የዘንድሮውን የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ ዕጣን የወሰኑ 10 ክስተቶች

ሃላንድ እና ሳካ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ማንቸስተር ሲቲዎች መድፈኞቹን ከሊጉ አናት አውርደው የዘንድሮው ፕሪሚዬር ሊግ የዋንጫ ባለድል ሆነዋል።

አብዛኛውን የውድድር ዘመን ከሚኬል አርቴታ ቡድን ኋላ ሆነው የከረሙት ሲቲዎች በመጨረሻው ወር ዋንጫውን ማንሳት ችለዋል።

በርካታ ክስተቶች በታዩበት የዘንድሮው ፕሪሚዬር ሊግ የዋንጫውን ዕጣ ፈንታ የወሰኑ 10 ክስተቶችን እንመልከት።

1. የሃላንድ የመጀመሪያ ግብ

አሁን ስናስበው ከዘመናት በፊት የሆነ ይመስላል። የውድድር ዘመኑ ሊጀምር አካባቢ በኮሚዩኒቲ ሺልድ ግጥሚያ ኧርሊንግ ሃላንድ ጎል ማግባት ሲሳነው ዳርዊን ኑኔዝ ደግሞ ደምቆ አመሸ። ሊቨርፑል ፍልሚያውን 3 ለ 1 ረታ።

በርካቶች ትችታቸውን አዘነቡ። በሳምንቱ ፕሪሚዬር ሊጉ ጀመረ። ኖርዌያዊው ሃላንድ ሁለት ጎሎች አስቆጥሮ ሲቲ ዌስትሃምን 2 ለ 0 አሸነፈ።

ምንም እንኳን በቀጣዩ ጨዋታ ቦርንመዝ ላይ ጎል ማስቆጠር ባይችል ከዚያ በኋላ በነበሩት ሰባት ጨዋታዎች ጎል አስቆጥሯል።

ሃላንድ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

2. ሲቲ ዩናይትድን የረመረመበት ጨዋታ

የማንቸስተር ደርቢ ሁሌም ተናፋቂ ነው። በመጀመሪያው ደርቢ ሲቲ ጎረቤቱ ዩናይትድን 6 ለ 3 ረመረመ።

ሃላንድ በጨዋታው ‘ሃት-ትሪክ’ ሠራ። በተመሳሳይ ፊል ፎደን ሦስት ግቦችን በማስቆጠር የሲቲን የበላይነት አስጠበቀ።

በወቅቱ የኤሪክ ቴን ሃግ ልጆች መልካም አቋም ላይ ነበሩ። ከዚህ ጨዋታ ጥቂት ሳምንታት በፊት አርሰናልን 3 ለ 2 ረትተው ነበር።

3. የደ ብረይን ድንቅ ግብ

የፈረንጆቹ የጥቅምት ወር ሲገባደድ 22 ጎሎች ያስቆጠረው ሃላንድ ለሲቲ በሁሉም ጨዋታዎች እየተሰለፈ ነበር። ነገር ግን ከሌይስተር ሲቲ ጋር በነበረው ፍልሚያ አልተሰለፈም።

በወቅቱ አርሰናል ከኖቲንግሃም ፎረስት ከመጫወታቸው በፊት ሲቲ ይህን ጨዋታ አሸንፈው በሊጉ አናት ላይ መቀመጥ ፈልገዋል።

ይሄኔ ነው በሁለተኛው አጋማሽ መባቻ ደ ብረይን ከፍፁም ቅጣት ምት ክልል ውጪ እጁን በወገቡ አድርጎ ብቅ ያለው።

ከ25 ሜትር ርቀት ላይ አክርሮ ወደ ግብ የሰደዳት ኳስ መረቡን በመነቅነቅ ለሲቲ ድል አጎናፀፈች።

ደ ብረይን

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

4. የሃላንድ ፍፁም ቅጣት ምት

ይህ የሆነው አርሰናል ሊጉን እየተንፈላሰሰበት በነበረበት ወቅት ነው። ሲቲዎች በዚህ ወቅት ነጥብ ማባከን እንደሌለባቸው ያውቃሉ።

ሲቲዎች በሜዳቸው ኢቲሃድ ከፉልሃም እየተጫወቱ ነው። ያለፉትን ዘጠኝ ጨዋታዎች ረትተዋል።

አንድ ተጫዋች በቀይ ወጥቶባቸው የነበሩት ሲቲዎች፣ በ95ኛው ደቂቃ የፍፁም ቅጣት ምት አገኙ።

ኧርሊንግ ሃላንድ ኳሷን ታቅፎ ወደ መምቻው ሥፍራ ብቅ አለ። ሳያንገራግር ኳሷን ከመረብ ደባለቃት።

ሲቲ ይህን ፍልሚያ ማሸነፉ ከአርሰናል ጋር የነበረው ትንቅንቅ እንዲቀጥል ረድቶታል።

5. ተቀያሪው ማህሬዝ

የዋንጫ ፉክክሩ እንደደራ የፈረንጆቹ መስከረም ጠባ። በዚህ ወቅት አርሰናልን የሚደርስበት አልነበረም።

ማንቸስተር ሲቲ ጥር 5 ወደ ቼልሲ ሜዳ አቀኑ። ይህን ጨዋታ ከተሸነፉ ከአርሰናል ጋር ያላቸው የነጥብ ልዩነት ወደ ስምንት ይሰፋል።

