ቢሊየነሩ መስክ የመንግሥትን ብቃት የሚገመግም መስሪያ ቤት ኃላፊነት ሹመት ተሰጠው

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የተመራጩ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ የምርጫ ቅስቀሳ የጀርባ አጥንት የሆነው ቢሊየነሩ ኤለን መስክ የመንግሥትን ብቃት የሚገመግም አዲስ መስሪያ ቤት የኃላፊነት ሹመት ተሰጠው።
ተመራጩ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ኤለን መስክ ለሪፐብሊካን እጩ ፕሬዚዳንትነት ተወዳድረው ከነበሩት ቪቬክ ራምስዋሚ ጋር በጋራ ይህንን መስሪያ ቤት ይመራሉ ብለዋል።
መስሪያ ቤቱ በዋነኝነት የመንግሥት ቢሮክራሲን ለማስወገድ እና ወጪን በመቀነስ ላይ ከመንግሥታዊ ስራ ውጭ ምክር እና መመሪያ ይሰጣል ተብሏል።
መስሪያ ቤቱ መንግሥታዊ ሚና የለውም የተባለ ሲሆን ምን አይነት ቅርጽ እንደሚኖረው እስካሁን ግልጽ አልሆነም።
ተመራጩ ፕሬዚዳንት ትራምፕ የፎክስ ኒውስ አቅራቢውን ፒት ሄግስትን የመከላከያ ጸሓፊ እንዲሁም ጆን ራትክሊፍን የብሔራዊ መረጃ ዳይሬክተር አድርገው መርጠዋል።
ኤለን መስክ በመንግሥት ብቃት እና የበጀት ቅነሳ ላይ ለመስራት ፍላጎት እንዳለው ከዚህ ቀደም በተደጋጋሚ ተናግሮ ነበር።
ባለፈው ወር በኒውዮርክ ተካሂዶ በነበረ የትራምፕ የምርጫ ቅስቀሳ ላይ 6.5 ትሪሊየን ከሆነው የአሜሪካ አጠቃላይ የመንግሥት በጀት ምን ያህል አካባቢ መቀነስ ይቻላል ብሎ እንደሚያስብ ተጠይቆ ነበር።
መስክ በምላሹ “ ቢያንስ 2 ትሪሊየን መቀነስ የምንችል ይመስለኛል። ገንዘባችሁ በከንቱ እየባከነ ነው የመንግሥት ብቃት ክፍል ይህንን ያስተካከላል” ብሏል።
በቅርቡም በኤክስ ላይ በለጠፈው ጽሁፍ “በመንግሥት ውስጥ ከፍተኛ ማባከን እና አላስፈላጊ ቁጥጥር ያለ ሲሆን ይህ ሊወገድ ይገባል” ሲል መልዕክቱን አስተላልፎ ነበር።
አክሎም “እርምጃ ካልተወሰደ በስተቀር የፌደራል መንግሥት ወጪ አገሪቱን ባዶ ካዝና ያደርጋታል” ብሏል።
መስክ መንግሥት የሚቀጥራቸውን ሰዎች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ እንዲቀንስ በተደጋጋሚ ምክር በመስጠት ይታወቃል።
የዓለማችን ቁጥር አንድ ባለጸጋ የሆነው ኤለን መስክ የትራምፕ የስልጣን ሽግግርን የሙሉ ጊዜ ስራው እንዳደረገው ሪፖርቶች ወጥተዋል።
ተመራጩን ፕሬዚዳንት በካቢኔ ሹመት ላይ ከመምከር በተጨማሪ ባለፈው ሳምንት በነበረው የትራምፕ እና የዩክሬኑ ፕሬዚዳንት ቮሎድሚር ዘለንስኪ ውይይት ተገኝቶ ነበር።
መስክ የትራምፕን ፕሬዚዳንታዊ የምርጫ ቅስቀሳ ዘመቻ ለማገዝ ወደ 200 ሚሊዮን ዶላር ወጪ አውጥቷል።












