እስራኤል በኢራን የመጨረሻ ግቧ የስርዓት ለውጥ ሊሆን ይችላል - ግን አደገኛ ቁማር ነው

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
እስራኤል በኢራን ላይ ጥቃት ስትከፍት በይፋ የገለጸችው ግብ፤ ቴህራን ካላት የኒውክሌር አቅም የሚመነጭን የኅልውና ስጋት ማጥፋት የሚል ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔቴንያሁ ግን ከዚህ ባሻገር በቴህራን የስርዓት ለውጥ የማምጣት ሰፊ ዓላማ አላቸው።
ኔቴንያሁ በዚህ አካሄድ፤ ከዚህ በፊት ታይቶ የማይታወቁ ድብደባዎችን መፈጸም በመጨረሻ ኢስላማዊ ሪፐብሊክ እንዲገለበጥ የሚያደርግ የሁከት ሰንሰለት ያስጀምራል የሚል ተስፋ ሊኖራቸው ይችላል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ አርብ ምሽት ባወጡት መግለጫ፤ "የኢራን ሕዝብ ከክፉው እና ከጨቋኙ አገዛዝ ነጻ ለመውጣት በመቆም በባንዲራው እና በታሪካዊ አሻራው ዙሪያ አንድ የሚሆንበት ጊዜ ደርሷል" ብለዋል።
ብዙ ኢራናውያን በኢኮኖሚው ሁኔታ እንዲሁም በሀሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት፣ በሴቶች መብት እና በህዳጣን መብቶች እጦት የተነሳ ደስተኛ አይደሉም።
የእስራኤል ጥቃት በኢራን አመራሮች ላይ ትክክለኛ ስጋትን ደቅኗል።
የቴልአቪቭ ጥቃቶች የኢራን አብዮታዊ ጠባቂ ዘብ አዛዥ፣ የጦር ኃይሎች ዋና አዛዥ እና ሌሎች በርካታ ከፍተኛ የአብዮታዊ ዘቡ ኃላፊዎችን ገድለዋል። የእስራኤል ጥቃት ግን ገና አላበቃም።
ኢራን የበቀል እርምጃ በመውሰድ "በደርዘን የሚቆጠሩ ዒላማዎች፣ ወታደራዊ ማዕከላት እና አየር ማረፊያዎች" ላይ ጥቃት እንደፈጸመች የአገሪቱ አብዮታዊ ዘብ ገልጿል።
ሁኔታው በፍጥነት እየተባባሰ በመምጣቱ እና ኢራን በምላሹ የሚሳኤል ጥቃት መፈጸሟን ተከትሎ ኔቴንያሁ "ተጨማሪ ጥቃት እየመጣ ነው" ብለዋል።
በእነዚህ ጥቃቶች በርካታ የኢራን መሪዎች ዒላማ ሊሆኑ ይችላሉ።
እስራኤል ደግሞ የምትፈጽማቸው ጥቃቶች እና ግድያዎች ስርዓቱን ሊያውኩ እና ለሕዝባዊ አመፅ መንገድ ሊከፍቱ ይችላሉ የሚል ስሌት ልትይዝ ትችላለች። ቢያንስ ኔቴንያሁ የሚመኙት ይህንን ነው።
ነገር ግን ይህ አካሄድ ቁማር ነው፤ ትልቅ ቁማር ነው።
በመጀመሪያ ደረጃ እንዲህ አይነቱ ሁኔታ ሊፈጠር እንደሚችል የሚያመለክት ምንም ማስረጃ የለም። ቢፈጠር እንኳን እንዲህ ዓይነቱ ሁኔታ ወደ የት ሊያመራ እንደሚችል ግልጽ አይደለም።
ኢራን ውስጥ ከፍተኛ ስልጣን ያላቸው፤ የታጠቁ ኃይሎችን እና ኢኮኖሚውን የሚቆጣጠሩ ግሰለቦች ናቸው። እነዚህ ስልጣኖች አብዛኛው የተያዙት በአብዮታዊ ዘቡ እና በሌሎች ባልተመረጡ አካላት ውስጥ በሚገኙ አክራሪ ግለሰቦች እጅ ነው።
