በአቶ በቴ ግድያ ላይ ገለልተኛ ዓለም አቀፍ አካል ምርመራ እንዲያደርግ የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት እንዲፈቅዱ አሜሪካ ጠየቀች

የፎቶው ባለመብት, REPORTER NP
በትውልድ ከተማቸው መቂ ተገድለው በተገኙት የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር አቶ በቴ ኡርጌሳ ግድያ ላይ ገለልተኛ ዓለም አቀፍ አካል ምርመራ እንዲያደርግ የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት እንዲፈቅዱ አሜሪካ ጠየቀች።
“የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ተዓማኒ፣ ገለልተኛ ዓለም አቀፍ አካል በበቴ ኡርጌሳ ሞት ላይ ጥልቅ ምርመራ እንዲያደርግ እንዲፈቅዱ” የአሜሪካ ሴኔት የውጭ ጉዳዮች ኮሚቴ ሚያዝያ 2/2016 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ ላይ ጥሪ አቅርቧል።
ለደኅንነታቸው ሲባል ስማቸው እንዲገለጽ ያልፈቀዱ የአቶ በቴ ኡርጌሳ የቅርብ ጓደኛ ለቢቢሲ እንደተናገሩት አቶ በቴ በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ሸዋ ዞን በምትገኘው መቂ ከተማ የተገደሉት ማክሰኞ ሚያዚያ 1/2016 ዓ.ም. እኩለ ሌሊት ላይ ነው።
የፖለቲከኛው ግድያ “አስደንጋጭ እና አሳዛኝ እንደሆነ “ የሴኔቱ የውጭ ግንኙነት ኮሚቴ ሊቀመንበር የምክር ቤቱ አባል ቤን ካርዲን በኮሚቴው ይፋዊ ድረገጽ ላይ አስፍረዋል።
ለቤተሰቦቻው የተሰማቸውን ጥልቅ ሐዘን ባሰፈሩበት በዚህ መግለጫቸው በክልሉ “ሕገወጥ ግድያዎች፣ እንግልት እና የፖለቲካ ጭቆና እየተለመደ መጥቷል” ብለዋል።
“የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አገዛዝ” በኦሮሚያ ክልል ውስጥ ብቻ ሳይሆን በመላው ኢትዮጵያ የፖለቲካ ተቃዋሚዎችን፣ ሚዲያዎች እና ተቺዎች ላይ “ጭቆና እየፈጸመ” ነው ሲሉም ወቅሰዋል።
ይህም ሁኔታ ለመላው አገሪቱ “መጠነ ሰፊ የፀጥታ ችግር እና አጠቃላይ አለመረጋጋት አስተዋጽኦ አድርጓል” ብለዋል።
አስከሬናቸው ተጥሎ የተገኘው አመራሩ ላይ የተፈጸመውን ግድያ “ጭካኔ የተሞላበት ነው” ሲል የኦሮሞ ነጻነት ግንባር አውግዞታል።
የፖለቲከኛውን ግድያ የፈጠረበትን ጥልቅ ሐዘን ያሰፈረው መግለጫው ሟቹንም “አንደበተ ርቱዕ፣ ለራሱ የማይሳሳ፣ ጀግና የኦሮሞ ነፍስ” ሲልም ጠርቶታል።
ፓርቲው በግድያው ላይ ተጨማሪ ምርመራ እያደረገ እንደሆነም ጠቅሶ የሰብዓዊ መብት ድርጅቶች አፋጣኝ እና ገለልተኛ ምርመራ እንዲያደርጉ ጠይቋል።
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ዋና ኮሚሽነር ዳንኤል በቀለ (ዶ/ር) እንዲሁ በፖለቲከኛው ግድያ ዙሪያ ነጻ እና ገለልተኛ ምርመራ እንዲደረግ ጥሪ አቅርቧል።
የአሜሪካ የአፍሪካ ጉዳዮች ቢሮ ረቡዕ ሚያዝያ 2/2016 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽንም ያቀረበውንም ጥያቄ በመድገም ሙሉ ምርመራ እንዲደረግ ጥሪ አቅርቧል።
“የጥቃት አዙሪት ለመስበርም ፍትህ እና ተጠያቂነት ወሳኝ ናቸው” ብሏል።
በተደጋጋሚ ጊዜ በሕገወጥ መንገድ መታሰራቸውን ያስታወሱት የሂውማን ራይትስ ዋች የአፍሪካ ቀንድ ዳይሬክተር ላቲሺያ ባደር በበኩላቸው “አሳማኝ ምርመራ እንዲደረግ” በኤክስ ገጻቸው ጠይቀዋል።.
