ሩሲያ በዩክሬን ቁልፍ ግዛት ላይ የምትፈጽመውን ጥቃት አጠናክራ ቀጠለች

የፎቶው ባለመብት, Press service of the State Emergency Service of Ukraine in Odesa region
ሩሲያ በደቡባዊ የዩክሬን ኦዴሳ ክልል ላይ የምትፈጽመውን ጥቃት አጠናክራ ቀጠለች።
ይህም ሰፊ የኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥ እና በክልሉ የሚገኘውን የባህር መሠረተ ልማት አደጋ ላይ ጥሏል።
የዩክሬን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ኦሌክሲይ ኩሌባ፣ ሞስኮ በክልሉ ላይ "ስልታዊ" ጥቃቶችን እያካሄደች መሆኑን ተናግረዋል።
ባለፈው ሳምንት የጦርነቱ ትኩረት "ወደ ኦዴሳ አቅጣጫ ሊሆን ይችላል" ሲሉ አስጠንቅቀው ነበር።
ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዜሌንስኪ በበኩላቸው ሩሲያ በተደጋጋሚ የምትፈጽማቸው ጥቃቶች ዩክሬን የባህር ላይ ሎጂስቲክስን እንዳትጠቀም ለማገድ የምታደርገው ሙከራ ነው ብለዋል።
የሩሲያ ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን በታኅሳስ ወር መጀመሪያ ላይ ዩክሬን በጥቁር ባህር ላይ የሚንቀሳቀስ የሩሲያ ነዳጅ ጫኝ መርከብ ላይ ጥቃት ከፈጸመች በኋላ ወደ ባሕሩ የመግባት አቅሟን እንደሚቀንሱ ዝተው ነበር።
እአአ በ2022 ሩሲያ ዩክሬንን ሙሉ በሙሉ ከወረረች በኋላ ምዕራባውያን የጣሉባትን ማዕቀብ ለማለፍ እና በመቶዎች የሚቆጠሩ ነዳጅ ጫኝ መርከቦችን ለማሳለፍ የምትጠቀምባቸው "ሻዶው ፍሊት" የሚባሉ መርከቦች አሏት።
እነዚህ በምስጢር ነዳጅ የሚያመላልሱ መርከቦች በአብዛኛው ያረጁ ነዳጅ መጫኛ ቦቴዎችን የሚይዙ ሲሆን ብዙዎቹ ንብረትነታቸው የማን እንደሆነ እና የመድን ዋስትና የቱ ኩባንያ እንደሰጣቸው ግልጽ አይደለም።
ሰኞ ምሽት ላይ የኦዴሳ የወደብ መሠረተ ልማት ላይ በተፈጸመ ጥቃት ለሰላማዊ አገልግሎት የሚውሉ መርከቦች መጎዳታቸውን የክልሉ አስተዳዳሪ ተናግረዋል።
ሩሲያ በክልሉ በተደጋጋሚ በፈፀመችው ጥቃት ለቀናት የኤሌክትሪክ አቅርቦት የተቋረጠ ሲሆን በርካታ ሰዎች ተገድለዋል።
እሁድ ምሽት በተፈፀመ ጥቃት የ120,000 ሰዎች የኤሌክትሪክ ኃይል ተቋርጦ የነበረ ሲሆን በዋናው ወደብ ላይ እሳት በመቀስቀሱ በርካታ የዱቄት እና የምግብ ዘይት የያዙ ኮንቴይነሮች ወድመዋል።
ባለፈው ሳምንት በኦዴሳ ምሥራቃዊ ክፍል በሚገኘው ፒቭዴኒ ወደብ ላይ በተፈፀመ የባለስቲክ ሚሳኤል ጥቃት ስምንት ሰዎች ሲገደሉ ቢያንስ 30 ሰዎችን ቆስለዋል።
በሳምንቱ መጀመሪያ ላይ በተፈጸመ ሌላ ጥቃት ከሦስት ልጆቿ ጋር በመኪና የምትጓዝ እናትን ገድሎ ዩክሬን እና ሞልዶቫ የሚያገናኘውን የኦዴሳ ክልል ብቸኛ ድልድይ ሰብሯል።
ዜሌንስኪ፣ ዲሚትሮ ካርፔንኮ በሳምንቱ መጨረሻ ላይ መባረራቸውን ተከትሎ ለክልሉ አዲስ የአየር ኃይል አዛዥ እንደሚመረጥ ተናግረዋል።
የኦዴሳ ወደብ ለአገሪቱ ኢኮኖሚ ቁልፍ ስትሆን ከተማዋ ከኪየቭ እና ከካርኪቭ ቀጥሎ በዩክሬን ሦስተኛዋ ትልቅ ከተማ ነች።
አሁን በሩስያ ወረራ ምክንያት በዛፖሪዝሂያ፣ በኬርሰን እና በማይኮላይቭ ክልሎች ውስጥ የሚገኙ ሌሎች ወደቦች መድረስ ስለማይቻል ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታም አላት።
ጦርነቱ ቢኖርም ዩክሬን በዓለም ላይ ከፍተኛ የስንዴና የበቆሎ ላኪ ናት።
እንደ አውሮፓውያኑ ከነሐሴ 2023 ጀምሮ ኦዴሳ የሮማኒያ እና የቡልጋሪያ የባህር ዳርቻዎችን በመከተል እህል ወደ ውጭ ለመላክ የሚያስችላት ወሳኝ መተላለፊያ ሆና ቆይታለች።
ቀደም ሲል ሩሲያ በኦዴሳ ሕዝብ ላይ "ትርምስ እየፈጠረች ነው" ሲል የከሰሱት ዜሌንስኪ "ሩሲያ ላይ ጫና ሳይደረግ፣ የምትፈጽመውን ጥቃት ለማቆም ምንም ፍላጎት እንደሌላት ሁሉም ማየት አለበት" ብለው ነበር።















