ዘላቂ የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ ለመድረስ በሳዑዲና ሁቲ መካከል ንግግር ሊጀመር ነው

የፎቶው ባለመብት, EPA
ወደ የመኗ ዋና ከተማ ሰንአ ያቀናው የሳዑዲ የልዑክ ቡድን ከሁቲ አማጽያን ጋር የጀመረው አዲስ ንግግር ዘላቂ የተኩስ አቁም ሰምምነት ላይ ለመድረስ ተስፋ ተጥሎበታል።
ሶስተኛ ወገን በመሆን የሚያቀራርበው ከኦማን የተጓዘው ቡድንም ሰንአ ገብቷል።
እአአ 2015 ላይ አማጽያኑ የየመን መንግስትን አስለቅቀው ከተማዋ ከተቆጣጠሯት ወዲህ በአጅቻው ትገኛለች።
ይህ በሆነ በአጭር ጊዜ ውስጥ በአማጽያኑና በሳዑዲ መራሹ ጥምረት በሚመራው መንግስት መካከል ጦርነት ተቀስቅሷል።
እሳከሁን የቀጠለው ጦርነት በ10 ሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ለሞት የዳረገ ሲሆን 80 በመቶ የሚሆነውን ህዝቧን እርዳታ ጠባቂ አድርጓል።
በሁለቱ የጦርነቱ ተዋንያን መካከል የሚደረገው ንግግር ስለመጀመሩ በሳዑዲ በኩል ማረጋገጫ ባይሰጥም የሁቲ የዜና ምንጮች ግን የሳዑዲና የኦማን ልዑክ ቡድኖች ሰንአ መግባታቸውን አስታውቀዋል።
አንድ ሾልኮ የወጣ ፎቶ የሁቲው መሪ ሞሃመድ አሊ አልሁቲ ፊታቸው በግልጽ የማይታይን የሳዑዲ ባለስልጣን እጅ ጨብጠው ይታያሉ።
ይህም ሁለቱ ኃይሎች ጦርነቱን ለማቆም የሚያስችል ስምምነት ላይ ለመድረስ ያላቸውን ፍላጎት የሚያሳይ ቁልፍ ምልክት ነው ተብሏል።
በሰም የተጠቀሰ ባለስልጣን የሰጠው መረጋገጫ ባይኖርም በተያዘው የፈረንጆቹ ወር ጨረሻ ላይ በሁለቱ ኃይሎች መካከል ስምምነት ሊደረስ እንደሚችል በርካታ ምንጮች እየገለጹ ነው።
የስምምነቱ ይዘት እስካሁን ይፋ ባይሆነም የመንግሥት ሰራተኞችን ውጪ መሸፈን እንዲሁም የተዘጉ ወደቦችና አየር ማረፊያዎችን መክፈት ሊያካትት እንደሚችል እና ከዚያም አልፎ ሀገሪቱን መገንባት፣ የውጪ ኃይሎችን ማስወጣትና ፖለቲካዊ ሽግግር ላይ ሊያተኩር እንደሚችል ተገምቷል።
እነዚህ ጉዳዮች ባለፉት ጊዜያት በየመን እጅግ ፈታኝ ሁኔታን የጋረጡ ናቸው።
ይህ የሰላም ስምምነት የምንገስታቱ ድርጅት እየመራው ያለው እና ባለፈው ዓመት ጊዜያዊ የተኩስ ማቆም ስምምነት እንዲደረስ ካደረገው ጥረት ትይዩ የሚሄድ ነው።
ውስብስብ ጦርነት በሚካሄድበት የመን የሳዑዲ መራሹ ጥምረት እና የሁቲ አማጽያን ስምምነት ብቻውን ሁሉም ጦርነቶች እንዲቆሙ ላያደርግ ይችላል።
ለዚህ ደግሞ አልቀይዳ የሚያደርገውን ውጊያ ጨምሮ በርካታ ምክንያቶች ተጠቃሽ ናቸው።
ሆኖም ሳዑዲና ኢራን የመን እጅ አዙር የሚያደርጉት ጦርንት ማክተሚያው የደረሰ ይመስላል፥ ምክንያቱም ሁለቱ የቀጠናው ተቃናቃኝ ኃይሎች ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን ለማደስ ቁርጠኛ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ይህም በሰንአ የሚደረገውን ሰምምነት ውጤታማ ሆኖ እንዲቀጥል እና ጦርነቱ በዘላቂነት እንዲቆም ቁልፍ ሚና ይኖረዋል።












