ቀጣዩ ጄምስ ቦንድ ማን ሊሆን ይችላል?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images/BBC
በሆሊውድ የፊልም ታሪኮች ውስጥ ገናና ከሆኑ ገጸ ባህርያት አንዱ ጄምስ ቦንድ ነው።
አቻ የሌለው ሰላይ፣ ጠላቶቹን የገቡበት ገብቶ የሚያጠፋ ጀግና ተደርጎ በመሳል ከስድስት አስርት ዓመታት በላይ ታይቷል።
ጄምስ ቦንድ በብሪታንያዊው ደራሲ ኢያን ፍሌሚንግ በአውሮፓውያኑ 1953 የተፈጠረ ገጸ ባሕርይ ነው።
ለዩናይትድ ኪንግደም (ዩኬ) የስለላ ድርጅት ኤምአይ ሲክስ በኮድ ስም 007 (ደብል ኦ ሰቨን) ተብሎ የሚጠራው ጄምስ ቦንድ በሃያ አምስት የፊልም ፕሮዳክሽኞች ላይ ታይቷል።
በመጀመሪያ ፊልሙ ለዕይታ በበቃበት አውሮፓውያኑ 1962 ታዋቂው የፊልም ተዋናይ ሾን ኮነሪ ጄምስ ቦንድ ሆኖ ብቅ አለ።
ለቀጣዩ አስር ዓመት ገደማ ሾን ኮነሪ እና ጄምስ ቦንድ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታ በሚመስሉበት ሁኔታ ተጣምረው ቀርበዋል።
ከሾን ኮነሪ በመቀጠል ለዓመታት ጄምስ ቦንድ የሆኑት ዴቪድ ኒቨን፣ ጆርጅ ላዜንቢ፣ ሮጀር ሙር፣ ቲሞቲ ዳልተር፣ ፒርስ ብሮስናን እና ዳንኤል ክሬይግ ናቸው።
የመጀመሪያው የጄምስ ቦንድ ፊልም ‘ዶክተር ኖ’ ከተሠራ ከስልሳ ዓመታት በላይ የሆነው ሲሆን፣ እስካሁን በተሠሩት 25 ፊልሞች ከ20 ቢሊዮን ዶላር በላይ በማግኘትም ኢንዱስትሪውን ከሚመሩት አንዱ ሲኒማዎች ሆኖ ተቀምጧል።
ፊልሙ በመላው ዓለም ካለው ዕውቅና ጋርም ተያይዞ ነው ቀጣዩ ጄምስ ቦንድ ማን ይሆን? የሚለው ጥያቄ ትልቅ ስፍራ የተሰጠው።
በተለይም ብሪታኒያዊው ተዋናይ አሮን ቴይለር ቀጣዩ ጄምስ ቦንድ ሊሆን ይችላል የሚሉ ሪፖርቶች መውጣታቸውን ተከትሎ መነጋገሪያ ሆኗል።
የዩኬው 'ዘ ሰን' እንደዘገበው ‘ኪክ አስ’ እና ‘ቡሌት ትሬይን’ በተሰኙ ፊልሞቹ የሚታወቀው አሮን የመጨረሻውን ጄምስ ቦንድ ዳንኤል ክሬግን በመተካት የደብልኦ ሰቨን ገጸ ባህርይን ለመጫወት ጥያቄ እንደቀረበለት ነው።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ዳንኤል ክሬግ በአምስት ፊልሞች ለ16 ዓመታት ያህል ጄምስ ቦንድን ሆኖ ከተወነ በኋላ ነው ከሦስት ዓመት በፊት ያቆመው።
የመጨረሻው የጄምስ ቦንድ ፊልም ‘ኖ ታይም ቱ ዳይ’ ሲሆን ቀጣዩም 26ኛ ይሆናል።
የጄምስ ቦንድ ፊልሞችን የሚያዘጋጀው ኢዮን ፕሮዳክሽን ቀጣዩ ደብል ኦ ሰቨን (ጄምስ ቦንድ) ማን ይሆናል? በሚሉ መላ ምቶች ላይ አስተያየቱን እንደማይሰጥ አስታውቋል።
