ዋይፋይ ካንሰር ያመጣል የሚሉት እና ክትባቶችን የሚጠራጠሩት የትራምፕ ዕጩ የጤና ሚኒስትር

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ሮበርት ኤፍ ኬኔዲ ጁኒየር አሊያም በምህፃሩ አርኤፍኬ ጁኒየር ይባላሉ። አሜሪካውያን የሚበሉትን እና የሚጠጡትን እንዲመርጡ ለማድረግ ትልቅ ዕቅድ ነድፈዋል።
ፍሩት ሉፕስ የተባለው አሜሪካውያን ቁርስ ላይ ከሚመገቡት ምግብ እስከ ቺክን ነጌትስ የተባለው የዶሮ ጥብስ በአርኤፍኬ ዘመን ጉዳቸው የሚፈላ ይመስላል።
ተመራጩ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ የጤና ሚኒስትራቸው አድርገው አጭተዋቸዋል። ሰውዬው አሜሪካውያን የሚበሉት እና የሚጠጡት ጤናማ አይደለም በማለት ብዙ ጊዜ ሲናገሩ ይሰማሉ።
“በኢንዱስትሪ የተበከለ ምግብ በማብላት ልጆቻችን እየገደልናቸው” ሲሉ ባለፈው ኅዳር ተናግረው ነበር። በግላቸው ፕሬዝደንት ለመሆን ሞክረው ስላልተሳካላቸው ነው ለዶናልድ ትራምፕ ድጋፋቸውን የሰጡት።
ነገር ግን ኬኔዲ አሜሪካውያን የሚበሉትን እና የሚጠጡትን ከመቀየራቸው በፊት የምግብ ቁጥጥሩን ማጥበቅ አላቸው። ይህ ማለት ደግሞ ከግዙፍ ምግብ አምራች ኩባንያዎች ጋር ሊጋጩ ይችላሉ ማለት ነው።
“ግዙፉን የምግብ ኢንዱስትሪ እጋፈጣለሁ ነው የሚሉት” ይላሉ የኒው ዮርክ ዩኒቨርሲቲ የሥነ ምግብ ፕሮፌሰር የሆኑት ማሪዮን ኔስል።
“ትራምፕ ይህን ሲያደርጉ ዝም ብለው ያያሉ? እሱን ሳየው ነው የማምነው።”
አርኤፍኬ ጁኒዬር የተፈጥሮ ሀብት ጠበቃ ነበሩ። የአሜሪካ ሕግ መወሰኛ ምክር ቤት (ሴኔት) ሹመታቸውን ካፀደቀው ቀጣዩ የአሜሪካ የጤና ሚኒስትር ይሆናሉ።
ሰውዬው በብዙዎች ዘንድ አከራካሪ የሆኑት ሐሳቦችን በማንሳት ይታወቃሉ። ስለጤና መሠረተ ቢስ አስተያየቶችን ይሰጣሉ። ክትባት ኦቲዝም ያመጣል፤ የዋይፋይ ቴክኖሎጂ ካንሰር ያስከትላል ብለው ያምናሉ።
ቢሆንም የአሜሪካ የምግብ እና መድኃኒት ቁጥጥርን ለመቀየር ያመጡት ሐሳብ በጤና ባለሙያዎች ዘንድ ተቀባይነት ያገኘ ይመስላል። ሕግ አውጪዎች እና ተጠቃሚዎች እንዲሁም አንዳንድ ዲሞክራቶች ድጋፋቸውን ገልፀዋል።
“ኬኔዲ የጤና ሚኒስቴር እና የምግብና መድኃኒት ቁጥጥር ባለሥልጣንን አፍርሰው በመሥራት አሜሪካውያን ድጋሚ ጤናማ እንዲሆኑ ያደርጋሉ የሚል እምነት አለኝ” ይላሉ ዲሞክራቱ የኮሎራዶ ግዛት ገዢ ጃሬድ ፖሊስ በማኅበራዊ ሚዲያቸው ላይ በለጠፉት መልዕክት።
አሜሪካን ድጋሚ ጤናማ ማድረግ
በእንግሊዝኛው ‘ሜካ አሜሪካ ሄልዚ ኧጌይን’ አሊያም አሜሪካን ድጋሚ ጤናማ እናድርጋት በተሰኘው መሪ ቃላቸው ነው የሚታወቁት። ኬኔዲ አሁን የሪፐብሊካን ፓርቲው ዶናልድ ትራምፕ አጋር ከመሆናቸው በፊት ዲሞክራት ነበሩ።