በዚህ ጨዋታ የፔፕ ልጆች ደካማ ሆነው ታዩ። ይሄኔ ነው ጉዋርዲዮላ ማህሬዝ እና ግሪሊሽን ቀይሮ ያስገባው።

ማህሬዝ ከግሪሊሽ የተሻገረችለትን ኳስ ከመረብ አሳርፎ ሲቲ ከስታምፈርድ ብሪጅ ሦስት ነጥብ ይዞ ተመለሰ።

ማህሬዝ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

6. ማንቸስተር ሲቲ ከአርሰናል

እነሆ ቀኑ ደረሰ። የሊጉ መሪ አርሰናል ከማንቸስተር ሲቲ በመድፈኞቹ ሜዳ ተገናኙ። ይህ የአርሰናል ትልቁ ፈተና ነው ተባለ።

አርሰናል ይህን ጨዋታ ከረታ ከሲቲ በሦስት ነጥብ ርቆ ይቀመጣል። ሲቲ በተራው ካሸነፈ ደግሞ ከኅዳር በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ የሊጉ መሪ ይሆናል።

ደ ብረይን የመጀመሪያዋን ጎል ለሲቲ አስቆጠረ። ከቆይታ በኋላ ቡካዮ ሳካ አቻ በማድረግ ኤሜሬትስ ስታድየምን አነቃነቀው።

ነገር ግን ግሪሊሽ እና ሃላንድ ያስቆጠሯቸው ሁለት ጎሎች ድሉ የሲቲ እንዲሆን አደረጉ።

ብዙዎች ይህ ምሽት ነው ዋንጫውን ማን ሊበላው እንደሚችል የጠቆመው ይላሉ።

7. የሳሊባ ጉዳት

የአርሰናል ደጋፊዎችን እንዴት ባለቀ ሰዓት ዋንጫውን አሳልፋችሁ ሰጣችሁ ብትሏቸው አንድ ምክንያት ይነግሯችኋል። የዊሊያም ሳሊባ ጉዳት።

ወጣቱ ፈረንሳዊ ተከላካይ የአርሰናል የጀርባ አጥንት ነበር። ነገር ግን በአውሮፓ ሊግ ፍልሚያ ከስፖርቲንግ ሊዝበን ጋር በነበረው ፍልሚያ ተጎድቶ ወጣ።

አልፎም ሌላኛው ተከላካይ ታኬሂሮ ቶሚያሱ በጉዳት ለወራት ወደ ሜዳ እንደማይመለስ ተሰማ።

አርሰናል በሚቀጥሉት ሰባት ጨዋታዎች መረቡን አለማስደፈር ሳይችል በሁሉም ጨዋታዎች ጎል ተቆጠረበት።

ሳሊባ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

8. አርሰናል ከሊቨርፑል

ወደ አንፊልድ ያቀናው ወጣቱ የአርሰናል ቡድን በሊቨርፑል ሜዳ ከ11 ዓመታት በኋላ ድል ለማድረግ አልሞ ነበር።

አርሰናል በ28 ደቂቃዎች ሁለት ጎሎች በማስቆጠር አንፊልድን ጭጭ አሰኘው። ነገር ግን በዚህ ያልተበገሩት ሊቨርፑሎች ከኋላ ተነስተው 2 ጎል በማስቆጠር አቻ ሆኑ።

ይሄ ነው የዋንጫው ጫና የአርሰናል ተጫዋቾችን እየፈተናቸው እንደሆነ የተገለጠው።

በዚህ ወቅት ሲቲ ከአርሰናል 6 ነጥብ ርቀው ቢገኙም አንድ ቀሪ ጨዋታ እና አንድ ጨዋታ ደግሞ ከአርሰናል ጋር ነበራቸው።

9. የሳካ ፍፁም ቅጣት ምት

ከሊቨርፑል ቀጥሎ አርሰናል ወደ ዌስትሃም አቀና። በ10 ደቂቃ ውስጥ በገብርኤል ሄሱስ እና በማርቲን ኦዴጋርድ ጎሎች 2 ለምንም ይመራ ጀመር።

ቢሆንም ዌስትሃም በሳይድ ቤንራህማ እና በጃሬድ ቦዌን ጎሎች ከአርሰናል ጋር ነጥብ ተጋርቶ መውጣት ቻለ።

የዚህ ጨዋታ ትልቁ ነጥብ የነበረው አርሰናል 2 ለ 1 እየመራ ሳለ ቡካዮ ሳካ ያገኛት ፍፁም ቅጣት ምት ነበረች።

ቡካዮ ሳካ ኳሷን ከጎል ክልል ውጪ በመለጋት ዕድሉን አባከነ።

10. ሲቲ አርሰናልን የረታበት ጨዋታ

ምንም እንኳ አርሰናል ነጥብ እየጣለ የነበረ ቢሆንም በዚህ ወቅት ዋንጫውን የማንሳት ዕድል ነበረው።

የሊጉ መሪ ሆነው ወደ ሲቲ ሜዳ በተስፋ ያቀኑት አርሰናሎች ያሰቡት አልተሳካላቸውም። በሰባተኛው ደቂቃ ደ ብረይን ግላዊ ብቃቱን ያሳየበት ጎል የአርሰናልን ተስፋ በጊዜ አጨለመው።

ሲቲ ሦስት ጎሎች አክሎ ግጥሚያውን 4 ለ 1 ረታ። ይህ ሽንፈት ለመድፈኞቹ ትልቅ አንደምታ ነበረው። የአርሰናል ዋንጫውን የማንሳት ዕድል ወደ 10 በመቶ ጠበበ።

አሁንም ተስፋ ያልቆረጡት አርሰናሎች በሜዳቸው ብራይተንን አስተናግደው በመሸነፋቸው ከፈረንጆቹ 2004 በኋላ ዋንጫ ለማንሳት የነበራቸው ተስፋ ከሰመ።