ነገር ግን የኩባንያው ውስጥ አዋቂዎች ቀጣዩ ጄምስ ቦንድን አስመልክቶ እየተንሸራሸሩ ያሉ ወሬዎች እውነትነት እንደሌላቸው ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ቀጣዩ ጄምስ ቦንድ ይሆናል ተብሎ እየተነገረለት እና እየተዘገበለት ያለው አሮን ቴይለር በበኩሉ “ሰዎች በዚያ ገጸ ባህርይ ውስጥ እኔን ማየታቸው አስደሳች እና አስደናቂ ሆኖ አግኝቼዋለሁ” ሲል 'ኑሜሮ' ለተሰኘ መጽሔት ተናግሯል።
አክሎም “እንደ ትልቅ ሙገሳ እና ውደሳ አድርጌ ነው የማየው” ማለቱም ተዘግቧል።
በብሪታንያዊው ታላቅ ሙዚቀኛ ጆን ሌነን የሕይወት ታሪክ ላይ ተመሥርቶ የተሠራውን ‘ኖ ዌር ቦይ’ ፊልም ላይ የተጫወተው የ33 ዓመቱ አሮን ቴይለር በበርካቶች ዘንድ ለጄምስ ቦንድ ገጸ ባህርይ ከፍተኛ ግምት ተሰጥቶታል።
አሮን ቴይለር በአውሮፓውያኑ 2017 የጎልደን ግሎብ ሽልማት አሸናፊ የሆነበትን ‘ኖክቹርናል አኒማልስ’ እንዲሁም ‘አና ካሬኒና’፣ ‘ጎዚላ’ እና ‘ቴኔት’ በተሰኙ ፊልሞቹም ይታወቃል።

የፎቶው ባለመብት, EPA
ጄምስ ቦንድ ሊሆኑ ይችላሉ የተባሉ ተዋናዮች
የመጨረሻው ጄምስ ቦንድ ዳንኤል ክሬግ ገጸ ባህርዩን ወክሎ እንደማይጫወት ከሦስት ዓመታት በፊት ማሳወቁን ተከትሎ በርካታ ግምቶች እና መላምቶች ሲንሸራሸሩ ቆይተዋል።
ቀጣዩ ጄምስ ቦንድ “የፊልም ኢንዱስትሪው የቀይ ምንጣፍ ማድመቂያ እንዲሁም ተከታዩ ምትክ ብቻ እንደማይሆን” የካቺንግ ቡሌት ሜምዋርስ ኦፍ ኤ ቦንድ ፋን (Catching Bullet: Memoirs of a Bond Fan) ደራሲ ማርክ አኮነል ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ቀጣዩ ጄምስ ቦንድ “የፊልም ተዋናይ፣ የሲኒማ እና የተከታያዩ ፊልም አምባሳደር፣ የሚዲያ ዲፕሎማት፣ የብሪታንያ ባህል ችቦ አቀጣጣይ፣ ቢሊዮን ዶላሮች የሚያስገኘው የፕሮዳክሽኑ ተወካይ መሆን የሚችል ነው” ሲሉ ይናገራሉ።
ይሄ ብቻ አይደለም “በየትኛውም የዓለም ማዕዘናት በጄምስ ቦንድነቱ ሰዎች በቅጽበት ሊያውቁት የሚገባ መሆን አለበት” ይላሉ።
“የሚማርክ ቁመና እና ገጽታ ያለው፣ የሲኒማ ስክሪኖች ላይ ሲታይ የሰውን ልቦና መቆጣጠር የሚችል መሆን አለበት” በማለትም አዲሱ ጄምስ ቦንድ የሚጠበቅበትን ኃላፊነት ይናገራሉ።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
‘በጣም፣ በጣም አስደሳች ነው’
ቀጣዩ ጄምስ ቦንድ ይሆናል ተብለው ከተገመቱት መካከል ሌላኛው ‘ሱፐር ማን’ እና ‘ሚሽን ኢምፖሲፕል’ በተሰኙት ፊልሞቹ የሚታወቀው ተዋናይ ሄንሪ ካቪል ነው። ሄንሪ የመጨረሻው ጄምስ ቦንድ ዳንኤል ክሬግ በተዋናይነት ከመመረጡ በፊትም ግምት ተሰጥቶት ነበር።
“የቦንድን ገጸ ባህርይ መጫወት እፈልጋለሁ፣ በጣም፣ በጣም አስደሳች ይሆናል” ሲልም ሄንሪ 'ጂኪው' ለተሰኘው መጽሔት በአውሮፓውያኑ 2020 ተናግሮ ነበር።
