ፑንትላንድ እና ሶማሊላንድ የኢትዮጵያን ቆንስላ ጽህፈት ቤቶችን እንደማይዘጉ አስታወቁ

የፎቶው ባለመብት, puntland tv
የሶማሊያ ፌደራል መንግሥት በፑንትላንድ ዋና ከተማ ጋሮዌ እና በሶማሊላንድ ሐርጌሳ የሚገኙት የኢትዮጵያ ቆንስላ ጽህፈት ቤቶችን እንዲዘጉ ያስተላለፈውን ትዕዛዝ እንደማይቀበሉት ሁለቱ ግዛቶች አስታወቁ።
የሶማሊያ ማዕከላዊ መንግሥት የኢትዮጵያ መንግሥት በውስጥ ጉዳዬ ጣልቃ እየገባ ነው በሚል በሞቃዲሾ የኢትዮጵያ አምባሳደር አገሪቱን ለቀው እንዲወጡ እና በከፊል ራስገዟ ፑንትላንድ እና ነጻነቷን ባወጀችው ሶማሊላንድ ያሉት የኢትዮጵያ ቆንስላ ጽህፈት ቤቶች እንዲዘጉ አዟል።
የፑንትላንድ ሶማሊያ መንግሥት በሚለው ይፋዊ መጠሪያዋ የምትታወቀው የፑንትላንድ አስተዳዳር ዓርብ መጋቢት 27/2016 ዓ.ም. ባወጠው መግለጫ ቆንስላው እንዲዘጋ የተላለፈው ትዕዛዝ የሶማሊያን ሕገ-መንግሥትን የሚጥስ ነው በማለት ተግባራዊ እንደማይደረግ አስታውቋል።
ከሶማሊያ በመለየት ነጻ አገርነቷን ካወጀች ሦስት አስርት ዓመታት የሆናት ሶማሊላንድ በበኩሏ በሶማሊያ ፌደራል መንግሥት በኩል በኢትዮጵያ ላይ የተወሰደው ዲፕሎማሲያዊ እርምጃ በሁለቱ ወገኖች በኩል ባለው ግንኙነት ላይ ውጤት የለውም ብላለች።
የሶማሊያ የውጭ ጉዳይ ምክትል ሚኒስትር ሩዳ ጃማ ለቢቢሲ ሶማሊኛ፣ በኢትዮጵያ እና በሶማሊላንድ መካከል ያለው ግንኙነት የሁለቱ አገራት ጉዳይ እንደሆነ እና እየተጠናከረ መሆኑን ገልጸዋል።
“ኢትዮጵያ እና ሶማሊላንድ መልካም ግንኙነት ያላቸው ሁለት አገራት ናቸው” በማለት በሶማሊያ ፌደራል መንግሥት የተወሰደው እርምጃ እንደማያሳስባቸው ተናግረዋል።
ከጎረቤት አገር ኢትዮጵያ፣ ነጻ አገር ነኝ ከምትለው ሶማሊላንድ እና በከፊል ራስ ገዝ ከሆነችው ፑንትላንድ ጋር ፖለቲካዊ እሰጣ ገባው ውስጥ የገባው የሶማሊያ ፌደራል መንግሥት ሐሙስ ሦስቱን መንግሥታት የተመለከተ ጠንካራ ዲፕማሲያዊ እርምጃ መውሰዱን አስታውቋል።
የፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ ሙሐመድ አስተዳደር የኢትዮጵያው አምባሳደር ሙክታር ከድር ዋሬ በ72 ሰዓታት ከአገር እንዲወጡ ትዕዛዝ ከማስተላለፉ በተጨማሪ አዲስ አበባ በሐርጌሳ እና ጋሮዌ ያላት ቆንስላዎች በአንድ ሳምንት ውስጥ እንዲዘጉ ትዕዛዝ ሰጥቷል።
ይሁን እንጂ የሶማሊላንድ እና ፑንትላንድ በሚኒስትር ደረጃ ያሉ መሪዎች የፌደራል መንግሥቱ ውሳኔን እንደማይቀበሉ ተናግረው ነበር።
ከዚህ በተጨማሪም የሶማሊያ መንግሥት በአዲስ አበባ የሚገኙትን አምባሳደሩን “ለአጠቃላይ ምክክር” ከኢትዮጵያ ለቀው እንዲወጡ ማዘዙን የሶማሊያ የውጭ ጉዳይ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሚኒስቴር ይፋ አድርጓል።

የፎቶው ባለመብት, SOMALIAONLINE
ሶማሊያ በኢትዮጵያ አምባሳደር እና ቆንስላ ጽህፈት ቤቶች ላይ የወሰደችው እርምጃ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የማቋረጥ ያህል የሚታይ ነው።
የሶማሊያን እርምጃ ተከትሎ ኢትዮጵያ እስካሁን በጉዳዩ ላይ በይፋ ያለችው ነገር የለም።
ሶማሊያ “በቅርቡ የተከሰቱ ሁኔታዎችን መሠረት በማድረግ እና የአገሪቱን ሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነትን መሠረት በማድረግ” በርካታ ዲፕሎማሲያው እርምጃዎችን መውሰዷን መግለጫዋ አስታውቃለች።
የሶማሊያ መንግሥት በመግለጫው ኢትዮጵያ “በሶማሊያ ሉዓላዊነት እና የውስጥ ጉዳይ” ጣልቃ ገብታለች ሲል ከሷል።
ኢትዮጵያ ታኅሣሥ 2016 ዓ.ም. ከሶማሊያ ተገንጥላ ነጻ አገርነቷን ካወጀችው ሶማሊላንድ ጋር የባሕር ጠረፍ ማግኘት የሚያስችላትን የመግባቢያ ስምምነት መፈረሟ ሞቃዲሾን ያስቆጣ ሲሆን፣ በሁለቱ አገራት መካከል ያለውን ግንኑነትም አጠልሽቶት ቆይቷል።
ባለፈው ሳምንት ማብቂያ ላይ ደግሞ የሶማሊያ መንግሥት ያደረገውን የሕገ-መንግሥት ማሻሻያ በመቃወም ከፊል ራስ ገዝ የሆነችው ፑንትላንድ ለፌደራል መንግሥቱ እውቅና መስጠት አቁሚያለሁ ብላለች።
ይህ የፑንትላንድ ውሳኔ በሶማሊያ ፖለቲካ ውጥረት ፈጥሮ ባለበት ወቅት የፑንትላንድ የገንዘብ ሚኒስትር በስቲያ ረቡዕ መጋቢት 25/2016 ዓ.ም. ለጉብኝት አዲስ አበባ ገብተው ከኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዲኤታ ጋር መወያየታቸው ሶማሊያን ሳይስቆጣ አልቀረም።
የሶማሊያ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት አሁን የኢትዮጵያን ዲፕሎማት ለማባረር እና የቆንስላ ጽህፈት ቤቶቿ እንዲዘጉ ከውሳኔ ላይ የደረሰው የገንዘብ ሚኒስትሩን ጉብኝት ተከትሎ ሊሆን እንደሚችል ተገምቷል።
የፑንትላንድ አስተዳደር መንግሥት ዛሬ ዓርብ ንጋት ባወጣው መግለጫ የሶማሊያን ውሳኔ እንደሚቃወም ገልጾ፤ ፑንትላንድ የውጭ ፍላጎቷን ለማስጠቅ ከማዕከላዊው የሶማሊያ መንግሥት እውቅና ውጪ በቀጥታ በራሷ አማካይነት ግንኙነቶችን እንደምታደርግም ጨምራ ገልጻለች።












