ቬትናማዊቷ ቢሊየነር 44 ቢሊዮን ዶላር በማጭበርበር የሞት ፍርድ ተፈረደባቸው

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በቬትናም ታሪክ ውስጥ እጅግ አስደናቂ በሆነው የፍርድ ሂደት በዓለም ላይ ታይቶ የማያውቅ ተብሎ በተፈረጀው የባንክ ማጭበርበር ብያኔ ተላልፏል።
በሆቺ ሚኒ ከተማ የሚገኘው ፍርድ ቤት በሪል እስቴት ላይ በተሰማሩት የ67 ዓመቷ ቢሊየነር ላይ ለ11 ዓመታት ያህል የአገሪቱን ታላላቅ ባንኮች በመዝረፍ የሞት ፍርድ ፈርዶባቸዋል።
የቬትናም ፍርድ ቤት በሴቶች ላይ የሞት ፍርድ መፍረድ ያልተለመደ ሲሆን በተለይም በገንዘብ ነክ ወንጀል ጋር በተያያዘ ብያኔ ሲያስተላልፍ የመጀመሪያው ነው።
ትሩኦንግ ማይ ላን የተባሉት ቢሊዮነር በአገሪቱ ከሚገኘው ሳይጎን ንግድ ባንክ 44 ቢሊዮን ዶላር በመውሰድ ነው የተከሰሱት።
በብያኔው መሰረት ቢሊየነሯ 27 ቢሊዮን ዶላር እንዲመልሱ የሚያስገድዳቸው ቢሆንም አጠቃላይ አቃቤ ህግ በፍጹም ሊመለስ አይችልም ብለዋል። በሚስጥራዊነታቸው የሚታወቁት የገዢው ፓርቲ ኮሚኒስት ባለስልጣናት ባልተለመደ ሁኔታ ስለ ፍርዱ ሁኔታም ዝርዝር መረጃዎችን ሰጥተዋል።
ለፍርድ ሂደቱ 2 ሺህ 700 ሰዎች በምስክርነት መጠራታቸውን እንዲሁም 10 አቃብያነ ህግ እና 200 የሚጠጉ ጠበቆች ተሳታፊ መሆናቸውንም ተናግረዋል።
የቀረበባቸው ማስረጃ ስድስት ሺህ ኪሎግራም በሚመዝኑ 104 ሳጥኖች ቀርበዋል።
ሰማንያ አምስት ተከሳሾችም ከትሩኦንግ ማይ ላይ ጋር ክስ የቀረበባቸው ሲሆን እሳቸውም ክሱን ውድቅ አድርገዋል።
በኮሚኒስት የአገዛዝ ዘመን እንዲህ ዓይነት የፍርድ ሂደት አጋጥሞ እንደማያውቅ በቬትናም የረዥም ጊዜ ልምድ ያላቸው በጡረታ ላይ ያሉት የአሜሪካ የቀድሞ ባልስልጣን ዴቪድ ብራውን ተናግረዋል።
የፍርድ ሂደቱ በኮሚኒስት ፓርቲ ዋና ጸሐፊውን ንጉየን ፉ ትሮንግ የሚመራው የጸረ ሙስና ዘመቻ እጅግ አስደናቂ ምዕራፍ ነው ተብሏል። ዋና ጸሐፊው ባልተገራ ሙስና የተነሳ እየተንቀለቀለ ያለው የህዝብ ቁጣ ለኮሚኒስት ፓርቲ ስልጣን የህልውና ስጋት ይፈጥራል ብለው ያምናሉ።
የንግድ ደጋፊ የነበሩትን ጠቅላይ ሚኒስትር በማሸነፍ በፓርቲው የበላይነት የያዙት ዋና ጸሓፊው ዘመቻቸውንም በአውሮፓውያኑ 2016 ነው የጀመሩት። በዘመቻው የተነሳ ሁለት ፕሬዚዳንቶች እና ሁለት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሮች ስልጣን ለመልቀቅ ሲገደዱ በመቶዎች የሚቆጠሩ ባልስልጣናት የዲሲፒሊን ቅጣት ወይም በእስር ላይ ይገኛሉ።