ቀጣይ ጄምስ ቦንድ ይሆናል ተብሎ ግምት የተሰጠው ሌላኛው ተዋናይ ደግሞ የ32 ዓመቱ ዳምሰን ኢድሪስ ነው።
ዳምሰን ‘ስኖውፎል’ በተሰኘው በአሜሪካው የቴሌቪዥን ተከታታይ የወንጀል ፊልሙ ይታወቃል። ይህ ፊልም ስድስት ተከታታይ ክፍሎች (ሲዝንስ) ያሉት ሲሆን ከአውሮፓውያኑ 2017 እስከ 2023ም ታይቷል።
በኔትፊሊክስ ለዕይታ በበቃው ‘አውትሳይድ ዋየር’ በተሰኘው የሳይንስ ፊክሽን ፊልም የመሪውን ገጸ ባህርይ ወስዶ ተጫውቷል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የጄምስ ቦንድ ፊልሞች አፍቃሪ የሆኑት ታዳሚዎች ሌላኛው የመረጡት ጄምስ ኖርተንን ነው። ጄምስ ኖርንተን በቅርቡ ‘ኤ ሊትል ላይፍ’ የተሰኘ የመድረክ ቲያትር ላይ የተጫወተ ሲሆን፣ በአውሮፓውያኑ 2019 ‘ሊትል ውሜን’ በተሰኘው ፊልሙ ይታወቃል።
የ38 ዓመቱ ጄምስ ጀግንነትን በሚያወድሱት ‘ማክ ማፊያ’ እና ‘ሃፒ ቫሊን’ ጨምሮ በተለያዩ የቴሌቪዥን ድራማዎች ላይ ተውኗል።
ከስድስት ዓመታት በፊት ቀጣዩ ጄምስ ቦንድ ሊሆን ይችላል በሚሉ ጉዳዮች ላይ ከ'ኢቪኒንግ ስታንዳርድ' ጋዜጣ ጋር ባደረገው ቆይታ “ቀጣዩ ልሆን እንደምችል በርካታ መላ ምቶች አሉ። ምንም እንኳን መላ ምቶች ቢሆኑም “በጣም የሚያስደስት እና የመወደስ ስሜት እንዲሰማኝ የሚያደርግ ነው” ብሎ ነበር።
ነገር ግን በስድስት ዓመታት ውስጥ ብዙ ሁኔታዎች ሊቀየሩ ይችላሉ።

እነዚህ ብቻ አይደሉም እንደ ቶም ሃርዲ፣ ኢድሪስ ኤልባ እና ክሪስ ኢቫንስ ያሉ ተዋናዮችም ቀጣዮቹ ጄምስ ቦንድ ሊሆኑ እንደሚችሉ እየተጠቀሱ ይገኛሉ።
የ51 ዓመቱ ኢድሪስ ኤልባ የጄምስ ቦንድን ገጸ ባህርይ ለመጫወት “አርጅቶ” ሊሆን እንደሚችል ተናግሯል።
ለዚህም ምላሽ ዳንኤል ክሬግ ጄምስ ቦንድን የተጫወተበትን አስራ አምስት ዓመታት ቢሠራ 66 ዓመቱ ሊሆን እንደሚችልም ኢድሪስ ጠቅሷል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ለዚህ ገጸ ባህርይ ፕሮዲውሰሮች የግድ ትልቅ እና ስሙ የገነነ ተዋናይ ላይመርጡ ይችላሉ። ፒርስ ብሮስናን የጄምስ ቦንድ ፊልሞቹን መጫወት ባቆመበት በአውሮፓውያኑ 2002 በግንባር ቀደምትነት ስማቸው ሲጠቀሱ ከነበሩት መካከል ዳንኤል ክሬግ አንዱ አልነበረም።
ፒርስ ብሮስናን የአገሩ የአየርላንድ ተወላጅ የሆነው እና የኦስካር ሽልማት አሸናፊው ሲሊያን መርፊ “ግሩም” ደብል ኦ ሰቨን ሊሆን እንደሚችል በቅርቡ ለቢቢሲ ተናግሯል።
ብሮስናን ከዚህ ቀደምም ብሪጅተን በተሰኘው ፊልሙ የበርካቶችን ልብ የሰረቀውን ሬጌ ጂን ፔጅ “ድንቅ ቦንድ” ሊሆን ይችላል ብሎ ነበር።












