አዲሷ የትራምፕ የጽህፈት ቤት ኃላፊ ማን ናቸው?

አዲሷ የጽህፈት ቤት ኃላፊ ሱዛን ዋይልስ ከተመራጩ ፕሬዚዳንት ትራምፕ ጋር

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, አዲሷ የጽህፈት ቤት ኃላፊ ሱዛን ዋይልስ ከተመራጩ ፕሬዚዳንት ትራምፕ ጋር

ተመራጩ 47ኛው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት በይፋ ሥልጣን ከመረከባቸው በፊት ሹመኞቻቸውን መምረጥ ጀምረዋል።

ትራምፕ የምርጫ ቅስቀሳቸው ኃላፊ የነበሩትን ሱዛን ሳመርል ዋይልስ ጥር ወር ለሚረከቡት ዋይት ሐውስ የጽህፈት ቤት ኃላፊ ሆነው እንዲያገለግሉ መርጠዋቸዋል።

እሳቸውን ለምን እንደመረጧቸውም ትራምፕ ሲያስረዱ “በአሜሪካ ታሪክ ውስጥ ታላላቅ የፖለቲካ ድሎች ከሆኑት አንዱን እንዳሳካ ረድታኛለች” ብለዋል።

አክለውም ሱዛን “ጠንካራ፣ ብልህ፣ የፈጠራ ሰው እንዲሁም በሁሉም የምትደነቅ እና የምትከበር ናት” ሲሉ አሞካሽተዋቸዋል።

በአሜሪካ ታሪክ የመጀመሪያዋ የዋይት ሐውስ ጽህፈት ቤት ሴት ኃላፊ መሆናቸው የሚገባቸው እንደሆነ የተናገሩት ትራምፕ “አገራችንን እንደምታኮራ አልጠራጠርም” ብለዋል።

የ67 ዓመቷ ሱዛን ዋይልስ የመጀመሪያዋ የዋይት ሐውስ የጽህፈት ቤት ኃላፊ በመሆን ታሪክ ሠርተዋል።

ከጥር 12 በኋላ በይፋ ፕሬዚዳንት ሆነው አገሪቷን የሚመሩት ትራምፕ የውጭ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ እና የመከላከያ ሚኒስትርን ጨምሮ 15 ከፍተኛ የሪፐብሊካን ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚዎቻቸውን ለመምረጥ የሽግግር ቡድናቸው ሥራውን ጀምሯል።

ትራምፕ በዚህ ሳምንት ድል መቀዳጀታቸውን አስመልክቶ ንግግር በሚያደርጉበት ወቅት ሱዛን በመድረኩ ላይ ከኋላቸው ቆመው ታይተዋል።

ትራምፕም በዚሁ ወቅት “ብረቷ ሴት” ሲሉ ነው ያወደሷቸው።

ሱዛን በአብዛኛው ተግባራቸውን የሚያከናውኑት “ከኋላ ሆና ነው” ሆኖም “በአሜሪካ ውስጥ እጅጉኑ ከሚፈሩ ፖለቲከኞች አንዷ መሆኗ የታወቀ ነው” ሲሉ ተመራጩ ፕሬዚዳንት ገልጸዋል።

“ሱዚ አሜሪካን ዳግም ታላቅ የማድረግ ሥራን ያለመታከት መሥራቷን ትቀጥላለች” በማለትም ተደጋጋሚ መፈክራቸውን በመጠቀም ገልጸዋቸዋል።

አዲሷ የጽህፈት ቤት ኃላፊ ሱዛን

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, አዲሷ የጽህፈት ቤት ኃላፊ ሱዛን

ሱዛን ዋይልስ ማን ናቸው?

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የፖለቲካ ሁነቶችን በመተንተን የሚታወቀው ፖለቲኮ የተሰኘው የአሜሪካው ጋዜጣ ሱዛን ዋይልስን ሲገልጻቸው “የሚፈሩ ነገር ግን ብዙም የማይታወቁ” ሲል ነው።

ሱዛን የፖለቲካ መድረኩን በተቀላቀሉ አንድ ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ነው ከአውሮፓውያኑ 1980 ምርጫ በፊት የቀድሞውን ፕሬዚዳንት ሮናልድ ሬጋንን የምርጫ ቅስቀሳ ዘመቻ የተቀላቀሉት።