የፖለቲከኛውን ግድያ ተከትሎ የተለያዩ መላምቶች የተሰነዘሩ ሲሆን የኦሮሚያ ክልል በፖለቲከኛው ግድያ ላይ የመንግሥት ኃይሎች አሉበት መባሉን ውድቅ አድርጓል።
ክልሉ ረቡዕ ሚያዝያ 2/2016 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ የታዋቂውን ፖለቲከኛ ግድያ አውግዞ “መንግሥትን ተጠያቂ ለማድረግ የሚሰራው ፕሮፖጋንዳ በፍጹም ተቀባይነት የለውም” ብሏል።
የክልሉ መንግሥት መግለጫ በመቂ ከተማ እስከሬናቸው ተጥሎ የገኙት ፖለቲከኛ የተገደሉት “ባልታወቁ ጥቃት አድራሾች” እንደሆነ ገልጿል።
ሆኖም “ለግድያው መንግሥትን ተጠያቂ በማድረግ የፖለቲካ ኪሳራቸውን ለማካካስ እየሞከሩ ነው ያላቸውን አንዳንድ የፖለቲካ አካላትንም” ሁኔታውን እየተጠቀሙበት እንደሆነም አስፍሯል።
መንግሥት የሕግ የምርመራ ሂደቱን ተከትሎ የበቴ ግድያ ውጤት ለሕዝብ ይፋ እንደሚያደርግ ገልጾ፣ ያልተረጋገጡ ውንጀላዎችን ማሰራጨትን በተመለከተ ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል።
“የፀጥታ ኃይሎች አጣርተው ለሕዝብ እስካላስታወቁ ድረስ ግድያውን የፈጸመው ይህ አካል ነው ብሎ መበየን አይቻልም” ሲል መግለጫው አክሏል።
አቶ በቴ የካቲት አጋማሽ ላይ በቁጥጥር ስር ውለው ለሁለት ሳምንታት ያህል በእስር ከቆዩ በኋላ በ100 ሺህ ብር የገንዘብ ዋስትና የተለቀቁት ከአንድ ወር ገደማ በፊት የካቲት 30/2016 ዓ.ም. ነበር።
አቶ በቴ በፖለቲካ ተሳትፏቸው ምክንያት በተደጋጋሚ ለእስር ሲዳረጉ የቆዩ ፖለቲከኛ ሲሆኑ፤ ከጥቂት ሳምንታት በፊትም ከአንድ ፈረንሳያዊ ጋዜጠኛ ጋር በአዲስ አበባ በቁጥጥር ስር ውለው ነበር።
አቶ በቴ ኡርጌሳ ሐሙስ የካቲት 14/2016 ዓ.ም. ከፈረንሳዊው ጋዜጠኛ አንቷን ጋሊንዶ ጋር በአዲስ አበባ ስካይ ላይት ሆቴል እየተነጋገሩ ሳለ በቁጥጥር ስር ውለው ከሁለት ሳምንታት እስር በኋላ ተለቀዋል።
በወቅቱ መንግሥት የ“አፍሪካ ኢንተለጀንስ” ጋዜጠኛው እና የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር በቁጥጥር ስር የዋሉት “ከፋኖ እና ኦነግ ሸኔ ጋር በመተባባር ሁከት እና ብጥብጥ ለማስነሳት በመንቀሳቀሳቸው ነው” ብሎ ነበር።
በኦሮሞ ፖለቲካ ውስጥ ጉልህ እንቅስቃሴ በማድረግ የሚታወቁት እና በፓርቲያቸው ውስጥ በከፍተኛ ኃላፊነት ላይ የነበሩት አቶ በቴ ከዚህ ከቀደምም ለተደጋጋሚ እስር ሲዳረጉ ቆይተዋል።
በ2013 ዓ.ም. አጋማሽ ላይ በኦሮሚያ ክልል ቡራዩ ከተማ በቁጥጥር ስር የሚገኙ የኦነግ ከፍተኛ አመራሮችን ለመጠየቅ በሄዱበት ተይዘው ረዘም ላለ ጊዜ በእስር መቆየታቸው ይታወሳል።
አቶ በቴ በቡራዩ በእስር በነበሩበት ወቅት አያያዛቸው የሰብዓዊ መብትን ያከበረ አይደለም በማለት ለቀናት የረሃብ አድማ በማድረጋቸው ከፍተኛ የጤና መቃወስ አጋጥሟቸው ነበር።












