የሐማስ መሪ ሦስት ልጆቻቸው በእስራኤል የአየር ጥቃት እንደተገደሉባቸው ተናገሩ

የሐማስ ፖለቲካዊ መሪ እስማኤል ሃኒየህ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, የሐማስ ፖለቲካዊ መሪ እስማኤል ሃኒየህ

የሐማስ ፖለቲካዊ መሪ እስማኤል ሃኒየህ ሦስት ልጆቻቸው እና አራት የልጅ ልጆቻቸው በእስራኤል የአየር ጥቃት ጋዛ ውስጥ መገደላቸውን አረጋገጡ።

ልጆቻቸው ሲጓዙበት የነበረው መኪና በእስራኤል ጥቃት የተፈጸመበት በጋዛ ከተማ አቅራቢያ በሚገኘው አል ሻቲ የስደተኞች መጠለያ ካምፕ መሆኑን ከሐማስ ጋር ግንኙነት ያለው ሚዲያ ዘግቧል።

የልጆቻቸው እና የልጅ ልጆቻቸው መገደል ሐማስ በጋዛ ላይ እንዲደረስ ለሚፈልገው ዘላቂ የተኩስ አቁም ስምምነት ዙሪያ በሚደረገው ንግግር ላይ ለውጥ እንደማያመጣም መሪው ተናግረዋል።

የእስራኤል ጦር የተገደሉት ልጆች የሐማስ ወታደራዊ ክንፍ አባላት ናቸው ብሏል።

የሐማስ መሪ ልጆች የኢድ በዓልን ከሌሎች ቤተሰቦች ጋር ለማክበር እያቀኑ በነበረበት ወቅት ጥቃት እንደተፈጸመባቸው ተዘግቧል።

የሃኒየህ ሦስቱ ወንድ ልጆቻቸው ሐዜም፣ አሚር እና መሐመድ በጦርነቱ ወቅት በጋዛ እንደቆዩ መሪው ለአልጀዚራ ተናግረዋል።

በተጨማሪም ሐማስ፣ አራት የሃኒየህ የልጅ ልጆች ሞና፣ አማል፣ ካሊድ እና ራዘን “አጸያፊ እና ፈሪ” ብሎ በጠራው የእስራኤል ጥቃት እንደተገደሉም አስታውቋል።

ሃኒየህ የልጆቻቸው እና ልጅ ልጆቻቸውን ግድያ የሰሙት በጥቃቱ የቆሰሉ ፍልስጤማውያን ለህክምና የሐማስ ፖለቲካዊ መሪ ወደሚኖሩበት የኳታሯ መዲና ዶሃ በመጡበት ወቅት ነው።

“ጠላት ልጆቼን ኢላማ ማድረጉ እየተደረገ ባለው የተኩስ አቁም ስምምነት እና ቡድኑ ምላሹን ከመላኩ በፊት ጥቃት መፈጸሙ ሐማስ አቋሙን እንዲቀይር ይገፋፋዋል ብሎ ካሰበ ተሳስቷል” በማለትም ፖለቲካዊ መሪው ለአልጀዚራ ገልጸዋል።

በሐማስ የቴሌግራም ቻናል ላይ በሰጡት አስተያየት “ልጆቻቸው እና እና የልጅ ልጆቻው ሰማዕትነት” ክብር ስላመጣላቸው አምላካቸውን አመስግነዋል።

የእስራኤል ጦር በማዕከላዊው ጋዛ ሰርጥ “ሦስት የሐማስ ወታደራዊ ክንፍ ታጣቂዎችን ማስወገዱን” ጠቁሞ የእስማኤል ሃኒየህ ልጆች መሆናቸውን ገልጿል።

መግለጫው የሃኒየህ የልጅ ልጆች መገደላቸውን በተመለከተ ያለው ነገር የለም።

በአስር ሺዎች በሚቆጠሩ ፍልስጤማውያን በተገደሉባት ጋዛ የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ እንዲደረስ ዓለም አቀፋዊ ጫና እየጨመረ ሲሆን፣ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን የሲአይኤ ኃላፊ ዊልያም በርንስን በካይሮ እየተደረገ ላለው የመጨረሻ ዙር ድርድር ልከዋል።