በጋዛ የተከሰተው ረሃብ "የሰብዓዊነት ውድቀት ነው"- የተባበሩት መንግሥታት ኃላፊ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በጋዛ ከተማ እና በአካባቢው የተከሰተው ረሃብ "የሰብዓዊነት ውድቅት ማሳያ ነው" ሲሉ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ኃላፊ ተናገሩ።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ በጋዛ ያለውን ረሃብ "እንቆቅልሽ አይደለም፤ ሰው ሰራሽ ጥፋት፣ የሞራል መላሸቅ እንዲሁም የሰብዓዊነት ውድቀት ነው" ሲሉ ገልጸውታል።
ዋና ጸሃፊው አክለውም "በጋዛ ውስጥ ያለውን ገሃነም ለመግለጽ ቃላት ያጠሩበት ሁኔታ ነው" ያለው ብለዋል።
እስራኤል "የጋዛን ምግብና እና ህክምና አቅርቦት የማረጋገጥን ጨምሮ በአለም አቀፉ ህግ የማያሻማ ግዴታዎች አሉባት" ሲሉም ዋና ጸሐፊው ተናግረዋል።
የተባበሩት መንግሥታት የፍልስጤም ስደተኞች ኤጀንሲ ኃላፊ ፉሊፔ ላዛሪኒ በበኩላቸው "ይህ በእስራኤል መንግሥት የተነደፈ ሰው ሰራሽ ረሃብ ነው" ሲሉ የዚህ ቀውስ መንስዔን ገልጸዋል።
በዓለም ዙሪያ የረሃብ ደረጃን የሚመድበው በተባበሩት መንግሥታት ድጋፍ ያለው ተቋም በጋዛ ያለውን የምግብ ዋስትና በጣም የከፋ እና ከባድ ሁኔታ ላይ በመድረሱም ከፍተኛው አምስተኛ ደረጃ ላይ መድቦታል።
የተቀናጀ የምግብ ዋስትና ደረጃ ምደባ (አይፒሲ) ከሆነ በመላው ጋዛ ከግማሽ ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ፍልስጤማውያን "በረሃብ፣ በቸነፈር እና በሞት" አሰቃቂ ሁኔታዎችን እያለፉ ነው ብሏል።
እስራኤል ይህንን ሪፖርት አጣጥላ "ሐሰተኛ" ነው ስትል የፈረጀችው ሲሆን፤ በጋዛ ረሃብ የለም በሚለው አቋሟም ጸንታለች።
እስራኤል በከበባ ውስጥ ባስገባቻት ጋዛ የሚገባውን የእርዳታ መጠን እየገደበች መሆኑን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አስታውቋል። እስራኤል ይህንን ታስተባብላለች።
ከ100 በላይ የሚሆኑ የረድዔት ድርጅቶች፣ በጋዛ ያሉ የዓይን እማኞች፣ የተባበሩት መንግሥታት ኤጀንሲዎች እንዲሁም ዩናይትድ ኪንግደምን ጨምሮ የእስራኤል አጋሮች በጋዛ ረሃብ መከሰቱን ያስታወቁ ሲሆን እስራኤል ከምትለው ጋር የሚጻረር ነው።
አይፒሲ በጋዛ ያለው ረሃብ "አፋጣኝ ምላሽ" ያስፈልገዋል ሲል ያሳሰበ ሲሆን ካለበለዚያ ሞቶች መጨመራቸው አይቀሬ ነው ብሏል።
ከነሐሴ አጋማሽ በኋላ እስከ መጪው መስከረም መገባደጃ ባለው ጊዜ ያለው ረሃብ እስከ ዴይር አል ባላህ እና ኻን ዩኒስ ረሃብ ይዛመታል ብሏል።
የጋዛ ጦርነት ከተጀመረ ጀምሮ 112 ህጻናትን ጨምሮ 271 ፍልስጤማውያን በረሃብ መሞታቸውን በሐማስ ከሚመራው የጋዛ የጤና ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያስረዳል።
አይፒሲ ከተቋቋመበት ከአውሮፓውያኑ 2004 ጀምሮ በተቋሙ በዚህ ደረጃ የተመደቡት አራት ረሃቦች ሲሆኑ ባለፈው ዓመት በሱዳን የተከሰተው አንደኛው ነው።
አይፒሲ በይፋ ረሃብ ተከስቷል ብሎ በይፋ ማወጅ አይችልም፤ ይህ የሚከናወነው በመንግሥታት ወይም በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ነው።
ለሪፖርቱ ምላሽ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የእርዳታ ኃላፊ ቶም ፍሌቸር ረሃቡን ሙሉ በሙሉ መከላከል እንደሚቻል ገልጸው፤ ምግብ ወደ ፍልስጤም ግዛት ሊደርስ ያልቻለው "በእስራኤል ስልታዊ እገዳ የተነሳ ነው" ብለዋል።"
የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ መብት ሃላፊ ቮልከር ቱርክ ረሃቡን "በእስራኤል መንግስት የተደረገ እርምጃ ቀጥተኛ ውጤት ነው" ሲሉ ገልጸው ይህም እርዳታ ወደ ጋዛ እንዳይገባ "ህገወጥ በሆነ መንገድ በመከልከሏ ነው" ሲሉ አስረድተዋል።
እስራኤል በጋዛ በሚኖሩ ፍልስጤማውያን እርዳታ እንዳይደርሳቸው ከመጋቢት ጀምሮ ሙሉ እገዳ ጥላለች። ለሁለት ወራት የቆየው የተኩስ አቁም መፍረሱን ተከትሎ በጋዛ የማያባራ ጥቃት እያካሄደች ነው።
የእስራኤል ጦር ይሄንን ሁሉ የሚያደርገው ሐማስ የቀሩ ታጋቾችን እንዲለቅ ጫና ለማድረግ ነው ይላል።
ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በጋዛ ረሃብ እያንዣበበ ነው የሚል ማስጠንቀቂያ በተደጋጋሚ ማሰማቱን ተከትሎ እገዳው በከፊል ቢላላም አሁንም ፍልስጤማውያኑ በከፍተኛ የምግብ፣ የመድኃኒት እና የነዳጅ እጥረት እየተፈተኑ ነው።
ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የተወሰኑ የእርዳታ መኪኖች በተጨማሪ፤ እስራኤል እና አሜሪካ ለፍልስጤማውያን እርዳታ እናከፋፍላለን በሚል 'የጋዛ ሂውማኒታሪያን ፋውንዴሽን' (ጂኤችኤፍ) የተሰኘ አወዛጋቢ ድርጅት አቋቁመዋል።
ከዚያን ጊዜ ጀምሮ እርዳታ ሲጠባበቁ ባሉ ፍልስጤማውያን ላይ በየቀኑ በሚባል ሁኔታ የእስራኤል ጦር በሚከፍተው ጥቃት በርካታ ሰዎች ተገድለዋል።
በባለፉት ሁለት ወራት የእስራኤል ጦር በእርዳታ ጠባቂ ፍልስጤማውያን ላይ በከፈተው ተኩስ ከ1,000 በላይ ሰዎች መገደላቸውን የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብቶች ቢሮ አስታውቋል።
ከእነዚህ ውስጥም 766 ግድያዎች የተፈጸሙት በጋዛ የሰብዓዊ ፋውንዴሽን ግቢ ውስጥ ነው።
ቀሪዎቹ 288 ፍልስጤማውያን ደግሞ የተገደሉት የተፈጸሙት በተባበሩት መንግሥታት እና በሌሎች የእርዳታ መኪኖች አቅራቢያ ነው።















