ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ ሞሐመድ ኢትዮጵያ ለሶማሊያ “ሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነት ስጋት” ናት አሉ

የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ ሞሐመድ
የምስሉ መግለጫ, የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ ሞሐመድ

የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ ሞሐመድ ኢትዮጵያ ለሶማሊያ “ሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነት ስጋት” መሆኗን እንዲሁም ከኢትዮጵያ ጋር የሚደረግ ድርድር እንደማይኖር እና ሶማሊያ ሉዓላዊነቷን ለድርድር እንደማታቀርብም ተናግረዋል።

የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼህ ሞሐመድ ይህንን ያሉት የኢድ አልፈጥር በዓልን አስመልክቶ ትናንት ረቡዕ ሚያዝያ 2/2016 ዓ.ም. ለአገሪቱ ሕዝብ ባደረጉት ንግግር ነው። 24 ደቂቃ ገደማ የቆየው የፕሬዝዳንቱ ንግግር የአገር ውስጥ እና ቀጣናዊ ጉዳዮችን የዳሰሰ ነበር።

የባሕር በር ለማገኘት ከሶማሊላንድ ጋር በተፈራረመችው የመግባቢያ ስምምነት ምክንያት ከሶማሊያ ጋር ውዝግብ ውስጥ የገባችው እና አምባሳደሯን እንድታስወጣ የተደረገችው የኢትዮጵያ ጉዳይም በፕሬዝዳንቱ ንግግር ውስጥ ተነስቷል።

“የኢትዮጵያ መሪዎች ወደ ቀልባቸው መመለስ አለባቸው” ያሉትን ሐሴን ሼህ፤ ግጭት እየፈጠረች ያለችው ኢትዮጵያ እንጂ ሶማሊያ እንዳልሆነች ለዓለም እየተናገሩ መሆኑን ገልጸዋል።

“እኛ የኢትዮጵያን አካል እንፈልጋለን አላልንም። ለኢትዮጵያን መንግሥት እውቅና አንሰጥም [አላልንም]፤ ከክልል መንግሥት ጋር ስምምነት እንፈጽማለንም አላልንም” ሲሉ ሶማሊያ ከኢትዮጵያ ጋር ግጭት እየፈጠረች አይደለም የሚለውን ሀሳባቸውን አጠናክረዋል።

ሁለቱ ጎረቤት አገራት በጋራ ፍላጎቶቻቸው ላይ መሥራት ያላቸው “ብቸኛ አማራጭ” መሆኑን በንግግራቸው ላይ የጠቀሱት ፕሬዝዳንቱ፤ “ሉዓላዊነታችንን፣ አንድነት እና ሙሉዕነታችንን ለድርድር የሚያቀርብ የጋራ ፍላጎት ሊኖረን አይችልም” ብለዋል።

ሐሰን ሼክ፤ “ለዓለም እየተናገርን ያለነው፤ እኛ ለኢትዮጵያ ሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነት ስጋት እንዳልሆንን ነው። እነሱ ግን ናቸው። እናም ይህ እንዲፈጠር በፍፁም አንፈቅድም” ሲሉ ከኢትዮጵያ ተጋርጦብናል ያሉትን ስጋት ገልጸዋል።

ሶማሊያ፤ ከኢትዮጵያ ጋር ድርድር ልታደርግ እንደማትችል እና ሉዓላዊነቷን ለድርድር እንደማታቀርብ የተናገሩት ሐሴን ሼክ፤ “ንግግርን ወይም ድርድርን እየተቃወምን አይደለም። ነገር ግን መሬታችን እንዲወሰድ ወይም ሉዐላዊነታችን ለድርድር እንዲቀርብ አንፈቅድም” ሲሉም ተደምጠዋል።

ፕሬዝዳንቱ፤ የኢትዮጵያ መሪዎች እየተከተሉት ያለው አካሄድ “እንደማይሠራላቸው” እና “ከዚህ መንገድ እንዲመለሱ እየመከሯቸው” መሆኑንም አንስተዋል።

ሐሰን ሼክ ሞሐመድ ይህንን ንግግር ያደረጉት አገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት በማቋረጥ የኢትዮጵያ አምባሳደር እና ዲፕሎማቶች ሶማሊያን ለቀው እንዲወጡ ትዕዛዝ ካስተላለፈች ከቀናት በኋላ ነው። በአዲስ አበባ የሚገኙት የሶማሊያ አምባሳደርም ወደ ሞቃዲሾ እንዲመለሱ መታዘዛቸው ይታወሳል።

ኢትዮጵያን እና ሶማሊያን ውዝግብ ውስጥ የከተተው የአዲስ አበባ እና ሐርጌሳ ስምምነት ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ የባሕር በር እንድታገኝ የሚያስችላት ነው። ሶማሊላንድ በምላሹ እንደ አገር እንድትቆጠር የሚያስችላትን ዕውቅና ከኢትዮጵያ ለማግኘት ስምምነት ላይ መድረሷን አሳውቃ ነበር።

ሁለቱ አካላት ጥር ላይ የተፈራረሙት የመግባቢያ ስምምነት በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ተፈፃሚነት ወደሚኖረው ስምምነት ተቀይሮ ተግባራዊ እንደሚሆን ሁለቱ አካላት በተፈራረሙበት ዕለት ተገልጾ ነበር። ይሁንና የመግባቢያ ስምምነቱ ከተፈረመ አራት ወራት ቢያልፍም እስካሁን ድረስ ተፈፃሚነቱ የደረሰበትን ደረጃ በተመለከተ በይፋ የተነገረ ነገር የለም።