ፋብሪካ ውስጥ ተብላልተው የሚወጡ ምግቦች ከገበያ እንዲጠፉ ይፈልጋሉ። እነዚህ ምግቦች ስብ እና ስኳር የሚጨመርባቸው በረዶ ውስጥ የሚቀመጡ ፒዛዎች፣ የድንች ጥብስ፣ የቁርስ ምግቦች ከካንሰር፣ ከልብ ህመም እና ከስኳር በሽታ ጋር ይይዛሉ።
በተለይ ደግሞ ለተማሪዎች የሚቀርቡ ምሳዎች ላይ ዒላማቸውን አድርገዋል። “የአሁኑ ትውልድ በጣም መርዛማ የሆነ ሾርባ ውስጥ ነው” ሲሉ ፎክስ ኒውስ ለተባለው የቴሌቪዥን ጣቢያ ተናግረው ነበር።
ኬኔዲ በጤና ሚኒስትርነታቸው የምግብ እና መድኃኒት ቁጥጥር ባለሥልጣንንም ይቆጣጠራሉ። ይህ መሥሪያ ቤት 18 ሺህ ሠራተኞች አሉት።
መሥሪያ ቤቱ የመድኃኒት ምርቶችን እና ምግብ አቅራቢዎችን የሚቆጣጠር ነው። ነገር ግን ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ባለሥልጣኑ በምግብ ቁጥጥር ዙሪያ ግልፅ የሆነ አሠራር አይከተልም የሚል ትችት ከብዙዎች ዘንድ እያስተናገደ ይገኛል።
የ70 ዓመቱ ዕጩ የጤና ሚኒስትር መሥሪያ ቤቱን በለውጥ ጎዳና እንደሚያራምዱት እና “ሙሰኛ የሆኑ” ሠራተኞችን እንደሚባርሩ ቃል ገብተዋል።
ጤናማ አይደሉም የሚባሉ ምግብ ላይ የሚጨመሩ ቀለሞችን እና በሌሎች ሀገራት የታገዱ ኬሚካሎችን ለማስወገድም አስበዋል።
አክለው ፍሎራይድ ከመጠጥ ውሀ ሊታገድ ይገባል እንዲሁም ያልፈላ ወተት ለጤና ጠቃሚ በመሆኑ ለባክቴሪያ ብክለት ቢያጋልጥም መጠጣት አለበት ይላሉ።
በማኅበራዊ ሚዲያ ገፃቸው ላይ ባሰፈሩት መልዕክት ደግሞ የምግብ ዘይቶችን እንደሚቃኙ ጠቁመው አሜሪካውያን ከሱፍ በሚመረቱ የምግብ ዘይቶች “ሳያውቁት እየተበከሉ ነው” ብለዋል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
መረጃዎች ምን ይላሉ?
በርካታ የጤና ባለሙያዎች ኬኔዲ ፋብሪካ ውስጥ የተቀናበሩ ምግቦች ከገበያው መወገድ አለባቸው ብለው የሚያነሱትን ሐሳብ ይቀበላሉ።
አንዳንድ የአሜሪካ ግዛቶች ከኬኔዲ አስቀድመው ምግብ ላይ የሚጨመሩ ኬሚካሎችን አግደዋል።
በሺዎች የሚቆጠሩ ምግብ ውስጥ የሚጨመሩ ቀለሞች እና ኬሚካሎች አሜሪካ ውስጥ ቢፈቀዱም በአውሮፓ ኅብረት ሀገራት የተከለከሉ ናቸው።
ምንም እንኳ ኬኔዲ ይህ ዕቅዳቸው በብዙዎች ዘንድ ተቀባይነት ቢያገኝም አንዳንድ ሐሳቦቻቸው ግን አሁንም ትችት እያስተናገዱ ናቸው።
ለምሳሌ ያልፈላ አሊያም ፓስቸራይዝ (ባክቴሪያ መግደያ መንገድ) ያልተደረገ ወተት ለጤና ጠቃሚ ነው ማለታቸው አከራካሪ ሆኗል። ያልፈላ ወተት ለህመም ሊያጋልጥ አልፎም ለሞት ሊዳርግ እንደሚችል ጥናቶች ይጠቁማሉ።
ኬኔዲ ፍሎራይድ ከመጠጥ ውሀ መወገድ አለበት ብለው ያረቀቁት ሐሳብም ተቃውሞ ገጥሞታል። ፍሎራይድ ማለት የመጠጥ ውሀ ውስጥ የሚገኝ ኬሚካል ሲሆን፣ ለጥርስ ጤና ጠቃሚ መሆኑ ይታወቃል።
አርኤፍኬ እኒህን ለውጦች እውን ለማድረግ ብዙ ርቀት መጓዝ ይጠበቅባቸዋል። ግዙፍ የሚባሉት የምግብ አምራች ኩባንያዎች ተቃውሟቸውን ማሰማታቸው የማይቀር ነው።