ሱዛን፣ መኖሪያቸው የሆነችውን የፍሎሪዳ ግዛትን ፖለቲካ ሂደትን በመቀየር ቁልፍ ሚና እንደተጫወቱ ይነገርላቸዋል።

በአውሮፓውያኑ 2010 ብዙም የፖለቲካ ልምድ የሌላቸውን እና ነጋዴውን ሪክ ስኮት በሰባት ወራት ውስጥ የፍሎሪዳ ገዥ እንዲሆን አስችለዋል - ሱዛን። ስኮት በአሁኑ ወቅት የአሜሪካ ሴናተር ናቸው።

ሱዛን እና ትራምፕ ትውውቃቸው በአውሮፓውያኑ 2015 ነበር። በቀጣዩ ዓመት በተደረገው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ የፍሎሪዳ የቅስቀሳ ዘመቻ ተባባሪ ኃላፊ ነበሩ። በአውሮፓውያኑ 2016 በተደረገው ምርጫ በዚህች ግዛት ላይ ትራምፕ፣ ሂላሪ ክሊንተንን መርታት ቻሉ።

ከሁለት ዓመት በኋላ ለፍሎሪዳ ገዢነት ሲወዳደሩ ለነበሩት ሮን ዴ ሳንቲስ የምርጫ ቅስቀሳ ኃላፊ ሆነው መርተዋል።

የግዛቲቷ ገዢነትንም በተሳካ ሁኔታ ያሸነፉት ሮን ዴ ሳንቲስ ሱዛንን “ካሉት ምርጧ” ሲል ነበር የገለጿቸው።

ሱዛን በአሁኑ የትራምፕ የምርጫ ቅስቀሳ ዘመቻ ላይ ለበርካታ አስርት ዓመታት ልምድ ካላቸው አንጋፋው የሪፐብሊካን ፖለቲከኛ ክሪስ ላቪታ ጋር ነው አብረው የሠሩት።

ሁለቱ ፖለቲከኞች ፕሬዚዳንቱን አሸናፊ ያደረጋቸውን ስትራቴጂ ከትራምፕ ጋር አብረው ነድፈዋል።

የ67 ዓመቷ ሱዛን በፖለቲኮ ላይ የሰፈረው የሕይወት ታሪካቸው እንደሚያሳየው አያት ናቸው።

አባታቸው የቀድሞው እግር ኳስ ተጫዋች እና ጋዜጠኛ የነበሩት ፓት ሰመራል ሲሆኑ፣ ቤተሰባቸውም በፖለቲካ ዕይታ የተቃኘ እንደሆነ ተናግረዋል።

“በመጀመሪያ የሥራዬ ዘመን እንደ ሥነ ምግባር እና መልካም ባህርይ ያሉ ጉዳዮች አስፈላጊ ነበሩ” ያሉት ሱዛን የሪፐብሊካን ፓርቲ ከበርካታ አስርት ዓመታት በፊት ከነበረው በእጅጉ የተለየ እንደነበር ያስረዳሉ።

“የዛሬው ሪፐብሊካን ፓርቲ የተለየ እንደሆነ ተረድቻለሁ” የሚሉት ሱዛን ከለውጡ ጋር መሄድ እንደሚገባም ገልጸዋል።

የዋይት ሐውስ ጽህፈት ቤት ኃላፊ የፕሬዚዳንቱ ከፍተኛ ረዳት እንደሆነ የሚታሰብ ሲሆን፣ በፕሬዚዳንቱ አስተዳደር ውስጥ ወሳኝ እና መሠረታዊ ሚናን ይጫወታሉ።

በሌላ ቃል ሲገለጽ የዋይት ሐውስ ሥራ አስኪያጅ ሆነው የሚያገለግሉ ሲሆን፣ የፕሬዚዳንቱን ሠራተኞች የማሰባሰብ ኃላፊነት በእሳቸው ላይ ተጥሏል።

የጽህፈት ቤት ኃላፊው ሠራተኞቹን በፕሬዚዳንቱ ሥራ አስፈጻሚ ጽህፈት በኩል የሚመራ ሲሆን፣ ሁሉንም የዕለት ተዕለት ተግባራት እና የሠራተኞችን እንቅስቃሴዎችም ይቆጣጠራሉ።

በተጨማሪም ፕሬዚዳንቱን በፖሊሲ ጉዳዮች ላይ ይመክራሉ እንዲሁም ፖሊሲን የመምራት እና የመቆጣጠር ኃላፊነትም በጽህፈት ቤት ኃላፊው ትከሻ ላይ ያረፈ ነው።