ራሳቸው በስልጣን ላይ ስለሆኑ መፈንቅለ መንግሥት ማካሄድ አያስፈልጋቸውም። ኢራንንም የበለጠ ወደ ግጭት መንገድ ሊያስገቧት ይችላሉ።

የፎቶው ባለመብት, EPA-EFE/Shutterstock
ሌላው ሊከሰት የሚችል ውጤት፤ የአገዛዝ ውድቀት እና ያንንም ተከትሎ የኢራን ወደ ትርምስ መግባት ሊሆን ይችላል።
90 ሚሊዮን ያህል የሕዝብ ብዛት ባላት አገር የሚፈጠር ሁነት በመላው መካከለኛው ምሥራቅ ግዙፍ ተጽዕኖ የመፍጠር እድል አለው።
የእስራኤል የምትፈልገው ውጤት፤ ወዳጅ የሆነ ኃይል ስልጣን የሚይዝበት ተቃውሞ እንዲነሳ ይመስላል። ነገር ግን ስልጣን ላይ የሚወጣው አማራጭ ማነው የሚለው ዋና ጥያቄ ነው።
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የኢራን ተቃዋሚ ኃይሎች በእጅጉ የተበታተኑ በመሆናቸው፤ እዚህ ላይ ግልጽ አማራጮች የሉም።
"የሴቶች ሕይወት ነጻነት" እንቅስቃሴ በመባል የሚታወቀው እና በአብዛኛው ኢራንን ያናወጠው የ2022 አመፅ ከተከሰተ በኋላ፤ አንዳንድ ተቃዋሚዎች ከጸረ ኢስላማዊ ሪፐብሊክ ቡድኖች እና አክቲቪስቶች ጋር ሰፊ ጥምረት ለመፍጠር ሞክረዋል።
ነገር ግን ጥምረቱን ማን እንደሚመራ እና የአሁኑ ስርዓት ከወደቀ በኋላ ምን ዓይነት የስርዓት ቅርጽ እንደሚኖር ስምምነት ላይ መድረስ ባለመቻላቸው ሙከራው አልዘለቀም።
የእስራኤል መሪዎች ከእነዚህ ቡድኖች ወይም ግለሰቦች መካከል የተወሰኑትን እንደ ተመራጭ አማራጮች ሊያዩ ይችላሉ።
ለምሳሌ፤ እ.አ.አ በ1979 በአገሪቱ በተካደው ኢስላማዊ አብዮት የተወገደው የኢራን የቀድሞ ንጉሥ (ሻህ) ልጅ የሆነው የቀድሞ ዘውዳዊ ልዑል ረዛ ፓህላቪ ይጠቀሳል።
በስደት የሚኖረው ረዛ፤ የውጭ አጋሮች ሀሳቡን እንዲደግፉ ተፅእኖ ለማሳደር በንቃት እየሞከረ ይገኛል። በቅርብ ዓመታትም እስራኤልን ጎብኝቷል።
ምንም እንኳን በአንዳንድ ኢራናውያን ዘንድ ተወዳጅነት ቢያገኝም፤ በፍጥነት ወደ አገዛዝ ለውጥ ኃይልነት ሊለወጥ ይችል እንደሆነ ግን ግልፅ አይደለም።
ሙጃሂዲን ኢ ካልቅ የተባለው እና በስደት የሚገኘው እና የኢስላማዊ ሪፐብሊክን የመገርሰስን ሀሳብ የሚደግፈው ተቃዋሚ ቡድንም ሌላኛው ኃይል ነው። ነገር ግን ይህ ቡድን ወደ ንጉሣዊ አገዛዝ መመለስ ይቃወማል።
ግራ ዘመም የሙስሊም ቡድን ሆኖ የተመሰረው ተቃዋሚው ቡድን ከዚህ ቀደምም ንጉሡን አጥብቆ ይቃወም ነበር።
ቡድኑ ከአብዮቱ በኋላ ወደ ኢራቅ በማምራት፣ እ.አ.አ በ1980ዎቹ መጀመሪያ ላይ ኢራቅ እና ኢራን ጋር ጦርነት ላይ በነበሩበት ወቅት፣ሳዳም ሁሴንን ተቀላቀቅሏል። ይህም በብዙ ኢራናውያን እንዳይወደድ አድርጎታል።
