በኤል ሳልቫዶር ስታዲየም በተፈጠረ ግርግር እና መረጋገጥ ቢያንስ 12 ሰዎች ሞቱ

አደጋው ያጋጠመበት ስታዲየም

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በኤል ሳልቫዶር ዋን ከተማ ሳን ሳልቫዶር የሚገኝ ስታድየም ውስጥ በተፈጠረ ግርግር እና መረጋገጥ ምክንያት ቢያንስ 12 ሰዎች መሞታቸውን ባለሥልጣናት ገለጹ።

አደጋው የተከሰተው በኩስካትላን ስታድየም አሊያንዛ እና ፋስ የተባሉ ቡድኖች ሲጫወቱ በተፈጠረ ግርግር ምክንያት ነው።

ግጥሚያው በአደጋው ምክንያት ሳይገባደድ እንዲቆም ሆኗል።

ፕሬዝዳንት ናይብ ቡኬሌ አደጋውን “ያልተጠበቀ” ብለው “ጠበቅ ያለ ምርመራ” እንደሚካሄድ ተናግረዋል።

የከተማዋ ፖሊስ አደጋው መከሰቱን ተከትሎ ዕድሜያቸው ከ18 በላይ የሆኑ ሰባት ወንዶች እና ሁለት ሴቶች በአደጋው ምክንያት መሞታቸውን አሳውቆ ነበር።

በርካታ ቁጥር ያላቸው ደጋፊዎች የስታድየሙ በር ከተዘጋ በኋላ ወደ ውስጥ ለመግባት በፈጠሩት ግርግር ምክንያት አደጋው እንደተከሰተ ተዘግቧል።

ባለሥልጣናት እንደሚሉት አንዳንድ ደጋፊዎች ሕጋዊ ያልሆነ ቲኬት ገዝተው ወደ ሜዳ መጥተዋል። ይህም እንዲጣራ ምርመራ መጀመሩን ታውቋል።

ማኅበራዊ ሚድያዎች ላይ የተለተጠፉ ተንቃሳቃሽ ምስሎች እንደሚያሳዩት ደጋፊዎች የስታድየሙ መግቢያ ላይ አጥሮችን ለማፍረስ ሲታገሉ ነበር።

በዩቲዩብ የቀጥታ ሥርጭት እግር ኳስ ግጥሚያው ሲተላለፍ እንደታየው በደጋፊዎች መቀመጫ አካባቢ ግርግር ሲፈጠር ጨዋታው እንዲቋረጥ ተደርጓል።

ከቆይታ በኋላ ደጋፊዎች በአደጋ ጊዜ ሠራተኞች እርዳታ ሲደርግላቸው ታይተዋል።

አንድ የአደጋ ጊዜ ሠራተኛ ለጋዜጠኞች እንደተናገረው “ሕዝቡ አንድ ላይ ሆኖ በሩን ገንጥሎት ገብቷል።”

ፕሬዝዳንት ቡኬሌ እንዳሉት ቡድኖች፣ አሠልጣኞች፣ የስታድየሙ አመራሮች እና የሊጉ ባለሥልጣናትን ጨምሮ “ሁሉም ሰው” ምርመራ ይደረግበታል።

የፕሬዝዳንቱ ፕሬስ ሴክሬታሪ በትዊተር ገፃቸው እንደለጠፉት የአገሪቱ መሪ “ሁሉም የዚህ ጥፋት ውስጥ የተሳተፉ ሰዎች የእጃቸውን ያገኛሉ።”

ባለሥልጣናት አክለው እንደገለጡት 90 ሰዎች የሕክምና እርዳታ እየተሰጣቸው ሲሆን ሌሎች ደግሞ እንዲረጋጉ እየተደረገ ነው።

የጤና ሚኒስትሩ ፍራንቺስኮ አላቢ፤ በርካታ ሰዎች የሕክምና እርዳታ እንደተረገላቸው አሳውቀው፣ አብዛኞቹ አሁን በመልካም ጤንነት ላይ እንዳሉ ተናግረዋል።

የሳልቫዶር እግር ኳስ ፌዴሬሽን እሑድ ዕለት የሚከናወኑ ሁሉም ጨዋታዎች ለጊዜ እንደማይካሄዱ አሳውቋል።

ፌዴሬሽኑ በተፈጠረው አደጋ ማዘኑን አሳውቆ ለተጎጂዎች እና ለቤተሰቦቻቸው እርዳታ ለማድረግ ቃል ግብቷል።