በአሁኑ ወቅት በአገሪቷ ውስጥ በሃብት በቁንጮነት ስፍራ የተቀመጡትም ሃብታም ሴትም ይሄው እድል አጋጥሟቸዋል።
ትሩኦንግ ማይ ላን ቀደም ባለ ወቅት ሳይጎን በአሁኑ ወቅት ሆቺ ሚኒ በተሰኘችው ከተማ ሲኖ ቬትናም በሚል ከሚጠሩት ቤተሰብ ነው ትውልዳቸው።
ከተማዋ በርካታ ትውልዳቸውን ከቻይና የሚመዙ ማህበረሰቦች መኖሪያ የቬትናም ምጣኔ ኃብት እና የንግድ አንቀሳቃሽ ሞተር ሆና ቆይታለች።
ከእናቷ ጋር የመዋዋቢያ ዕቃዎችን በመሸጥ ወደ ንግዱ የገቡት ትሩኦንግ የኮሚኒስት ፓርቲ በአውሮፓውያኑ 1986 ያደረገውን የኢኮኖሚ ማሻሻያ ተከትሎም መሬት እና ንብረት መግዛት ጀመሩ። በ1990ዎቹም ስመ ጥር የሆኑ ሆቴሎች እና ምግብ ቤቶች ነበሯቸው።
በአውሮፓውያኑ 2011 ትሩኦንግ ማይ ላን በሆቺ ሚኒ ከተማ ውስጥ ስመ ጥር የሆኑ ሀብታም ለመሆን በቁ።
እንዲሁም የጥሬ ገንዘብ እጥረት አጋጥሟቸዋል የተባሉ ሶስት ትንንሽ ባንኮችንም ወደ ትልቁ ሳይጎን ንግድ ባንክ እንዲያስገቡም ተፈቅዶላቸው ነበር።
የቬትናም ህግ ማንኛውም ግለሰብ በየትኛውም ባንክ ውስጥ ከ5 በመቶ በላይ ድርሻ እንዳይኖራቸው ቢከለክልም እሳቸው ግን በመቶዎች በሚቆጠሩ የሼል ኩባንያዎቻቸው እና ለሳቸው በሚሰሩ ግለሰቦች አማካኝነት ከሳይጎን የንግድ ባንክ ከ90 በመቶ በላይ ድርሻ አላቸው ሲሉም አቃብያነ ህግ ያስረዳሉ። ያንንም ስልጣን በመጠቀም የራሳቸውን ሰዎች የባንኩ ስራ አስኪያጆች አድርጎ በመሾም እና ለሚቆጣጠሯቸው የሼል ኩባንያዎች በመቶዎች የሚቆጠሩ ብድሮችን እንዲያጸድቁ ትዕዛዝ ሰጥተዋል። ባንኩ ከፈጸመው ብድር ውስጥ 93 በመቶው የሳቸው ብድር ነው ተብሏል።
እንዲሁም አቃቤ ህግ እንደሚያስረዳው ከአውሮፓውያኑ 2019 ጀምሮ ባሉት ሶስት ዓመታት ውስጥ በአሽከርካሪያቸው አማካኝነት 108 ትሪሊየን የቬትናም ዶንግ ወይም ከ4 ቢሊዮን ትሪሊየን ዶላር በላይ በጥሬ ገንዘብ አውጥተው ምድር ቤታቸው ውስጥ እንዲያከማቹ ትዕዛዝ አስተላልፈዋል።
በተጨማሪም ብድራቸው ጥያቄ እንዳይነሳበት እና ምርመራ እንዳይደረግበትም ጉቦ ሰጥተዋል ተብሏል ከዚህም ውስጥ በማዕከላዊ ባንክ ዋና ኢንስፔክተር 5 ሚሊዮን ዶላር ጉቦ እንደሰጡም ክሳቸው ያስረዳል።