ቡድኑ በንቃት እንቅስቃሴ ማድረግ የቀጠለ ሲሆን እና አሜሪካ ውስጥም ወዳጆች አሉት። አንዳንዶቹም ለዶናልድ ትራምፕ አጋሮች ቅርብ ናቸው።
ይሁን እንጂ እንደ ማይክ ፖምፔዮ፣ ጆን ቦልተን እና ሩዲ ጁሊያኒን ያሉ ከፍተኛ የአሜሪካ ባለስልጣናት በቡድኑ ስብሰባዎች ላይ ተገኝተው ንግግሮችን ሲያቀርቡ ከነበረበት የፕሬዝዳንት ትራምፕ የመጀመሪያ የስልጣን ዘመን ጋር ሲነጻጸር በዋይት ሐውስ ያለው ተጽዕኖ ያነሰ ይመስላል።
ከሃይማኖት ነጻ ከሆነ ዴሞክራሲዊ ስርዓት እስከ ፓርላማዊ ንጉሣዊ አገዛዝ እና ሌሎችንም የሚፈልጉ ሌሎች የፖለቲካ ኃይሎችም አሉ።
አሁን የተፈጸሙትን ጥቃቶች ስፋት ለመተንተን ጊዜው ገና ሊሆን ይችላል። ነገር ግን ባለፈው ዓመት በኢራን እና በእስራኤል መካከል በተደረገው የተኩስ ልውውጥ ወቅት ኢራናውያን ሁኔታውን አገዛዙን ለመገልበጥ እንደ ዕድል ሲመለከቱት እንደነበር የሚያሳይ ጠንካራ ምልክት የለም።
ይሁን እንጂ እነዚህ ክስተቶች የአሁኖቹ ጥቃቶች ካደረሱት ጥፋት ጋር የሚመሳሰሉ አልነበሩም።
የኢስላማዊ ሪፐብሊኩ የመጨረሻ ግብ
አሁን ላይ የኢራን ጨዋታ መጨረሻ ምን እንደሆነ ጥያቄዎች ይነሳሉ።
ምንም እንኳ ኢራን እስራኤል ውስጥ በርካታ ስፍራዎች ዒላማ ብታደርግም፤ ብዙ ጥሩ አማራጮች ያሏት አይመስልም።
አንዳንዶች ከአሜሪካ ጋር ድርድር መቀጠሉ እና ከዚያ ግጭቱን ለመቀነስ መሞከር አስተማማኝ መንገድ አድርገው ሊመለከቱት ይችላሉ።
ነገር ግን ትራምፕ የሚጠይቁትን ወደ ድርድር የመመለስ ሀሳብ መቀበል ለኢራን መሪዎች ከባድ ምርጫ ነው። ምክንያቱም ይህ እርምጃ ሽንፈትን እንደተቀበሉ ሊያመለክት ይችላል።
ሌላኛው አማራጭ በእስራኤል ላይ የአጸፋ ምላሽ ጥቃቶችን መፈጸም መቀጠል ነው። የሚፈለገው አማራጭ ይህ ይመስላል።
የኢራን መሪዎች ለደጋፊዎቻቸው ቃል የገቡትም ይህንኑ ነው። ነገር ግን ጥቃቱ መቀጠሉ እስራኤል ተጨማሪ ጥቃቶችን እንድትፈጽም ሊጋብዝ ይችላል።
ቴህራን ከዚህ ቀደም የአሜሪካ የጦር ሰፈሮችን፣ ኤምባሲዎችን እና ሌሎች በቀጣናው ያሉ ቦታዎችን ዒላማ እንደምታደርግ ዝታ ነበር።
ነገር ግን ይህ በቀላሉ የሚሳካ አይደለም። አሜሪካን ማጥቃት ዋሽንግተን በቀጥታ ወደ ጦርነቱ እንድትገባ ያደርጋል። ይህ ደግሞ ኢራን የማትፈልገው አካሄድ ነው።
ካሉት አማራጮች መካከል ለሁለቱም ወገን ቀላል የሆነ አንዳችም እርምጃ የለም። አማራጮቹ የሚያስከትሉትን ውጤት መተንበይም አስቸጋሪ ነው።
አሁን አየሩ በአቧራ ተሞልቷል፤ አቧራው እስከሚሰክን ካልተጠበቀ ምን ለውጦች እንደተከሰቱ ለማየት አይቻልም።















