የቻይና እና የሩሲያ ወዳጅንት ምን ያህል ይዘልቃል?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ሩሲያ እንደ ፔንዱለም ናት።
ከአንድ ወገን ወደ ሌላው በዝግታ ትንቀሳቀሳለች።
በአንድ በኩል ወደ አውሮፓ ስታማትር በሌላ በኩል ወደ ምሥራቁ ዓለም ትመለከታለች።
ራሷን እንደ ምዕራቡ ዓለም ሥልጣኔ አካል የምትቆጥርበት ጊዜም አለ።
በተቃራኒው ራሷን የምዕራቡ ዓለም ተጻራራሪ፣ የምሥራቁ ዓለም አጋር አድርጋ ትመለከታለች።
ቭላድሚር ፑቲን ሩሲያን በበለጠ ወደ ምሥረቁ ዓለም ይጎትታሉ።
ሩሲያ ዩክሬንን ከወረረች በኋላ ከምዕራቡ ዓለም ተቆራርጣለች። በማዕቀብ አጥለቅለቀዋታል።
ጆ ባይደን፣ ፑቲንን “አምባገነን ገዳይ” ብለዋቸዋል።
የዩኬ ጠቅላይ ሚንስትር ሊዝ ተረስ ደግሞ “ተስፋ ያጣ ወንበዴ” ይሏቸዋል።
ዢ ዢንፒንግ ግን ፑቲንን “ውዱ ጓደኛዬ” ሲሉ አሞካሽተዋቸዋል።
ከሰሞኑ ኡዝቤኪስታን ተገናኝተዋል።
ፑቲን በቻይና እና ሩሲያ መካከል ያለውን ትስስር “ስትራቴጂያዊና ሁሉን ዓቀፍ ወዳጅነት” ብለውታል።
ሁለቱ መሪዎች ራሳቸውን እንደ ምዕራቡ ዓለም ተገዳዳሪ ያያሉ።
እንደው እስከወዲያኛው ወዳጆች ሆነው ይቀጥላሉ?
ይህ የሚሆንበት ዕድል ጠባብ ነው።
በፖለቲካ “ዘላለማዊ ጓደኝነት” የለም።
በዚያ ላይ ጓደኝተናቸው የእኩያሞች አይደለም።
ሩሲያ ዩክሬንን መውረሯ ጎድቷታል።
በቅርቡ በተለያየ ግንባር ሽንፈት እየገጠማት እንደሆነም ተናግራለች።
ምዕራባውያንም በማዕቀብ አዳክመዋታል።
ስለዚህም በቻይና እና ሩሲያ ወዳጅነት፣ ሩሲያ የበታች ናት።
ቻይና ‘ልዩ ኦፕሬሽን’ የምትለውን የዩክሬን ወረራ በተመለከተ ቻይና “ጥያቄዎችና ስጋቶች” እንዳሏት አስታውቃለች።

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ከአውሮፓ ጋር የነዳጅ ጦርነት ውስጥ የገቡት ፑቲን፣ ምሥራቁን ጠበቅ ከማድረግ ውጭ ምን አማራጭ አላቸው?
የግድ ለሩሲያ ጋዝ አዲስ ገበያ ማግኘት አለባቸው።
በጆን ሆፕኪንስ የዓለም አቀፍ ጥናት ተመራማሪው ፕ/ር ሰርጌ ራድቻንኮ “ሩሲያ ወደ ምሥራቁ ማማተሯ በገንዘብ ተጠቃሚ ያደርጋትል ብዬ አላምንም” ይላሉ።
ጋዝ እና ነዳጅ ለማዘዋወር የምዕራባውያን ቴክኖሎጂ ድጋፍ እደሚያስፈልጋት እንደ ማሳያ ይጠቅሳሉ።
“ጋዙን ወደ ሌላ መስመር እንዲጓዝ ማድረግ ቀላል አይደለም። ሶቭየት ኅብረትና ሩሲያ ትቦውን ለመዘርጋት ዓመታት ወስዶባቸዋል” ሲሉ ያስረዳሉ።
ስለዚህ በአንዴ የጋዝ ገበያው ወደ እስያ አይዞርም።
ፑቲን እና ዢ የተገናኙት በሻንጋይ ኮፕሬሽን ኦርጋናይዜሽን (ኤስሲኦ) ስብሰባ ነው።
ሩሲያ፣ ቻይና፣ ካዛኪስታን፣ ኡዝቤኪስታን፣ ታጃኪስታን፣ ኪጋዚስታን፣ ሕንድ እና ፓኪስታን ይገኙበታል።
የምዕራቡ ዓለም ሩሲያን ለመነጠል እየሞከሩ ባለበት ሰዓት ሌሎች ወዳጆችን የበለጠ ለማቅረብ ሩሲያ ስብሰባውን ትጠቀምበታለች ተብሎ ይታመናል።
“ሩሲያ የተገለለችው በምዕራቡ ዓለም ብቻ እንደሆነና ከምዕራቡ ዓለም በተጻራሪው ሩሲያን የሚያቅፍ ሌላ የኃያላን ስብስብ እንዳለ ማሳየት ትፈልጋለች” ይላሉ ፕ/ር ሰርጌ።
“ሆኖም ግን በኤስሲኦ ስብስብ ውስጥ ያለው የኃይል ሚዛን እየተቀየረ ነው። የማዕከላዊ እስያ የኃይል ሚዛን ከሩሲያ ቁጥጥር እየወጣ ነው” ሲሉ ያክላሉ።
ፑቲን በዩክሬኑ ጦርነት መዳከምና ሽንፈት እየታየባቸው ይገኛል።
በተቃራኒው የማዕከላዊ እስያ አገራት ፖሊሲዎቻቸውን በማስፈጸም ረገድ እየተሳካላቸው ነው።
ፕ/ር ሰርጌ እንደሚሉት፣ እንደ ካዛኪስታን ያሉ አገሮች ከሩሲያ ጋር ያላቸው ግንኙነት ባሻቸው አቅጣጫ የመዘወር አቅም ማሳየት ጀምረዋል።
በዩክሬኑ ጦርነት ፑቲን ከካዛኪስታን የሚጠብቁት ያህል ድጋፍ አላገኙም።
ይህም የኃይል ሚዛኑን መለወጥ ይጠቁማል።
ወጣም ወረደም፣ በዓለም ትልቋ አገር ሩሲያ ወደ ምሥራቁ ማዘንበሏን ገፍታበታለች
መረሳት የሌለበት ነጥብ ሩሲያ የአውሮፓም የእስያም አካል መሆኗ ነው።
ወደ አንዱ ብቻ ከማዘንበል፣ ምናልባትም የሁለትም ወገን ወዳጅ መሆን ሳያዋጣት አይቀርም።












