10 ሚሊዮን በላይ ነዋሪዎች ተፈናቅለዋል። እንዲሁም በርካቶች ለረሃብ እንዲጋለጡ ምክንያት ሆኗል።

“በአሁኑ ወቅት ሱዳን በዓለማችን ከፍተኛው የሰብዓዊ አደጋ የተጋረጠበት፣ ከባድ ረሃብ እንዲሁም ከፍተኛ የህዝብ ቁጥር የሚፈናቀልበት መሆኑን አይቻለሁ” ሲሉ ሱዳንን ከጎበኙ በኋላ ኃላፊው ተናግረዋል።

የዓለም የጤና ድርጅት በሱዳን ረሃብ “በሁሉም ስፍራዎች ተንሰራፍቷል” ሲል መስከረም ወር ላይ አስጠንቅቆ ነበር።

በሱዳን የረድዔት ድርጅቶች በገንዘብ ድጋፍ እጥረት ምክንያት ስራቸውን ለመቋረጥ ተገደዋል። በአገሪቷ ያለው የሰብዓዊ እርዳታ መታጣት ከፍተኛ ቀውስ መፍጠሩን ኃላፊው ገልጸዋል።

“በርካቶች በረሃብ አለንጋ እየተገረፉ ነው” ያሉት ኃላፊው ረሃብ በጦር መሳሪያነት ጥቅም ላይ እየዋለ መሆኑን አስጠንቅቀዋል።

አንዳንድ የረድዔት ድርጅት በአውሮፓውያኑ ዓመት መጨረሻ 2.5 ሚሊዮን ሰዎች በረሃብ ሊሞቱ ይችላሉ የሚል ስጋት አላቸው። ዓለም በቂ ባለማደረጉ “ሱዳን ሙሉ በሙሉ በውድቅት ጎዳና” ላይ ናት ሲሉ ኤግላንድ አስጠንቅቀዋል።

አውሮፓ የስደተኞችን ቀውስ ለማስወገድ ከፈለገች በተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች በ“እርዳታ፣ ጥበቃ እና ሰላም” ኢንቨስት ልታደርግ ይገባል ብለዋል።

“የዓለማችን ትልቁ አደገኛ ቀውስ ቢሆንም በገንዘብ ደረጃ አነስተኛ ድጋፍ የሚደረግበት ነው” ብለዋል።

የሱዳን የእርስ በርስ ጦርነት በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ቀጥፏል። በሱዳን የዘር ማጽዳትና የዘር ማጥፋት ወንጀሎች መፈጠሩን የመብት ተሟጋች ድርጅቶች እየገለጹ ይገኛሉ። የሰብዓዊ ቀውሱ ከፍተኛ ቢሆንም በጦሩ እና በፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ መካከከል ግጭትን በዘላቂነት ለመቋጨት የተደረጉ ድርድሮች ፍሬ አልባ ሆነዋል።

“ጦርነቱ የሚቆመው እነዚህ የጦር አበጋዞች ውጊያውን በመቀጠላቸው ኪሳራ እንደሚያደርስባቸው ሲሰማቸው ነው” ሲሉ ኤጌላንድ ገልጸዋል።